ዘኍል 27:12-23, ዘኍል 28:1-31, ዘኍል 29:1-11 NASV

ዘኍል 27:12-23

ኢያሱ በሙሴ እግር ተተካ

ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በዓባሪም ሸንተረር ላይ ወዳለው ወደዚህ ተራራ ውጣና ለእስራኤላውያን የሰጠኋቸውን ምድር እይ። ካየኸውም በኋላ አንተም እንደ ወንድምህ እንደ አሮን ወደ ሕዝብህ ትሰበሰባለህ፤ ምክንያቱም ማኅብረ ሰቡ በጺን ምድረ በዳ ባለው ውሃ አጠገብ ባመፁ ጊዜ እኔን በሕዝቡ ፊት ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ሁለታችሁም ትእዛዜን ስላልጠበቃችሁ ነው።” ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ የሚገኝ የመሪባ ውሃ ነው።

ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “የሰብአዊ ፍጡር ሁሉ መንፈስ አምላክ (ኤሎሂም) የሆነ ጌታ እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህ ማኅበረ ሰብ ላይ ሰው ይሹም፤ እርሱም፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሕዝብ እረኛ እንደሌለው የበግ መንጋ እንዳይሆን በፊቱ የሚወጣና የሚገባ፣ መርቶ የሚያወጣውና የሚያገባው እንዲሆን ነው።”

ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “መንፈስ ቅዱስ27፥18 ወይም መንፈስ ያደረበትን የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን ጫንበት። በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበር ፊት እንዲቆም አድርገው፤ በፊታቸውም ሹመው፤ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ እንዲታዘዝለትም ከሥልጣንህ ከፍለህ ስጠው። እርሱም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ሆኖ በኡሪም በመጠየቅ ውሳኔ በሚያስገኝለት በካህኑ በአልዓዛር ፊት ይቆማል፤ እርሱም ሆነ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ በአልዓዛር ትእዛዝ ይወጣሉ፤ በእርሱም ቃል ይገባሉ።”

ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በመላው የእስራኤል ማኅበር ፊት አቆመው፤ ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት ባዘዘው መሠረት እጁን በራሱ ላይ ጭኖ ሾመው።

Read More of ዘኍል 27

ዘኍል 28:1-31

የየዕለቱ መሥዋዕት

እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ይህን ትእዛዝ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ስጣቸው፤ ‘ሽታው ደስ እንዲያሰኘኝ በእሳት የሚቀርብልኝን የምግብ ቍርባን የተወሰነውን ጊዜ ጠብቃችሁ አቅርቡልኝ።’ ደግሞም እንዲህ በላቸው፤ ‘በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የምታቀርቡት መሥዋዕት ይህ ነው፤ አንድ ዓመት የሆናቸውንና እንከን የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መደበኛ የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ በየዕለቱ አቅርቡ። አንዱን ጠቦት ጧት ሌላውን ደግሞ ማታ አቅርቡ፤ ከዚህም ጋር ተወቅጦ በተጠለለ በሂን28፥5 አንድ ሊትር ያህል ነው። አንድ አራተኛ የወይራ ዘይት የተለወሰ የኢፍ28፥5 ሁለት ሊትር ያህል ነው። አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን አዘጋጁ። ይህም ሽታው ደስ እንዲያሰኝ በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ ምሥዋዕት ሲሆን፣ በሲና ተራራ የተደነገገ መደበኛ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። ከእያንዳንዱ ጠቦት ጋር አብሮት የሚቀርበውም የመጠጥ ቍርባን ፈልቶ የወጣለት የሂን አንድ አራተኛ መጠጥ ይሆናል፤ የመጠጡንም ቍርባን በተቀደሰው ቦታ ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አፍስሱት። ሁለተኛውንም ጠቦት ጧት ባቀረባችሁት ዐይነት አድርጋችሁ ከእህል ቍርባኑና ከመጠጥ ቍርባኑ ጋር ማታ አቅርቡት፤ ይህም ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

የሰንበት መሥዋዕት

“ ‘በሰንበት ዕለት፣ አንድ ዓመት የሆናቸውንና እንከን የማይገኝባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶች መሥዋዕት ከመጠጥ ቍርባኑና በዘይት ከተለወሰ የኢፍ28፥9 አራት ተኩል ሊትር ያህል ነው። ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ጋር አቅርቡ። ይህም ከመጠጥ ቍርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ በየሰንበቱ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

የየወሩ መሥዋዕት

“ ‘በየወሩ መባቻ እንከን የሌለባቸውን ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ፣ ዓመት የሆናቸውን ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ። ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋር ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ28፥12 ስድስት ተኩል ሊትር ያህል ነው። ሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቀርባል፤ እንደዚሁም ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋር ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ ይህም ለሚቃጠል መሥዋዕት ሲሆን ሽታው ደስ የሚያሰኝና በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። ከእያንዳንዱ ወይፈን ጋር ለመጠጥ ቍርባን የሚሆን የኢን28፥14 ሁለት ሊትር ያህል ነው። ግማሽ የወይን ጠጅ፣ ከአውራው በግ ጋር የኢን28፥14 አንድ ሊትር ያህል ነው። አንድ ሦስተኛ፣ ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር የኢን አንድ አራተኛ የወይን ጠጅ ይቅረብ፤ ይህም በየወሩ መባቻ ዓመቱን ሙሉ የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። ከመጠጥ ቍርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ይቀርባል።

ፋሲካ

28፥16-25 ተጓ ምብ – ዘፀ 12፥14-20ዘሌ 23፥4-8ዘዳ 16፥1-8

“ ‘የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ፋሲካ በዓል ይከበራል። በዚሁ ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል፤ እስከ ሰባትም ቀን ድረስ ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ብሉ። በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባራችሁንም አትሥሩበት። እንከን የሌለባቸው ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርቡ። ከእያንዳንዱም ወይፈን ጋር ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ ልም ዱቄት፣ ከአውራውም በግ ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ ከሰባቱም የበግ ጠቦቶች ከእያንዳንዳቸው ጋር የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አዘጋጁ። በተጨማሪም ማስተስረያ እንዲሆናችሁ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ። እነዚህንም ጧት ጧት በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር አቅርቧቸው። በዚህም ዐይነት ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሆኖ በየዕለቱ ለሰባት ቀን በእሳት ለሚቀርብ መሥዋዕት የምግብ ቍርባን አዘጋጁ፤ ይህም ከመጠጥ ቍርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ሆኖ በተጨማሪ ይቀርባል። በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባርም አትሥሩበት።

የሳምንቱ በዓል

28፥26-31 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥15-22ዘዳ 16፥9-12

“ ‘በየሳምንቱ በሚደረገው በዓል፣ አዲስ የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በምታቀርቡበት በፍሬ በኵራት ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባርም አትሥሩበት። ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸውን ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ አድርጋችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ። ከእያንዳንዱም ወይፈን ጋር ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፉ ሦስት ዐሥረኛ፣ ከአውራው በግ ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቀርባል፤ ከሰባቱም የበግ ጠቦቶች ከእያንዳንዳቸው ጋር የኢፉ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት ይቅረብ። በተጨማሪም ማስተስረያ እንዲሆንላችሁ አንድ ተባዕት ፍየል አቅርቡ። ከእህል ቍርባኑ ጋር በመደበኛነት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በተጨማሪ፣ እነዚህን ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋር አቅርቡ። እንስሳቱም እንከን የሌላቸው መሆናቸውን አረጋግጡ።

Read More of ዘኍል 28

ዘኍል 29:1-11

የመለከት በዓል

29፥1-6 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥23-25

“ ‘በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ሥራም አትሥሩበት፤ ይህም የመለከት ድምፅ የምታሰሙበት ቀናችሁ ነው። እንከን የሌለባቸውን አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ። ከወይፈኑ ጋር ለእህል ቍርባን የሚሆን የኢፍ29፥3 ስድስት ተኩል ሊትር ያህል ነው። ሦስት ዐሥረኛ፣ ከአውራውም በግ ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ፣29፥3 አራት ተኩል ሊትር ያህል ነው። በዘይት የተለወሰ ልም ዱቄት አቅርቡ፤ ከእያንዳንዱም ሰባት የበግ ጠቦት ጋር በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ29፥4 ሁለት ሊትር ያህል ነው። ልም ዱቄት አዘጋጁ። ማስተስረያ እንዲሆናችሁም አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ በተጨማሪ አቅርቡ። እነዚህ እንግዲህ በተደነገገው መሠረት ከእህል ቍርባናቸውና ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋር በየዕለቱና በየወሩ ከሚቀርቡት የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ሌላ ተጨማሪ ሆነው፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሽታቸው ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቀርቡ መሥዋዕቶች ናቸው።

የማስተስረያ ቀን

29፥7-11 ተጓ ምብ – ዘሌ 16፥2-3423፥26-32

“ ‘በዚሁ በሰባተኛው ወር በዐሥረኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ ራሳችሁን አዋርዱ፤29፥7 ወይም ጹሙ ሥራም አትሥሩ። ሁሉም እንከን የሌለባቸው አንድ ወይፈን፣ አንድ አውራ በግና ዓመት የሆናቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ። ከወይፈኑ ጋር ለእህል ቍርባን የሚሆን የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ፣ ከአውራ በጉ ጋር የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ በዘይት የተለወሰ ዱቄት አቅርቡ፤ ከሰባቱ የበግ ጠቦቶችም ከእያንዳንዳቸው ጋር በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ ልም ዱቄት አዘጋጁ። ማስተስረያ እንዲሆንም ለኀጢአት መሥዋዕት ከሚቀርበው እንዲሁም ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋር በመደበኛነት ቀርቦ ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ አንድ ተባዕት ፍየል የኀጢአት መሥዋዕት አድርጋችሁ በተጨማሪ አቅርቡ።

Read More of ዘኍል 29