መሳፍንት 12 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መሳፍንት 12:1-15

ዮፍታሔና ኤፍሬም

1የኤፍሬም ሰዎች ኀይላቸውን አሰባስበው ወደ ጻፎን በመሻገር ዮፍታሔን፣ “አሞናውያንን ለመውጋት ስትወጣ አብረንህ እንድንሄድ ያልጠራኸን ለምንድን ነው? ቤትህን በላይህ ላይ እናቃጥለዋለን አሉት።”

2ዮፍታሔም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔና ሕዝቤ ከአሞናውያን ጋር ከፍተኛ ትግል ገጥመን በነበረበት ጊዜ ጠርቼያችሁ ከእጃቸው አላዳናችሁኝም፤ 3እኔም እንደማትረዱኝ በተረዳሁ ጊዜ በሕይወቴ ቈርጬ አሞናውያንን ለመውጋት ተሻገርሁ፤ እግዚአብሔርም ድሉን ሰጠኝ። ታዲያ ዛሬ እኔን ለመውጋት የመጣችሁት ለምንድን ነው?”

4ከዚያም ዮፍታሔ የገለዓድን ሰዎች አሰባስቦ ከኤፍሬም ጋር ተዋጋ። ኤፍሬማውያን ገለዓዳውያንን፣ “እናንተ ገለዓዳውያን ከኤፍሬምና ከምናሴ የከዳችሁ ናችሁ” ይሏቸው ስለ ነበር በብርቱ መቷቸው። 5ገለዓዳውያን ወደ ኤፍሬም የሚያሻግሩትን የዮርዳኖስን መልካዎች ያዙ። ታዲያ አምልጦ የሚሸሽ አንድ ኤፍሬማዊ ለመሻገር በሚጠይቃቸው ጊዜ፣ የገለዓድ ሰዎች “አንተ ኤፍሬማዊ ነህ?” ብለው ይጠይቁታል፤ ያም ሰው፣ “አይደለሁም” ብሎ ከመለሰላቸው፣ 6እስቲ “ሺቦሌት” በል ይሉታል፤ ቃሉን በትክክል ማለት ሳይችል ቀርቶ “ሲቦሊት” ካለ፣ ይዘው እዚያው እመልካው ላይ ይገድሉታል። በዚያ ጊዜም አርባ ሁለት ሺሕ ኤፍሬማውያን ተገደሉ።

7ዮፍታሔ በእስራኤል ላይ ለስድስት ዓመት ፈራጅ12፥7 በዚህ እንዲሁም በቍጥር 8-14 ላይ ባለው ክፍል በትውፊት መሳፍንት ይባላል። ሆነ። ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ሞተ፤ ከገለዓድም ከተሞች በአንዲቱ ተቀበረ።

ኢብጻን፣ ኤሎም፣ ዔብዶን

8ከዮፍታሔ ቀጥሎ የቤተ ልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ። 9እርሱም ሠላሳ ወንዶችና ሠላሳ ሴቶች ልጆች ነበሩት። ሴቶች ልጆቹንም ከጐሣው ውጭ ለሆኑ ሰዎች ዳራቸው፤ ከጐሣው ውጭ የሆኑ ሠላሳ ልጃገረዶች አምጥቶ ከወንዶች ልጆቹ ጋር አጋባቸው። ኢብጻን በእስራኤል ላይ ሰባት ዓመት ፈራጅ ሆነ። 10ኢብጻን ሞተ፤ በቤተ ልሔምም ተቀበረ።

11ከእርሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎም በእስራኤል ላይ ዐሥር ዓመት ፈራጅ ሆነ። 12ከዚያም ኤሎም ሞተ፤ በዛብሎን ምድር በኢያሎን ተቀበረ።

13ከኤሎም ቀጥሎ የጲርዓቶናዊው የሂሌል ልጅ ዓብዶን በእስራኤል ፈራጅ ሆነ። 14እርሱም በሰባ አህዮች ላይ የሚቀመጡ አርባ ወንዶች ልጆችና ሠላሳ ወንዶች የልጅ ልጆች ነበሩት፤ በእስራኤልም ላይ ስምንት ዓመት ፈራጅ ሆነ። 15ከዚያም የሂሌል ልጅ ዓብዶን ሞተ፤ ኰረብታማ በሆነው በአማሌቃውያን አገር በኤፍሬም ምድር በጲርዓቶን ተቀበረ።