New Amharic Standard Version

መሳፍንት 8:1-35

ዛብሄልና ስልማና

1በዚህ ጊዜ የኤፍሬም ሰዎች፣ “ምድያማውያንን ለመውጋት ስትሄድ ለምን አልጠራኸንም? ለምንስ እንዲህ ያለ ነገር አደረግህ?” በማለት ጌዴዎንን እጅግ ነቀፉት።

2ጌዴዎን ግን፣ “እናንተ ካደረጋችሁት ጋር ሲነጻጸር የእኔ ከምን ይቈጠራል? የኤፍሬም የወይን ቃርሚያ ተጠቃሎ ከገባው ከአቢዔዝር የወይን መከር አይበልጥምን? 3እግዚአብሔር የምድያማውያንን መሪዎች ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ ታዲያ እናንተ ከፈጸማችሁት ጋር የሚወዳደር ምን ማድረግ እችል ነበር?” ይህን ሲሰሙ ቍጣቸው በረደ።

4ጌዴዎንና ሦስት መቶዎቹ ሰዎች ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ምንም እንኳ ድካም ቢሰማቸውም ጠላቶቻቸውን ያሳድዱ ነበር። 5የሱኮትንም ሰዎች፣ “የምድያምንም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን በማሳደድ ላይ ስለ ሆንሁ የተከተሉኝም ሰዎች ስለ ደከሙብኝ እባካችሁ የሚበሉትን እንጀራ ስጧቸው” አላቸው።

6የሱኮት ሹማምት ግን፣ “ለተከተሉህ ሰዎች እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዛብሄልና ስልማና በእጅህ ገብተዋልን?” አሉት።

7ጌዴዎንም መልሶ፣ “ደህና፤ እግዚብሔር ዛብሄልንና ስልማናን በእጄ አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ በምድረ በዳ እሾኽና አሜከላ ሥጋችሁን እተለትላለሁ” አላቸው።

8ከዚያም ወደ ጵኒኤል ሰዎች ሄዶ ያንኑ ጥያቄ አቀረበላቸው፤ የእነርሱም መልስ የሱኮት ሰዎች ከሰጡት መልስ ጋር አንድ ዐይነት ነበር። 9እርሱም የጵኒኤልን ሰዎች፣ “በድል አድራጊነት በሰላም ስመለስ ከተማችሁን የምትጠብቁበትን ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ” አላቸው።

10በዚህ ጊዜ ዛብሄልና ስልማና ዐሥራ አምስት ሺህ ከሆነ ሰራዊታቸው ጋር ቀርቀር በተባለ ስፍራ ነበሩ፤ ይህም ከምሥራቅ ሕዝቦች ከተውጣጣውና በጦር ሜዳ ከወደቀው መቶ ሃያ ሺህ ሰይፍ ታጣቂ ሰራዊት የተረፈው ነበር። 11ከዚያም ጌዴዎን ተነሣ፤ ከኖባህና ከዮግብሃ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩ ዘላኖች የሚሄዱበትን መንገድ ተከትሎ በጠላት ሰራዊት ላይ በድንገት አደጋ ጣለ። 12ሁለቱ የምድያም ነገሥታት ዛብሄልና ስልማና ሸሹ፤ ጌዴዎን ግን አሳዶ ያዛቸው፤ መላ ሰራዊታቸውንም እጅግ በታተነው።

13ከዚህ በኋላ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን በሐሬስ መተላለፊያ በኩል አድርጎ ከጦርነቱ ተመለሰ፤ 14እርሱም የሱኮት ሰው የሆነ አንድ ወጣት ማረከ፤ መረመረውም፤ ወጣቱም የሰባ ሰባት የሱኮት ሹማምትና የከተማዪቱንም አለቆች ስም ጻፈለት። 15ከዚያም ጌዴዎን ወደ ሱኮት ሰዎች መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ ‘ለደከሙት ሰዎችህ እንጀራ እንሰጥ ዘንድ ዛብሄልና ስልማና በእጅህ ገብተዋልን’ በማለት ያላገጣችሁብኝ ዛብሄልና ስልማና እነዚሁላችሁ።” 16ጌዴዎን የከተማዪቱን አለቆች ወሰደ፤ በምድረ በዳ እሾኽና አሜኬላ በመቅጣት የሱኮትን ሰዎች ትምህርት ሰጣቸው። 17እንዲሁም በጵኒኤል ያለውን የከተማ መጠበቂያ ግንብ አፈረሰ፤ የከተማዪቱንም ሰዎች ገደለ።

18ዛብሄልና ስልማናንም፣ “በታቦር ላይ የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ?” በማለት ጠየቃቸው።

እነርሱም፣ “ሁሉም እንዲህ እንዳንተ ያሉ የንጉሥ ልጆች የሚመስሉ ናቸው” አሉት።

19ጌዴዎንም፣ “እነርሱ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ናቸው፤ ባትገድሏቸው ኖሮ እኔም እንደማልገድላችሁ በሕያው እግዚአብሔር ስም አረጋግጥላችሁ ነበር።” ብሎ መለሰላቸው። 20ከዚያም ወደ በኵር ልጁ ወደ ዮቴር ዘወር ብሎ፣ “ግደላቸው” አለው፤ ዮቴር ግን ትንሽ ልጅ ነበርና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም።

21ዛብሄልና ስልማናም፣ “የሰው ጒልበቱ እንደ ሰውነቱ መጠን ነውና አንተው ራስህ ግደለን አሉት፤ ጌዴዎንም ተነሥቶ ገደላቸው፤ በግመሎቻቸው አንገት ላይ የነበሩትንም ጌጦች ወሰደ።

የጌዴዎን ኤፉድ

22እስራኤላውያንም ጌዴዎንን፣ “ከምድያማውያን እጅ ታድገኸናልና አንተ፣ ልጅህና የልጅ ልጅህ ግዙን” አሉት።

23ጌዴዎን ግን መልሶ፣ “እኔም ሆንሁ ልጄ አንገዛችሁም፤ የሚገዛችሁ እግዚአብሔር ነው” አላቸው። 24እርሱም፣ “አንድ የምጠይቃችሁ ነገር አለኝ፤ ይኸውም እያንዳንዳችሁ ከምርኮ ካገኛችሁት ውስጥ የጆሮ ጒትቻችሁን እንድ ትሰጡኝ ነው” አላቸው፤ የወርቅ ጒትቻ ማድረግ የእስማኤላውያን ባህል ነበርና።

25እነርሱም መልሰው፤ “ደስ እያለን እንሰጥሃለን” አሉት፤ ወዲያው ልብስ አነጠፉ፤ በላዩም ላይ እያንዳንዳቸው ከማረኩት ውስጥ የጆሮ ጒትቻ ጣል ጣል አደረጉለት። 26ሌሎቹን ጌጣጌጦች ይኸውም የዐንገት ሐብሉን ከነእንጥልጥሉ፣ የምድያም ነገሥታት ይለብሱት የነበረውን ሐምራዊ ልብስ ወይም በግመሎቻቸው ዐንገት ላይ ያሉትን ጌጦች ሳይጨምር ጌዴዎን በጠየቃቸው መሠረት የሰጡት የወርቅ ጒትቻ ክብደት ሺህ ሰባት መቶ ሰቅል8፥26 19.5 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ያህል መዘነ።

27ጌዴዎን በወርቁ ኤፉድ ሠራ፤ በተወለደበትም ከተማ በዖፍራ አኖረው። እስራኤልም በሙሉ ኤፉዱን በማምለክ ስላመነዘሩ፣ ኤፉዱ ለጌዴዎንና ለቤተ ሰቡ ወጥመድ ሆነ።

የጌዴዎን መሞት

28ስለዚህ ምድያማውያን በእስራኤላውያን ተሸነፉ፤ ዳግመኛም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም። ጌዴዎን በሕይወት እስካለ ጊዜ ድረስ ምድሪቱ አርባ ዓመት ሰላም አገኘች።

29የኢዮአስ ልጅ ይሩባኣል ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ በዚያም ተቀመጠ፤ 30ብዙ ሚስቶች ስላገባ ሰባ ልጆች ነበሩት፤ 31በሴኬም የምትኖረው ቁባቱም እንደዚሁ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ አለው። 32የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ በአቢዔዝራውያን ምድር ባለችው በዖፍራ፣ በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ።

33ጌዴዎን ሞቶ ብዙም ሳይቈይ እስራኤላውያን የበኣልን አማልክት በማምለክ አመነዘሩ፤ በኣልብሪትንም አምላካቸው አደረጉ፤ 34በዙሪያቸው ከነበሩት ጠላቶቻቸው እጅ የታደጋቸውን እግዚአብሔር አምላካቸውን አላሰቡትም። 35እንዲሁም ይሩባኣል የተባለው ጌዴዎን ያደረገላቸውን በጎ ነገር ሁሉ አስበው ለቤተ ሰቡ ውለታ መላሽ ሆነው አልተገኙም።

Knijga O Kristu

This chapter is not available yet in this translation.