ሕዝቅኤል 36 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሕዝቅኤል 36:1-38

ለእስራኤል ተራሮች የተነገረ ትንቢት

1“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ተራሮች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 2ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ጠላት ስለ አንቺ፣ “ዕሠይ! እነዚያ የጥንት ተራሮች የእኛ ርስት ሆነዋል ብሏል።” ’ 3ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከየአቅጣጫው ከብበው በመውጋት ስላጠቋችሁ፣ ለቀሩት ሕዝቦች ሁሉ ርስት ሆናችሁ፤ ለሕዝብም መሣቂያና መሣለቂያ ሆናችሁ። 4ስለዚህ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኰረብቶች፣ ለሸለቆዎችና ለውሃ መውረጃዎች፣ ለፈራረሱ ባድማዎችና፣ በሌሎቹ በዙሪያችሁ ባሉት ሕዝቦች ተዘርፈውና መዘባበቻ ሆነው መና ለቀሩት ከተሞች እንዲህ ይላል፤ 5ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሚቃጠል ቅናቴ በቀሩት ሕዝቦች ሁሉና በኤዶም ሁሉ ላይ ተናግሬአለሁ፤ ከልብ በመነጨ ደስታና በንቀት ተሞልተው የግጦሽ መሬቴን ይዘው ይበዘብዙት ዘንድ የራሳቸው ርስት አድርገውታልና።’ 6ስለዚህ የእስራኤልን ምድር የሚመለከት ትንቢት ተናገር፤ ለተራሮች፣ ለኰረብቶች፣ ለሸለቆዎችና ለውሃ መውረጃዎች እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሕዝቦች ዘለፋ ስለ ተሠቃያችሁ ቍጣ በተሞላ ቅናቴ እናገራለሁ።” 7ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እጄን አንሥቼ እምላለሁ፤ በዙሪያችሁ ያሉ ሕዝቦች ዘለፋ ይወርድባቸዋል።”

8“ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፣ እናንተ ግን፤ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቅርንጫፍ ታወጣላችሁ፤ ፍሬም ታፈራላችሁ፤ በቅርቡ ወደ አገራቸው ይመለሳሉና። 9ስለ እናንተ ይገድደኛል፤ በበጎነትም እመለከታችኋለሁ፤ ትታረሳላችሁ፤ ዘርም ይዘራባችኋል። 10መላው የእስራኤል ቤት እንኳ ሳትቀሩ፣ የሰዎችን ቍጥር በእናንተ ላይ አበዛለሁ። ከተሞች የሰው መኖሪያ ይሆናሉ፤ የፈረሱት እንደ ገና ይሠራሉ። 11በእናንተ ላይ የሰዎችንና የእንስሳትን ቍጥር እጨምራለሁ፤ ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ቍጥራቸውም ይበዛል። እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ ሰዎች በውስጣችሁ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ካለፈው የበለጠ አበለጽጋችኋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 12ሰዎችን፣ ሕዝቤን እስራኤልን በእናንተ ላይ እንዲመላለሱ አደርጋለሁ፤ ይወርሷችኋል፤ እናንተም ርስታቸው ትሆናላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ አልባ አታደርጓቸውም።

13“ ‘ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሕዝቡ እናንተን፣ “ሰዎችን ቦጫጭቀው ይበላሉ፤ ሕዝብንም ልጅ አልባ ያደርጋሉ” ስላሏችሁ፣ 14ከእንግዲህ ሰው አትበሉም፤ ሕዝቡንም ልጅ አልባ አታደርጉትም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር15ከእንግዲህ የሕዝቦችን ዘለፋ እንድትሰሙ አላደርግም፤ በሰዎችም ስድብ አትሠቃዩም፤ ከእንግዲህ ለሕዝባችሁ መሰናክል አትሆኑም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

16እንደ ገና የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 17“የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ሕዝብ በገዛ ምድራቸው ይኖሩ በነበረበት ጊዜ በሥራቸውና በአኗኗራቸው አረከሷት፤ ጠባያቸውም በፊቴ፣ ሴት በወር አበባዋ ወቅት እንደምትረክሰው ዐይነት ነበር። 18ስለዚህ በምድሪቱ ላይ ደም ስላፈሰሱና በጣዖታቶቻቸው ስላረከሷት፣ መዓቴን አፈሰስሁባቸው። 19በአሕዛብ መካከል በተንኋቸው፤ እነርሱም በየአገሩ ተበታተኑ፤ እንደ ጠባያቸውና እንደ ሥራቸው መጠን ፈረድሁባቸው። 20በአሕዛብ መካከል በሄዱበት ሁሉ ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለ እነርሱ፣ ‘እነዚህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ናቸው፤ ዳሩ ግን የእርሱን ምድር ትተው እንዲሄዱ ተገደዱ’ ተብሏልና። 21የእስራኤል ቤት በሄዱበት በአሕዛብ መካከል ሁሉ፣ ስላረከሱት ቅዱስ ስሜ ገድዶኛል።

22“ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ይህን ሁሉ የማደርገው ስለ እናንተ ብዬ ሳይሆን፣ በየሄዳችሁባቸው አሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ነው። 23በአሕዛብ መካከል የረከሰውን፣ እናንተ በእነርሱ ዘንድ ያረከሳችሁትን፣ የታላቁን ስሜን ቅድስና አሳያለሁ፤ ከዚያም ዐይኖቻቸው እያዩ፣ በእናንተ አማካይነት ራሴን ቅዱስ አድርጌ ስገልጥ፣ አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

24“ ‘ከአሕዛብ መካከል አስወጣችኋለሁ፤ ከየአገሩ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራችሁም መልሼ አመጣችኋለሁ። 25ንጹሕ ውሃ እረጫችኋለሁ፤ እናንተም ንጹሕ ትሆናላችሁ፤ ከርኩሰታችሁ ሁሉና ከጣዖታቶቻችሁ ሁሉ አነጻችኋለሁ። 26አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ የድንጋይ ልባችሁን ከእናንተ አስወግዳለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። 27መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ ሥርዐቴን እንድትከተሉና ሕጌን በጥንቃቄ እንድትጠብቁ አደርጋለሁ። 28ለቀድሞ አባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝቤም ትሆናላችሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋሁ። 29ከርኩሰታችሁ ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህሉን እጠራለሁ፤ አበዛዋለሁም፤ ራብንም አላመጣባችሁም። 30ከራብ የተነሣ በአሕዛብ መካከል በውርደት እንዳትሳቀቁ፣ የዛፉን ፍሬና የዕርሻውን ሰብል አበዛለሁ። 31ከዚያም ክፉ መንገዳችሁንና የረከሰ ሥራችሁን ታስታውሳላችሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁና ስለ አስጸያፊ ድርጊታችሁ ራሳችሁን ትጠላላችሁ። 32ለእናንተ ስል ይህን እንደማላደርግ እንድታውቁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ በአድራጎታችሁ ዕፈሩ፤ ተሸማቀቁ!

33“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከኀጢአታችሁ ሁሉ በማነጻችሁ ቀን፣ ከተሞቻችሁ እንደ ገና መኖሪያ ይሆናሉ። የፈረሱትም እንደ ገና ይታደሳሉ። 34በዐላፊ አግዳሚው ዐይን ጠፍ ሆኖ ይታይ የነበረው ባድማ መሬት ይታረሳል። 35እነርሱም፣ “ጠፍ የነበረው ይህ ምድር እንደ ዔድን ገነት መሰለ፤ የተደመሰሱ፣ የፈራረሱና ባድማ የሆኑት ከተሞች አሁን መኖሪያና ምሽግ ሆነዋል” ይላሉ። 36ከዚያም በዙሪያችሁ የነበሩ የቀሩት አሕዛብ ፈርሶ የነበረውን መልሼ የሠራሁ፣ ጠፍ የነበረውን ያለመለምሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ እኔም አደርገዋለሁ።’

37“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እንደ ገና ለእስራኤል ቤት ልመና እሺ እላለሁ፤ ይህንም አደርግላቸዋለሁ፤ ሕዝባቸውን እንደ በግ መንጋ አበዛዋለሁ፤ 38በኢየሩሳሌም በዓላት ላይ እንደሚገኘው የመሥዋዕት በግ መንጋ አበዛዋለሁ። እነሆ! ፈራርሰው የነበሩት ከተሞች የብዙ ሕዝብ መኖሪያ ይሆናሉ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”