ሕዝቅኤል 32 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሕዝቅኤል 32:1-32

ስለ ፈርዖን የወጣ ሙሾ

1በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ በዐሥራ ሁለተኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ሙሾ አውርድ፤ እንዲህም በለው፤

“ ‘አንተ በሕዝቦች መካከል እንደ አንበሳ፣

በባሕሮችም ውስጥ እንደ አስፈሪ አውሬ ነህ፤

በወንዞችህ የምትንቦጫረቅ፣

ውሃውን በእግርህ የምትመታ፣

ምንጮችን የምታደፈርስ ነህ።

3“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘ብዙ ሕዝብ ይዤ፣

መረቤን በላይህ ላይ እጥላለሁ፤

በመረቤም ጐትተው ያወጡሃል።

4በምድር ላይ እጥልሃለሁ፤

ሜዳም ላይ እዘረጋሃለሁ፤

የሰማይ ወፎች ሁሉ እንዲሰፍሩብህ አደርጋለሁ፤

የምድር አራዊት ሁሉ በመስገብገብ ይበሉሃል።

5ሥጋህን በተራሮች ላይ እበታትነዋለሁ፤

የተረፈውንም በየሸለቆው እሞላዋለሁ።

6እስከ ተራሮች ባለው መንገድ ሁሉ፣

በሚፈስሰው ደምህ ምድሪቱን አርሳታለሁ፤

ሸለቆዎችም በሥጋህ ይሞላሉ።

7አንተን በማጠፋ ጊዜ ሰማያትን እሸፍናለሁ፤

ከዋክብታቸውንም አጨልማለሁ፤

ፀሓይን በደመና እሸፍናለሁ፤

ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም።

8በሰማይ የሚያበሩትን ብርሃናት ሁሉ፣

በአንተ ላይ አጨልማለሁ፤

በምድርህ ላይ ጨለማን አመጣለሁ፤

ይላል ጌታ እግዚአብሔር

9በማታውቀው ምድር፣

በሕዝቦች መካከል ያንተን ጥፋት ሳመጣ፣32፥9 በዕብራይስጡም እንዲሁ ሲሆን ሰብዐ ሊቃናት ግን በአሕዛብ መካከል ወደ ምርኮ ሳመጣው ይላል

የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ።

10ሕዝቦች በአንተ ላይ ከደረሰው የተነሣ እንዲደነግጡ አደርጋለሁ፤

ሰይፌን በፊታቸው ስነቀንቅ፣

በአንተ ላይ ከደረሰው ሁኔታ የተነሣ ንጉሦቻቸው ይንቀጠቀጣሉ።

አንተ በምትወድቅበት ቀን፣

እያንዳንዳቸው ስለ ራሳቸው ሕይወት በመፍራት፣

በየቅጽበቱ ይርበደበዳሉ።

11“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤

“ ‘የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ፣

በአንተ ላይ ይመጣል።

12ከሕዝቦች ሁሉ እጅግ ጨካኝ በሆኑት፣

በኀያላን ሰዎች ሰይፍ፣

ያከማቸኸው ሰራዊት እንዲወድቅ አደርጋለሁ፤

የግብፅን ኵራት ያንኰታኵታሉ፤

የሰራዊቷም ብዛት ይጠፋል፤

13ብዙ ውሃ ባለበት አጠገብ ያለውን፣

የከብት መንጋዋን አጠፋለሁ፤

ከእንግዲህ የሰው እግር አይረጋግጠውም፤

የከብትም ኰቴ አያደፈርሰውም።

14ከዚያም ውሆቿን አጠራለሁ፤

ወንዞቿም እንደ ዘይት እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤

ይላል ጌታ እግዚአብሔር

15ግብፅን ባድማ ሳደርጋት፣

ምድሪቱም ያላትን ሁሉ ያጣች ስትሆን፣

በዚያም የሚኖሩትን ሁሉ ስመታ፣

ያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’

16“ስለ እርሷ የሚያወርዱት ሙሾ ይህ ነው፤ የሕዝቦች ሴት ልጆች ያዜሙታል፤ ስለ ግብፅና ስለ ብዙ ሰራዊቷ ሁሉ ሙሾ ያወርዳሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

17በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ ከወሩም በዐሥራ አምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 18“የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ብዙው የግብፅ ሰራዊት አልቅስ፤ እርሷንና የኀያላንን ሕዝቦች ሴት ልጆች ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋር ከምድር በታች አውርዳቸው። 19እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንተ ከሌሎች የተለያችሁ ናችሁን? ውረዱ፤ ባልተገረዙትም መካከል ተጋደሙ።’ 20እነርሱም በሰይፍ በተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፤ ሰይፉ ተመዝዟል፤ ከብዙ ሰራዊቷ ሁሉ ጋር ትጐተት። 21በመቃብርም32፥21 ዕብራይስጡ ሲኦል ይላል፤ በ27 ትም እንዲሁ ውስጥ ኀያላኑ መሪዎች ስለ ግብፅና ስለ ተባባሪዎቿ፣ ‘ወደ ታች ወርደዋል፤ በሰይፍ ከተገደሉትና ካልተገረዙትም ጋር በአንድ ላይ ተጋድመዋል’ ይላሉ።

22“አሦር ከመላው ሰራዊቷ ጋር በዚያ ትገኛለች፤ በሰይፍ በወደቁባትና በታረዱባት ሰዎች ሁሉ መቃብር ተከብባለች። 23መቃብራቸው በጥልቁ ጕድጓድ ውስጥ ነው፤ ሰራዊቷም በመቃብሯ ዙሪያ ተረፍርፏል። በሕያዋን ምድር ሽብርን የነዙ ሁሉ ታርደዋል፤ በሰይፍም ወድቀዋል።

24“ኤላም በዚያ አለች፤ ሰራዊቷም ሁሉ በመቃብሯ ዙሪያ አለ፤ ሁሉም ታርደዋል፤ በሰይፍ ወድቀዋል። በሕያዋን ምድር ሽብር የነዙ ሁሉ ሳይገረዙ ከምድር በታች ወርደዋል፤ ወደ ጕድጓድ ከወረዱት ጋር ዕፍረታቸውን ተሸክመዋል፤ 25በመቃብሯ ዙሪያ ካለው መላው ሰራዊቷ ጋር፣ በታረዱት መካከል መኝታ ተዘጋጅቶላታል። ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ ሽብራቸው በሕያዋን ምድር ስለ ተነዛ፣ ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋር ዕፍረታቸውን ይሸከማሉ፤ በታረዱትም መካከል ይጋደማሉ።

26“ሞሳህና ቶቤል መቃብሮቻቸው በብዙ ሰራዊታቸው መቃብር ተከብበው ይገኛሉ፤ ሁሉም ያልተገረዙ ሲሆኑ፣ በሕያዋን ምድር ሽብራቸውን ስለ ነዙ በሰይፍ ተገድለዋል። 27ከዘመናት በፊት ከወደቁት ከኀያላን ሰዎች፣ ከእነዚያ ሰይፋቸውን ተንተርሰው፣ ጋሻቸውንም ደረታቸው ላይ ይዘው ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ መቃብር ከወረዱት ጋር አይጋደሙምን? የእነዚህ ተዋጊዎች ሽብር በሕያዋን ምድር ባሉት ኀያላን ላይ ቢደርስም፣ የኀጢአታቸው ቅጣት በዐጥንታቸው ላይ ይሆናል።

28“ፈርዖን ሆይ፤ አንተም እንደዚሁ ትሰበራለህ፤ በሰይፍ ከተገደሉት ከእነዚያ ካልተገረዙት ጋር ትጋደማለህ።

29“ኤዶምም በዚያ አለች፤ ንጉሦቿና ገዦቿም ሁሉ በዚያ አሉ፤ ኀይል የነበራቸው ቢሆኑም፣ በሰይፍ ከተገደሉት ጋር ተጋድመዋል፤ ወደ ጕድጓድ ከወረዱት ከእነዚያ ካልተገረዙትም ጋር ተኝተዋል።

30“የሰሜን ገዦች በሙሉ፣ ሲዶናውያንም ሁሉ በዚያ ይገኛሉ፤ ከዚህ በፊት በኀይላቸው ምክንያት ሽብር የፈጠሩ ቢሆኑም፣ ከታረዱት ጋር በኀፍረት ወረዱ፤ ሳይገረዙም በሰይፍ ከተገደሉት ጋር ይጋደማሉ፤ ወደ ጕድጓድ ከወረዱትም ጋር ኀፍረታቸውን ይሸከማሉ።

31“ፈርዖንና ሰራዊቱ ሁሉ ያዩአቸዋል፤ በሰይፍ ከተገደለበት ሰራዊትም ሁሉ ሐዘን ይጽናናል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር32በሕያዋን ምድር ሽብር እንዲያስፋፋ ብፈቅድም እንኳ፣ ፈርዖንና ሰራዊቱ ሁሉ በሰይፍ ከተገደሉት ጋር ባልተገረዙት መካከል ይጋደማሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”