ሕዝቅኤል 35 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሕዝቅኤል 35:1-15

በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት

1የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ሴይር ተራራ አዙር፤ ትንቢትም ተናገርበት፤ 3እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የሴይር ተራራ ሆይ፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ እጄን በአንተ ላይ እዘረጋለሁ፤ ባድማና ጠፍ አደርግሃለሁ። 4ከተሞችህን ፍርስራሽ አደርጋቸዋለሁ፤ ባድማ ትሆናለህ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ።

5“ ‘እስራኤላውያን ቅጣታቸው እጅግ መራራ ከሆነ ደረጃ ላይ ደርሶ ፍዳቸውን በሚቀበሉበት ጊዜ፣ የጥንቱን ቂም ቋጥረህ ለሰይፍ ስለ ዳረግሃቸው፤ 6በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ለደም ማፍሰስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ እርሱም ያሳድድሃል። ደም ማፍሰስን ስላልጠላህ፣ ደም ማፍሰስ ያሳድድሃል። 7የሴይርን ተራራ ባድማና ጠፍ አደርጋለሁ፤ በእርሱም ላይ የሚወጡትንና የሚወርዱትን አስቀራለሁ። 8ተራሮችህን በሬሳ እሞላለሁ፤ በሰይፍ የተገደሉት ሁሉ በተራሮችህ፣ በሸለቆዎችህና በውሃ መውረጃዎችህ ሁሉ ላይ ይወድቃሉ። 9ለዘላለም ባድማ አደርግሃለሁ፤ ከተሞችህ መኖሪያ አይሆኑም። ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

10“ ‘እኔ እግዚአብሔር በዚያ እያለሁ፣ “እነዚህ ሁለት ሕዝቦችና ሁለት አገሮች የእኛ ይሆናሉ፤ እኛም እንወርሳቸዋለን።” ብለሃልና፤ 11ስለዚህ በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከጥላቻችሁ የተነሣ በእነርሱ ላይ በገለጣችሁት ቍጣና ቅናት ልክ እፈርድባችኋለሁ፤ በእናንተም ላይ በምፈርድበት ጊዜ፣ ማንነቴ በእነርሱ መካከል እንዲታወቅ አደርጋለሁ። 12ከዚያም ስለ እስራኤል ተራሮች፣ “ጠፍ ሆነዋል፤ ቦጫጭቀን እንድንበላቸው ለእኛ ተሰጥተዋል” ብለህ በንቀት የተናገርኸውን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሰማሁ በዚያን ጊዜ ታውቃለህ። 13በእኔ ላይ ታብየሃል፤ በድፍረትም በእኔ ላይ ተናግረሃል፤ እኔም ሰምቼዋለሁ። 14ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ መላዪቷ ምድር በምትደሰትበት ጊዜ፣ አንተን ባድማ አደርግሃለሁ። 15የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ በሆነች ጊዜ ስለ ተደሰትህ፣ እኔም እንዲሁ አደርግብሃለሁ። የሴይር ተራራ ሆይ፤ አንተና መላዋ ኤዶም ባድማ ትሆናላችሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”