New Amharic Standard Version

ሉቃስ 9:1-62

የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መላክ

9፥3-5 ተጓ ምብ – ማቴ 10፥9-15፤ ማር 6፥8-11

9፥7-9 ተጓ ምብ – ማቴ 14፥1፡2፤ ማር 6፥14-16

1ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት በአንድነት ጠርቶ አጋንንትን ሁሉ እንዲያወጡ፣ ደዌንም እንዲፈውሱ ኀይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ 2ደግሞም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩና የታመሙትን እንዲፈውሱ ላካቸው፤ 3እንዲህም አላቸው፤ “ለመንገዳችሁ በትር ቢሆን፣ ከረጢትም ቢሆን፣ እንጀራም ቢሆን፣ ገንዘብም ቢሆን፣ ሁለት ሁለት እጀ ጠባብም መያዝ አያስፈልጋችሁም። 4ከዚያ ከተማ እስከምትወጡ ድረስ መጀመሪያ በገባችሁበት በማንኛውም ቤት ቈዩ። 5የከተማው ሰዎች ሳይቀበሏችሁ ቀርተው ከተማቸውን ለቃችሁ ስትሄዱ፣ ምስክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ።” 6እነርሱም በዚሁ መሠረት ወጥተው ወንጌልን እየሰበኩ በየቦታው ሁሉ ሕመምተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።

7የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም፣ በዚህ ጊዜ የሆነውን ነገር ሁሉ ሰምቶ በሁኔታው ተደናገረ፤ ምክንያቱም አንዳንድ ሰዎች ዮሐንስ ከሙታን እንደ ተነሣ ያወሩ ነበር፤ 8ሌሎች ኤልያስ እንደ ተገለጠ፣ ሌሎች ደግሞ ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሙታን እንደ ተነሣ ይናገሩ ነበር። 9ሄሮድስም፣ “መጥምቁ ዮሐንስን እኔው ራሴ ዐንገቱን አስቈርጬው ሞቶአል፤ ታዲያ፣ ስለ እርሱ እንዲህ ሲወራ የምሰማው ይህ ሰው ማነው?” አለ፤ በዐይኑም ሊያየው ይሻ ነበር።

ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መገበ

9፥10-17 ተጓ ምብ – ማቴ 14፥13-21፤ ማር 6፥32-44፤ ዮሐ 6፥5-13

9፥13-17 ተጓ ምብ – 2ነገ 4፥42-44

10ሐዋርያትም ተመልሰው በመጡ ጊዜ ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት፤ እርሱም ይዞአቸው ቤተ ሳይዳ ወደምትባል ከተማ በመሄድ ለብቻው ገለል አለ። 11ሕዝቡም ይህንኑ ዐውቀው ተከተሉት፤ እርሱም ተቀብሎአቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስ የሚያስፈልጋቸውንም ፈወሳቸው።

12ቀኑም ሊመሽ ሲል፣ ዐሥራ ሁለቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ያለ ነው በምድረ በዳ ስለ ሆነ፣ ሕዝቡ ወደ አካባቢው መንደርና ገጠር ሄደው ማደሪያና ምግብ እንዲፈልጉ አሰናብታቸው” አሉት።

13እርሱ ግን፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው።

እነርሱም፣ “ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ሄደን ካልገዛን በስተቀር፣ እኛ ያለን ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ አይበልጥም” አሉት፤ 14አምስት ሺህ ያህል ወንዶች በዚያ ነበሩና።

ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሕዝቡን በአምሳ በአምሳ ሰው መድባችሁ አስቀምጧቸው” አላቸው። 15ደቀ መዛሙርቱም በታዘዙት መሠረት ሰዎቹ እንዲቀመጡ አደረጉ። 16እርሱም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ እያየ ባረካቸው፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ። 17ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ከእነርሱ የተረፈውን ቊርስራሽ እንጀራ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ።

ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ማንነት መሰከረ

9፥18-20 ተጓ ምብ – ማቴ 16፥13-16፤ ማር 8፥27-29

9፥22-27 ተጓ ምብ – ማቴ 16፥21-28፤ ማር 8፥31–9፥1

18ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ይጸልይ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ እርሱም፣ “ሕዝቡ እኔን ማን ነው ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው።

19እነርሱም፣ “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ከቀድሞ ነቢያት አንዱ ከሙታን ተነሥቶአል ይላሉ” አሉት።

20እርሱም፣ “እናንተስ ማን ነው ትሉኛላችሁ?” አላቸው።

ጴጥሮስም፣ “አንተ የእግዚአብሔር መሲሕ9፥20 ወይም ክርስቶስ ነህ” ሲል መለሰለት።

21ኢየሱስም ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ 22ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሓፍት ዘንድ መናቅ፣ መገደልና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን መነሣት አለበት” አላቸው።

23ከዚያም ለሁሉም እንዲህ አላቸው፤ “በኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየዕለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ፤ 24ምክንያቱም ነፍሱን ሊያድናት የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ ብሎ የሚያጠፋት ግን ያድናታል። 25ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ጥቅሙ ምንድን ነው? 26ማንም በእኔና በቃሌ ቢያፍር፣ የሰው ልጅ በራሱ ክብር እንዲሁም በአብና በቅዱሳን መላእክት ክብር ሲመጣ ያፍርበታል። 27እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔርን መንግሥት ሳያዩ ሞትን የማይቀምሱ ሰዎች አሉ።”

የኢየሱስ መልክ መለወጥ

9፥28-36 ተጓ ምብ – ማቴ 17፥1-8፤ ማር 9፥2-8

28ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ሊጸልይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ። 29በመጸለይ ላይ እንዳለም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ የሚያንጸባርቅ ነጭ ሆነ። 30እነሆ፤ ሁለት ሰዎች፣ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ 31በክብርም ተገልጠው፣ በኢየሩሳሌም ይፈጸም ዘንድ ስላለው ከዚህ ዓለም ስለ መለየቱ ይናገሩ ነበር። 32ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት ግን እንቅልፍ ተጭኖአቸው ነበር፤ ሲነቁ ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር የቆሙትን ሁለት ሰዎች አዩ። 33ሰዎቹም ከኢየሱስ ተለይተው ሲሄዱ፣ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ እዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ሦስት ዳስ እንሥራ፤ አንዱ ለአንተ፣ አንዱ ለሙሴ፣ አንዱም ለኤልያስ ይሆናል” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር።

34ይህንም እየተናገረ ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ፈሩ። 35ከደመናውም ውስጥ፣ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። 36ድምፁም በተሰማ ጊዜ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ፤ ደቀ መዛሙርቱም ነገሩን በልባቸው ያዙ እንጂ ስላዩት ነገር በዚያን ወቅት ለማንም አልተናገሩም።

ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ ያለበትን ልጅ ፈወሰ

9፥37-42፡43-45 ተጓ ምብ – ማቴ 17፥14-18፡22፡23፤ ማር 9፥14-27፡30-32

37በማግሥቱ ከተራራው ከወረዱ በኋላ፣ ብዙ ሕዝብ መጥቶ ኢየሱስን አገኘው። 38በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “መምህር ሆይ፤ ያለኝ ልጅ እርሱ ብቻ ስለ ሆነ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ። 39መንፈስ ሲይዘው በድንገት ይጮኻል፤ አረፋ እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፤ ጒዳትም ካደረሰበት በኋላ በስንት መከራ ይተወዋል፤ 40ደቀ መዛሙርትህ እንዲያወጡለት ለመንኋቸው፤ ነገር ግን አልቻሉም።”

41ኢየሱስም “እምነት የለሽ ጠማማ ትውልድ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? በል ልጅህን ወደዚህ አምጣው” አለ።

42ልጁ በመምጣት ላይ ሳለም ጋኔኑ መሬት ላይ ጥሎ አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን9፥42 ወይም ክፉ መንፈስ ገሥጾ ልጁን ፈወሰው፤ ለአባቱም መልሶ ሰጠው። 43ሰዎቹም ሁሉ በእግዚአብሔር ታላቅነት ተገረሙ።

እርሱ ባደረገው ሁሉ ሰዎች ሁሉ እየተገረሙ ሳሉ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣ 44“ይህን የምነግራችሁን ነገር ከቶ እንዳትዘነጉ፤ የሰው ልጅ አልፎ በሰዎች እጅ ይሰጣልና” አለ። 45እነርሱ ግን ይህን አባባል አልተረዱም፤ እንዳያስተውሉ ነገሩ ተሰውሮባቸው ነበር፤ መልሰው እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?

9፥46-48 ተጓ ምብ – ማቴ 18፥1-5

9፥46-50 ተጓ ምብ – ማር 9፥33-40

46ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ክርክር ተነሣ። 47ኢየሱስም የልባቸውን ሐሳብ ተረድቶ፣ አንድ ሕፃን ይዞ በአጠገቡ አቆመ፤ 48እንዲህም አላቸው፤ “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ማንም ቢኖር እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ደግሞ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና።”

49ዮሐንስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየን፤ ከእኛ ጋር ሆኖ ስለ ማይከተል ልንከለክለው ሞከርን” አለው።

50ኢየሱስም፣ አትከልክሉት “የማይቃወማችሁ ሁሉ እርሱ ከእናንተ ጋር ነውና” አለው።

የሰማርያ ሰዎች ተቃውሞ

51ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ በመቃረቡ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ፤ 52አስቀድሞም መልእክተኞችን ወደዚያ ላከ። እነርሱም ሁኔታዎችን አስቀድመው ሊያመቻቹለት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር ገቡ። 53ሕዝቡ ግን ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ መሆኑን ስላወቁ አልተቀበሉትም። 54ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ሲያዩ፣ “ጌታ ሆይ፤ ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ9፥54 አንዳንድ ቅጆች ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ የሚለው የላቸውም እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት። 55ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና9፥55-56 አንዳንድ ቅጆች ገሠጻቸው፤ 56ከዚያም ወደ ሌላ መንደር ሄዱ ይላሉ። በቍ 55 ላይ በትእምርተ ጥቅሱ ውስጥ የሚገኘው ዐረፍተ ነገር ተአማኒ በሆኑ ብዙ የጥንት ቅጆች ላይ አይገኝም። “እናንተ ከምን ዐይነት መንፈስ እንደሆናችሁ አታውቁም፤ የሰው ልጅ የመጣው የሰውን ሕይወት ለማዳን ነው እንጂ ለማጥፋት አይደለምና” አላቸው፤ 56ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።

ደቀ መዝሙርነት የሚያስከፍለው ዋጋ

9፥57-60 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥19-22

57በመንገድ ሲሄዱም አንድ ሰው ቀርቦ፣ “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።

58ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጒድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ዐንገቱን እንኳ የሚያስገባበት የለውም” አለው።

59ሌላውን ሰው ግን፣ “ተከተለኝ” አለው።

ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን ልቅበር” አለው።

60ኢየሱስም፣ “ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፤ አንተ ግን ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” አለው።

61ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መከተልስ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን ልመለስና መጀመሪያ የቤቴን ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለ።

62ኢየሱስ ግን፣ “ዕርፍ ጨብጦ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” አለው።