መዝሙር 47:1-9 NASV

መዝሙር 47:1-9

መዝሙር 47

እግዚአብሔር፣ የእስራኤል ንጉሥና የዓለም ጌታ

ለመዘምራን አለቃ፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር።

ሕዝቦች ሁላችሁ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፤

ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር እልል በሉ።

በምድር ሁሉ ላይ ታላቅ የሆነው ንጉሥ፣

ልዑል እግዚአብሔር የሚያስፈራ ነውና።

ሕዝቦችን ከእኛ በታች አደረገ፤

መንግሥታትንም ከእግራችን ሥር አስገዛልን።

ለሚወድደው ለያዕቆብ ክብር የሆነችውን፣

ርስታችንን እርሱ መረጠልን። ሴላ

አምላክ በእልልታ፣

እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።

አምላካችንን አወድሱት፤ አወድሱት፤

ንጉሣችንን አወድሱት፤ አወድሱት፤

እግዚአብሔር የምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፤

ምርጥ ዝማሬ47፥7 ዕብራይስጡ ማስኪል ይላል፤ ይኸውም የሥነ ጽሑፉን ቅርጽ ወይም የሙዚቃውን ሁኔታ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። አቅርቡለት።

እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ ነግሧል፤

እግዚአብሔር በተቀደሰ ዙፋኑ ላይ ተቀምጧል።

ከአብርሃም አምላክ ሕዝብ ጋር፣

የሕዝቦች መኳንንት ተሰበሰቡ፤

የምድር ነገሥታት47፥9 ወይም ጋሾች የእግዚአብሔር ናቸውና፤

እርሱም እጅግ ከፍ ከፍ ያለ ነው።

Read More of መዝሙር 47