ነህምያ 9:1-37 NASV

ነህምያ 9:1-37

እስራኤላውያን ኀጢአታቸውን ተናዘዙ

በዚያኑ ወር ሃያ አራተኛ ቀን እስራኤላውያን ጾመው፣ ማቅ ለብሰው፣ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው በአንድነት ተሰበሰቡ። የእስራኤላውያን ዘር የሆኑትም ራሳቸውን ከባዕዳን ሁሉ ለዩ። ቆመውም ኀጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን በደል ተናዘዙ። በያሉበትም ቦታ ቆመው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ሩብ ቀን አነበቡ፤ የቀረውን ሩብ ቀን ደግሞ ንስሓ በመግባትና ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር በመስገድ አሳለፉ። ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ባኒ፣ ቀድምኤል፣ ሰበንያ፣ ቡኒ፣ ሰራብያ፣ ባኒ፣ ከናኒ፣ በመውጫ ደረጃዎች ላይ ቆሙ፤ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅ ጮኹ። ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ቀድምኤል፣ ባኒ፣ አሰበንያ፣ ሰራብያ፣ ሆዲያ፣ ሰበንያና ፈታያ፣ “ተነሥታችሁ ቁሙ፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሚኖረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱ” አሉ።

“ክቡር ስምህ የተመሰገነ ይሁን፤ ከምስጋና ሁሉና ከውዳሴም በላይ ከፍ ከፍ ይበል። አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ። ሰማያትን፣ ከሰማያት በላይ ያሉትን ሰማያትና የከዋክብታቸውን ሰራዊት ሁሉ፣ ምድርንና በላይዋ ያለውን ሁሉ፣ ባሕሮችንና በውስጣቸው ያሉትንም ሁሉ ፈጥረሃል። ለሁሉም ሕይወትን ትሰጣለህ፤ የሰማይ ሰራዊትም ይሰግዱልሃል።

“አብራምን የመረጥኸውና ከከለዳውያን ዑር አውጥተህ አብርሃም የሚል ስም የሰጠኸው አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ። ልቡ ለአንተ የታመነ ሆኖ ስላገኘኸውም፣ የከነዓናውያንን የኬጢያውያንን፣ የአሞራውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የኢያቡሳውያንንና የጌርጌሳውያንን ምድር ለዘሮቹ ለመስጠት ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባህ፤ ጻድቅ ስለ ሆንህም የሰጠኸውን ተስፋ ጠበቅህ።

“አንተ በግብፅ የአባቶቻችንን ሥቃይ አየህ፤ በቀይ ባሕርም9፥9 ዕብራይስጡ፣ ያም ሱፍ ይላል፤ ይኸውም የደንገል ባሕር ማለት ነው። ጩኸታቸውን ሰማህ። ታምራታዊ ምልክቶችንና ድንቆችን በፈርዖንና፣ በሹማምቱ ሁሉ፣ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ላክህ፤ ይህንም ያደረግኸው ግብፃውያን እንዴት በእብሪት እንዳስጨነቋቸው ስላወቅህ ነው። እስከ ዛሬም የሚጠራ ስም ለራስህ እንዲኖርህ አደረግህ። በደረቅ ምድር እንዲሻገሩ ባሕሩን በፊታቸው ከፈልህ፤ ያሳደዷቸውን ግን በኀይለኛ ውሃ ውስጥ እንደሚጣል ድንጋይ ወደ ጥልቁ ውስጥ ወረወርሃቸው። ቀን በደመና ዐምድ፣ በሚሄዱበት መንገድ ታበራላቸውም ዘንድ ሌሊት በእሳት ዐምድ መራሃቸው።

“በሲና ተራራ ላይ ወረድህ፤ ከሰማይም ተናገርሃቸው። ትክክለኛ ደንቦችንና እውነተኛ ሕጎችን፣ መልካም ሥርዐቶችንና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው። የተቀደሰች ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፤ ትእዛዞችን፣ ሥርዐቶችንና ሕጎችን በባሪያህ በሙሴ አማካይነት ሰጠሃቸው። በተራቡ ጊዜ ከሰማይ መና ሰጠሃቸው፤ በተጠሙም ጊዜ ከዐለት ውሃ አፈለቅህላቸው፤ ልትሰጣቸው በተዘረጋች እጅ ወደ ማልህላቸውም ምድር ገብተው እንዲወርሱ አዘዝሃቸው።

“እነርሱና አባቶቻችን ግን ትምክሕተኞችና ዐንገተ ደንዳኖች ሆኑ፤ ትእዛዞችህንም አልፈጸሙም። ለመስማት አልፈለጉም፤ በመካከላቸውም ያደረግሃቸውን ታምራት ማስታወስ አልቻሉም። ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ በዐመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ። አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፣ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣም የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ። ስለዚህ አልተውሃቸውም፤ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አቅልጠው፣ ‘ከግብፅ ያወጣህ አምላክ ይህ ነው’ ባሉና አስጸያፊ የስድብ ቃል በተናገሩ ጊዜ እንኳ አልተለየሃቸውም።

“ከርኅራኄህ ብዛት የተነሣ በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ ቀን የደመናው ዐምድ በመንገዳቸው ላይ መምራቱን፣ ሌሊትም የእሳቱ ዐምድ በሚሄዱበት ላይ ማብራቱን አላቆመም። ያስተምራቸው ዘንድ ቸር መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ መናውን ከአፋቸው አልከለከልህም፤ በተጠሙ ጊዜ ውሃ ሰጠሃቸው። በምድረ በዳ አርባ ዓመት መገብሃቸው፤ ምንም ያጡት አልነበረም፤ ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸውም አላበጠም።

“በሩቅ የሚገኙትን ድንበሮች እንኳ ሳይቀር፣ መንግሥታትንና አሕዛብን ሰጠሃቸው። የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፣ የባሳን ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ። ወንዶች ልጆቻቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛሃቸው፤ አባቶቻቸው ገብተው እንዲወርሱ ወዳዘዝሃቸውም ምድር አገባሃቸው። በምድሪቱ ወንዶች ልጆቻቸው ገቡባት፤ ወረሷትም። በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያን በፊታቸው አንበረከክህ፤ ያሻቸውን ያደርጉባቸው ዘንድ ከነዓናውያንን ከንጉሦቻቸውና ከምድሪቱ ሕዝቦች ጋር በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። የተመሸጉ ከተሞቻቸውንና የሠባውን ምድር ያዙ፤ በመልካም ነገር ሁሉ የተሞሉ ቤቶቻቸውን፣ የተቈፈሩ የውሃ ጕድጓዶቻቸውን፣ የወይን ተክላቸውን፣ የወይራ ዛፎቻቸውንና ስፍር ቍጥር የሌላቸውን የፍሬ ዛፎች ያዙ። እስኪጠግቡ በሉ፤ ወፈሩም፤ በታላቅ በጎነትህም ደስ ተሰኙ።

“ነገር ግን እንቢተኞች ሆኑ፤ ዐመፁብህም፤ ሕግህንም አሽቀንጥረው ጣሉ፤ ወደ አንተ እንዲመለሱ ሲያስጠነቅቋቸው የነበሩት ነቢያትህን ገደሉ፤ አስጸያፊ የስድብ ቃልም ተናገሩ። ስለዚህ ላስጨነቋቸው ጠላቶቻቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። በተጨነቁ ጊዜ ግን ወደ አንተ ጮኹ፤ አንተም ከሰማይ ሰማሃቸው፤ ከርኅራኄህም ብዛት የተነሣ ከጠላቶቻቸው እጅ የሚያድኗቸውን ታዳጊዎች ሰጠሃቸው።

“ነገር ግን ዕረፍት ባገኙ ጊዜ፣ በፊትህ ክፉውን ነገር እንደ ገና ፈጸሙ፤ ከዚያም ይገዟቸው ዘንድ በጠላቶቻቸው እጅ ጣልሃቸው፤ እንደ ገና ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ፣ ከሰማይ ሰማህ፤ በርኅራኄህም በየጊዜው ታደግሃቸው።

“ወደ ሕግህ እንዲመለሱ አስጠነቀቅሃቸው፤ እነርሱ ግን እብሪተኞች ሆኑ። ትእዛዞችህንም አልፈጸሙም፤ አንድ ሰው ቢፈጽማቸው በሕይወት የሚኖርባቸውን ሥርዐቶችህን ተላለፉ። እንቢተኞች ሆነው ጀርባቸውን አዞሩብህ፤ ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ መስማትም አልፈለጉም። ብዙ ዘመን ታገሥሃቸው፤ በነቢያትህ አማካይነት በመንፈስህ አስጠነቀቅሃቸው። ነገር ግን አላደመጡህም፤ ከዚህም የተነሣ ጎረቤቶቻቸው ለሆኑ አሕዛብ አሳልፈህ ሰጠሃቸው። አንተ ግን ቸርና መሓሪ አምላክ ነህና ከምሕረትህ ብዛት የተነሣ፣ ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፤ አልተውሃቸውምም።

“አሁንም አምላካችን ሆይ፤ ቃል ኪዳንህንና ዘላለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ ታላቅ፣ ኀያልና የተፈራህ አምላክ ሆይ፤ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ፣ በነገሥታታችንና በመሪዎቻችን፣ በካህናታችንና በነቢያታችን፣ በአባቶቻችንና በመላው ሕዝብህ ላይ የደረሰው ይህ ሁሉ መከራ በፊትህ እንደ ቀላል ነገር አይታይ። በደረሰብን ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፤ እኛ በደለኞች ነን፤ አንተ ግን ትክክለኛውን አደረግህ። ነገሥታታችን፣ መሪዎቻችን፣ ካህናታችንና አባቶቻችን ሕግህን አልጠበቁም፤ ትእዛዞችህን ወይም የሰጠሃቸውን ማስጠንቀቂያዎች አልሰሙም። በገዛ መንግሥታቸው፣ በሰጠሃቸው ታላቅ በጎነትህና በፊታቸውም ባዘጋጀህላቸው ሰፊና ለም ምድር እንኳ፣ አንተን አላገለገሉም፤ ከክፉ መንገዳቸውም አልተመለሱም።

“እነሆ፤ ዛሬም ባሮች ነን፤ አባቶቻችን ፍሬዋንና በረከቷን እንዲበሉ በሰጠሃቸው ምድር ባሮች ነን። ከኀጢአታችን የተነሣ የተትረፈረፈው መከር ሲሳይ የሆነው በላያችን ላስቀመጥሃቸው ነገሥታት ነው፤ እነርሱም ደስ እንዳሰኛቸው በሰውነታችንና በቀንድ ከብቶቻችን ላይ ያዝዛሉ። እኛም በታላቅ ጭንቀት ውስጥ እንገኛለን።”

Read More of ነህምያ 9