መዝሙር 113:1-9 NASV

መዝሙር 113:1-9

መዝሙር 113

ለታላቁና ለመሓሪው ጌታ ምስጋና

ሃሌ ሉያ።113፥1 እግዚአብሔር ይመስገን ማለት ሲሆን፣ በ9 ላይም ይገኛል።

የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሆይ፤ አመስግኑት፤

የእግዚአብሔርን ስም አወድሱ።

ከአሁን እስከ ዘላለም፣

የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን።

ከፀሓይ መውጫ እስከ መግቢያው ድረስ፣

የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን።

እግዚአብሔር ከሕዝቦች ሁሉ በላይ ከፍ ያለ ነው፤

ክብሩም ከሰማያት በላይ ነው።

እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር

በላይ በዙፋኑ የተቀመጠ ማን ነው?

በሰማይና በምድር ያሉትንስ ለማየት፣

ራሱን ወደ ታች ዝቅ የሚያደርግ ማን ነው?

ድኻውን ከትቢያ ያነሣል፤

ችግረኛውን ከዐመድ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤

ከመኳንንትም እኩል ስፍራ ይሰጠዋል፤

ከሕዝቡም ሹማምት ጋር ያስቀምጠዋል።

መካኒቱን ሴት በቤት ያኖራታል፤

ደስተኛም የልጆች እናት ያደርጋታል።

ሃሌ ሉያ።

Read More of መዝሙር 113