ሕዝቅኤል 6 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሕዝቅኤል 6:1-14

ስለ እስራኤል ተራሮች የተነገረ ትንቢት

1የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አዙር፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፤ 3እንዲህም በል፤ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኰረብቶች፤ ለገደላገደሎችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል፤ ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፤ የማምለኪያ ኰረብቶቻችሁን አጠፋለሁ። 4መሠዊያዎቻችሁ ይፈርሳሉ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁም ይሰባበራሉ፤ የታረዱ ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ። 5የእስራኤላውያንን ሬሳ በጣዖቶቻችሁ ፊት አጋድማለሁ፤ ዐጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ። 6መሠዊያዎቻችሁ እንዲፈራርሱና እንዲወድሙ፣ ጣዖቶቻችሁ እንዲሰባበሩና እንዲደቅቁ፣ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁ እንዲንኰታኰቱ፣ የእጆቻችሁም ሥራ እንዲደመሰስ፣ የምትኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ባድማ ይሆናሉ፤ ማምለኪያ ኰረብቶችም እንዳልነበሩ ይሆናሉ። 7የታረዱ ሰዎቻችሁ በመካከላችሁ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

8“ ‘በአሕዛብ መካከል ስትበተኑ፣ አንዳንዶቻችሁ ከሰይፍ ታመልጣላችሁና፣ ጥቂት ሰዎችን አስቀራለሁ። 9እነዚህ ከሰይፍ የተረፉት፣ ከእኔ ዘወር ባለ አመንዝራ ልባቸውና ጣዖትን በተከተለ አመንዝራ ዐይናቸው የቱን ያህል እንዳሳዘኑኝ፤ በአሕዛብ ምድር ሆነው ያስታውሱኛል፤ ካደረጉት ክፋትና ከፈጸሙት ርኩስ ተግባር ሁሉ የተነሣም ራሳቸውን ይጸየፋሉ። 10እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ይህንም ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ ብዬ የተናገርሁት በከንቱ አይደለም።

11“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤል ቤት ካደረጉት ክፋትና ከፈጸሙት ጸያፍ ተግባራቸው ሁሉ የተነሣ በሰይፍ በራብና በቸነፈር ይወድቃሉና፤ በእጅህ እያጨበጨብህ በእግርህም መሬት እየረገጥህ፣ “ወየው!” ብለህ ጩኽ። 12በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፤ በቅርብ ያለው በሰይፍ ይወድቃል፤ በሕይወት የተረፈውና የዳነው በራብ ያልቃል። መዓቴንም በዚህ ዐይነት ሁኔታ በእነርሱ ላይ እፈጽማለሁ። 13የታረዱት ሰዎቻቸው በመሠዊያው ዙሪያ በጣዖቶቻቸው መካከል፣ ከፍ ባሉ ኰረብቶች ሁሉና በተራሮች ዐናት ሁሉ ላይ፣ በለመለመ ዛፍ ሁሉና ቅጠሉ በበዛ ወርካ ሁሉ ሥር፣ በአጠቃላይ ለጣዖቶቻቸው ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን ባቀረቡበት ስፍራ ሁሉ ተጥለው ሲታዩ፣ ያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 14እጄን በእነርሱ ላይ አነሣለሁ፤ የሚኖሩበትንም ስፍራ ከምድረ በዳው እስከ ዴብላታ6፥14 አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆች እንዲሁ ናቸው፤ ጥቂት የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆች ግን ሪብላህ ይላሉ ድረስ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፤ ያን ጊዜም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”