ጳውሎስ በመላጥያ ደሴት
1በደኅና ወደ ምድር ከደረስን በኋላ፣ ደሴቲቱ መላጥያ ተብላ እንደምትጠራ ተረዳን። 2የደሴቲቱ ነዋሪዎችም የሚያስገርም ደግነት አሳዩን፤ ዝናብና ብርድ ነበርና እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። 3ጳውሎስም ጭራሮ ሰብስቦ ወደ እሳቱ ሲጨምር፣ ከሙቀቱ የተነሣ እፉኝት ወጥታ እጁ ላይ ተጣበቀች። 4የደሴቲቱ ነዋሪዎች እባብ በእጁ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ነፍስ ገዳይ ነው፤ ከባሕር ቢያመልጥ እንኳ የፍርድ አምላክ በሕይወት እንዲኖር አልፈቀደለትም” ተባባሉ። 5ጳውሎስ ግን እባቢቱን ወደ እሳቱ አራገፋት፤ አንዳችም ጕዳት አልደረሰበትም። 6ሰዎቹ ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል ወይም ድንገት ሞቶ ይወድቃል ብለው ይጠባበቁ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ጠብቀው ምንም የተለየ ነገር እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ፣ ሐሳባቸውን ለውጠው፣ “ይህስ አምላክ ነው” አሉ።
7በዚያም ስፍራ አጠገብ የደሴቲቱ አለቃ የፑፕልዮስ ርስት የሆነ መሬት ነበረ፤ እርሱም በቤቱ ተቀብሎን ሦስት ቀን በቸርነት አስተናገደን። 8የፑፕልዮስም አባት በትኵሳትና በተቅማጥ ሕመም ተይዞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ሊጠይቀው ገብቶ ከጸለየለት በኋላ፣ እጁን ጭኖ ፈወሰው። 9ይህም በሆነ ጊዜ፣ በደሴቲቱ የነበሩ ሌሎች ሕመምተኞችም እየመጡ ተፈወሱ። 10እኛንም በብዙ መንገድ አከበሩን፤ በመርከብም ለመሄድ በተዘጋጀን ጊዜ፣ የሚያስፈልገንን ሁሉ ጫኑልን።
ጳውሎስ ሮም ደረሰ
11ከሦስት ወር በኋላም፣ በደሴቲቱ ክረምቱን ቆሞ በሰነበተ በአንድ መርከብ ተነሥተን ጕዞ ጀመርን። ይህም መርከብ የእስክንድርያ ሲሆን፣ በላዩ ላይ የመንታ አማልክቱ የዲዮስቆሮስ አርማ ነበረበት። 12ወደ ሰራኩስ ከተማ ገብተን ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጥን። 13ከዚያም በመርከብ ተጕዘን ሬጊዩም ደረስን፤ በማግስቱም የደቡብ ነፋስ ስለ ተነሣ ፑቲዮሉስ የደረስነው በሚቀጥለው ቀን ነበር። 14በዚያም ወንድሞችን አገኘን፤ እነርሱም ሰባት ቀን አብረናቸው እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሮም ሄድን። 15በዚያ የነበሩ ወንድሞችም መምጣታችንን ስለ ሰሙ፣ እስከ አፍዩስ ፋሩስ እንዲሁም “ሦስት ማደሪያ” እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን ወጡ፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ተጽናናም። 16ሮም በደረስን ጊዜም፣ ጳውሎስ ይጠብቀው ከነበረው ወታደር ጋር ለብቻው በዚያ እንዲቈይ ተፈቀደለት።
ጳውሎስ በጥበቃ ሥር ሆኖ ሰበከ
17ከሦስት ቀንም በኋላ፣ ጳውሎስ የአይሁድን መሪዎች በአንድነት ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፤ እኔ፣ ሕዝባችንን ወይም የአባቶቻችንን ሥርዐት የሚቃረን ምንም ሳላደርግ፣ በኢየሩሳሌም አስረው ለሮማውያን አሳልፈው ሰጥተውኛል። 18እነርሱም መርምረው ለሞት የሚያበቃ በደል ስላላገኙብኝ፣ ሊፈቱኝ ፈልገው ነበር፤ 19አይሁድ በተቃወሙ ጊዜ ግን፣ ለቄሳር ይግባኝ ማለት ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስስበት ምክንያት ኖሮኝ አይደለም። 20እናንተንም ለማየትና ለማነጋገር የጠራኋችሁ በዚሁ ምክንያት ነው፤ በዚህ ሰንሰለት የታሰርሁትም ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው።”
21እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ስለ አንተ ከይሁዳ ምድር የተጻፈ አንድም ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ከዚያ የመጡ ወንድሞችም ስለ አንተ ያቀረቡት ወይም የተናገሩት አንዳች መጥፎ ነገር የለም። 22ይሁን እንጂ፣ ሰዎች ስለዚህ የእምነት ክፍል በየቦታው ክፉ እንደሚያወሩበት እናውቃለን፤ የአንተ አስተያየት ደግሞ ምን እንደ ሆነ መስማት እንፈልጋለን።”
23ቀን ከቀጠሩለትም በኋላ፣ ብዙ ሆነው ወደ ማረፊያ ስፍራው መጡ፤ እርሱም ከጧት ጀምሮ እስከ ማታ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየመሰከረ ያብራራላቸው ነበር፤ ከሙሴ ሕግና ከነቢያትም በመጥቀስ ስለ ኢየሱስ ሊያሳምናቸው ሞከረ። 24አንዳንዶቹ እርሱ የሚለውን አምነው ተቀበሉ፤ ሌሎቹ ግን አላመኑበትም፤ 25እርስ በርሳቸውም አልተስማሙም፤ ጳውሎስም እንዲህ የሚል የመጨረሻ ቃል ከተናገራቸው በኋላ ሄዱ፤ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አማካይነት ለአባቶቻችሁ በትክክል እንዲህ ብሎ ተናግሯል፤
26“ ‘ወደዚህ ሕዝብ ሂድ፤ እንዲህም በላቸው፤
“መስማትን ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤
ማየትን ታያላችሁ፤ ነገር ግን አትመለከቱም።”
27የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኗልና፤
ጆሯቸውም ተደፍኗል፤
ዐይናቸውንም ጨፍነዋል።
አለዚያማ፣ በዐይናቸው አይተው፣
በጆሯቸው ሰምተው፣
በልባቸው አስተውለው፣
ይመለሱና እፈውሳቸዋለሁ።’
28“ስለዚህ የእግዚአብሔር ማዳን ለአሕዛብ እንደ ተላከ እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ እነርሱም ይሰሙታል።” 29ይህንም ከተናገረ በኋላ፣ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ።28፥29 አንዳንድ የጥንት ትርጕሞች ይህ ቍጥር የላቸውም።
30ጳውሎስም ራሱ በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ ወደ እርሱ የሚመጡትንም ሁሉ በደስታ ይቀበል ነበር፤ 31ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ፣ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ግልጽነት ያስተምር ነበር።