መክብብ 5 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መክብብ 5:1-20

እግዚአብሔርን ፍራ

1ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትሄድ እግርህን ጠብቅ። ለመስማት መቅረብ የሰነፎችን መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጣል፤ እነርሱ ክፉ እንደሚሠሩ አያውቁምና።

2በአፍህ አትፍጠን፤

በእግዚአብሔርም ፊት ማንኛውንም ነገር ለመናገር፣

በልብህ አትቸኵል፤

እግዚአብሔር በሰማይ፣

አንተ ደግሞ በምድር ነህ፤

ስለዚህ ቃልህ ጥቂት ይሁን።

3በሥራ ብዛት ሕልም እንደሚታይ፣

ብዙ ቃል ባለበትም የሞኝ ንግግር ይገለጣል።

4ለእግዚአብሔር ስእለትን በተሳልህ ጊዜ ለመፈጸም አትዘግይ፤ በሰነፎች ደስ አይለውምና፤ ስእለትህን ፈጽም። 5ስእለት ተስሎ ካለመፈጸም፣ አለመሳል ይሻላል። 6አንደበትህ ወደ ኀጢአት እንዲመራህ አትፍቀድ፤ ለቤተ መቅደስ መልእክተኛም፣ “የተሳልሁት በስሕተት ነበር” አትበል። እግዚአብሔር በተናገርኸው ተቈጥቶ የእጅህን ሥራ ለምን ያጥፋ? 7ብዙ ሕልምና ብዙ ቃል ከንቱ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን ፍራ።

ባለጠግነት ከንቱ ነው

8በአገር ውስጥ ድኻ ተጨቍኖ፣ ፍትሕ ተጓድሎ፣ መብትም ተረግጦ ብታይ፣ እንደነዚህ ባሉ ነገሮች አትደነቅ፤ ምክንያቱም አንዱን አለቃ የበላዩ ይመለከተዋል፤ በእነዚህ በሁለቱም ላይ ሌሎች ከፍ ያሉ አሉ። 9ከምድሩ የሚገኘው ትርፍ ለሁሉም ነው፤ ንጉሡም ራሱ የሚጠቀመው ከዕርሻ ነው።

10ገንዘብን የሚወድድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤

ብልጽግናም የሚወድድ፣ በትርፉ አይረካም፤

ይህም ከንቱ ነው።

11ሀብት በበዛ ቍጥር፣

ተጠቃሚውም ይበዛል፤

በዐይኑ ብቻ ከማየት በቀር

ታዲያ፣ ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል?

12ጥቂትም ይሁን ብዙ ቢበላ፣

የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፤

የሀብታም ሰው ብልጽግና ግን

እንቅልፍ ይነሣዋል።

13ከፀሓይ በታች የሚያሳዝን ክፉ ነገር አየሁ፦

ይህም ለባለቤቱ ጕዳት የተከማቸ ሀብት፣

14ወይም በአንድ መጥፎ አጋጣሚ የጠፋ ብልጽግና ነው፤

ልጅ ሲወልድም፣

ለእርሱ የሚያስቀርለት ምንም ነገር አይኖርም።

15ሰው ከእናቱ ማሕፀን ዕራቍቱን ይወለዳል፤

እንደ መጣው እንዲሁ ይመለሳል።

ከለፋበትም ነገር፣

አንድም እንኳ በእጁ ይዞ ሊሄድ አይችልም።

16ይህ ደግሞ እጅግ ክፉ ነገር ነው፤

ሰው እንደ መጣ እንዲሁ ይሄዳል፤

የሚደክመው ለነፋስ ስለሆነ፣

ትርፉ ምንድን ነው?

17በብዙ ጭንቀት፣ መከራና ብስጭት፣

ዘመኑን ሁሉ በጨለማ ውስጥ ይበላል።

18የሰው ዕጣው ይህ ስለሆነ፣ እግዚአብሔር በሰጠው በጥቂት ዘመኑ ከፀሓይ በታች በሚደክምበት ነገር ርካታን ያገኝ ዘንድ፣ መብላቱና መጠጣቱም መልካምና ተገቢ መሆኑን ተገነዘብሁ። 19እግዚአብሔር ለሰው ባለጠግነትና ሀብት መስጠቱ፣ እንዲደሰትበትም ማስቻሉ፣ ዕጣውን እንዲቀበልና በሥራውም እንዲደሰት ማድረጉ፣ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 20እግዚአብሔር የልብ ደስታ ስለሚሰጠውም በሕይወቱ ዘመን ያሉትን ቀናት እምብዛም አያስባቸውም።