መዝሙር 103 – New Amharic Standard Version (NASV)

New Amharic Standard Version

መዝሙር 103:1-22

መዝሙር 103

እግዚአብሔር ፍቅር ነው

የዳዊት መዝሙር

1ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ

የውስጥ ሰውነቴም ሁሉ ቅዱስ ስሙን ባርኪ።

2ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤

ውለታውንም ሁሉ አትርሺ፤

3ኀጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፣

ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፣

4ሕይወትሽን ከጥፋት ጒድጓድ የሚያድን፣

ምሕረትንና ርኅራኄን የሚያቀዳጅሽ፣

5ጐልማሳነትሽም እንደ ንስር ይታደስ ዘንድ፣

ምኞትሽን በበጎ ነገር የሚያረካ እርሱ ነው።

6እግዚአብሔር ለተጨቈኑ ሁሉ፣

ቅን ፍርድንና ፍትሕን ይሰጣቸዋል።

7መንገዱን ለሙሴ፣

ሥራውንም ለእስራኤል ሕዝብ አሳወቀ።

8እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፣

ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩም የበዛ ነው።

9እርሱ ሁል ጊዜ በደልን አይከታተልም፤

ለዘላለምም አይቈጣም።

10እንደ ኀጢአታችን አልመለሰልንም፤

እንደ በደላችንም አልከፈለንም።

11ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣

እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ ታላቅ ናት።

12ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣

መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ።

13አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣

እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል።

14እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤

ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።

15ሰው እኮ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤

እንደ ዱር አበባ ያቈጠቍጣል፤

16ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ግን ድራሹ ይጠፋል፤

ምልክቱም በቦታው አይገኝም።

17የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣

ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤

ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤

18ኪዳኑን በሚጠብቁት ላይ፣

ትእዛዙንም ለመፈጸም በሚተጉት ላይ ይሆናል።

19እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አጽንቶአል፤

መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች።

20እናንተ ለቃሉ የምትታዘዙ መላእክቱ፤

ትእዛዙንም የምትፈጽሙ እናንተ ኀያላን፤

እግዚአብሔርን ባርኩ።

21እናንተ ፈቃዱን የምትፈጽሙ አገልጋዮቹ፤

ሰራዊቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ።

22እናንተ በግዛቱ ሁሉ የምትኖሩ፣

ፍጥረቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ፤

ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ።