ሆሴዕ 12 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሆሴዕ 12:1-14

1ኤፍሬም የነፋስ እረኛ ነው፤

ቀኑን ሙሉ የምሥራቅን ነፋስ ይከተላል፤

ሐሰትንና ዐመፅን ያበዛል።

ከአሦር ጋር ቃል ኪዳን ያደርጋል፤

የወይራ ዘይትንም ወደ ግብፅ ይልካል።

2እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ የሚያቀርበው ክስ አለው፤

ያዕቆብን12፥2 ያዕቆብ ማለት ተረከዝ ይይዛል ማለት ሲሆን፣ ያታልላል ለማለት ዘይቤአዊ አገላለጽ ነው። እንደ መንገዱ ይቀጣዋል፤

እንደ ሥራውም ይከፍለዋል።

3በማሕፀን ሳለ የወንድሙን ተረከዝ ያዘ፤

ሙሉ ሰውም ሲሆን ከአምላክ ጋር ታገለ።

4ከመልአኩም ጋር ታገለ፤ አሸነፈውም፤

በፊቱ ሞገስን ለማግኘት አልቅሶ ለመነው፣

እርሱንም በቤቴል አገኘው፤

በዚያም ከእርሱ ጋር ተነጋገረ፤

5እርሱም ሁሉን የሚገዛ አምላክ እግዚአብሔር

የሚታወቅበት ስሙም እግዚአብሔር ነው።

6ስለዚህ ወደ አምላክህ ተመለስ፤

ፍቅርንና ፍትሕን ጠብቅ፤

ዘወትርም በአምላክህ ታመን።

7ነጋዴው በሐሰተኛ ሚዛን ይሸጣል፤

ማጭበርበርንም ይወድዳል።

8ኤፍሬም እንዲህ እያለ ይታበያል፤

“እኔ ባለጠጋ ነኝ፤ ሀብታምም ሆኛለሁ፤

ይህ ሁሉ ሀብት እያለኝ፣

ምንም ዐይነት በደል ወይም ኀጢአት አያገኙብኝም።”

9“ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ፣12፥9 ወይም በግብፅ ከነበራችሁበት ጊዜ አንሥቶ አምላካችሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤

በዓመት በዓላችሁ ቀን ታደርጉ እንደ ነበረው ሁሉ፣

እንደ ገና በድንኳኖች እንድትቀመጡ

አደርጋችኋለሁ።

10ለነቢያት ተናገርሁ፤

ራእይንም አበዛሁላቸው፤

በእነርሱም በኩል በምሳሌ ተናገርሁ።”

11ገለዓድ ክፉ ነው፤

ሕዝቡም ከንቱ ናቸው፤

ኮርማዎችን በጌልገላ ይሠዋሉን?

መሠዊያዎቻቸው በታረሰ መሬት ላይ እንዳለ፣

የድንጋይ ክምር ይሆናሉ።

12ያዕቆብ ወደ ሶርያ12፥12 ሰሜን መስጴጦምያን ያመለክታል ሸሸ፤

እስራኤል ሚስት ለማግኘት ሲል አገለገለ፤

ዋጋዋንም ለመክፈል በጎችን ጠበቀ።

13እግዚአብሔር በነቢይ አማካይነት እስራኤልን ከግብፅ አወጣ፤

በነቢይም በኩል ተንከባከበው።

14ኤፍሬም ግን ክፉኛ አስቈጣው፤

ጌታውም የደም አፍሳሽነቱን በደል በላዩ ላይ ያደርግበታል፤

ስለ ንቀቱም የሚገባውን ይከፍለዋል።