ነህምያ 3:1-32, ነህምያ 4:1-23 NASV

ነህምያ 3:1-32

የቅጥሩ ሠራተኞች

ሊቀ ካህናቱ ኤልያሴብና ወንድሞቹ ካህናት ለሥራ ተነሡ፤ የበጎች በር የተባለውንም እንደ ገና ሠሩ። ቀደሱት፤ መዝጊያዎቹንም በየቦታቸው ላይ አቆሙ። መቶ ማማ እስከሚባለው ግንብና ሐናንኤል ማማ ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ሠርተው ቀደሱት፤ ቀጥሎ ያለውንም የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ እነርሱ ከሠሩት ቀጥሎ ደግሞ የአምሪ ልጅ ዘኩር ሠራ።

የዓሣ በሩን የሃስናአ ልጆች ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ።

የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን የበዓና ልጅ ሳዶቅ መልሶ ሠራ፤ የሚቀጥለውን ክፍል የቴቁሐ ሰዎች መልሰው ሠሩ፤ መኳንንቶቻቸው ግን በተቈጣጣሪ አሠሪዎቻቸው3፥5 ጌቶቻቸው፤ ወይም ገዦቻቸው ሥር ሆነው በሥራው መጠመድ አልፈለጉም።

አሮጌውን3፥6 ወይም የይሻናን በር የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም መልሰው ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ ማያያዣዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የዕድሳቱ ሥራ የተከናወነው በኤፍራጥስ ማዶ በሚገኘው አገረ ገዥ ሥልጣን ሥር ባሉት በገባዖንና በምጽጳ ሰዎች በገባዖናዊው በመልጥያና በሜሮኖታዊው በያዶን ነበር። ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ የሆነው የሐርሃያ ልጅ ዑዝኤል የሚቀጥለውን ክፍል ሠራ፤ ከሽቱ ቀማሚዎች አንዱ የሆነው ሐናንያ ደግሞ ከዚያ ቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ። እነርሱም “ሰፊው ቅጥር” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ኢየሩሳሌምን መልሰው ሠሩ። ከዚያ የሚቀጥለውን ክፍል የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የሆር ልጅ ረፋያ መልሶ ሠራ። የኤርማፍ ልጅ ይዳያ ከቤቱ ፊት ለፊት ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ፤ የአሰበንያ ልጅ ሐጡስ ደግሞ ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ። የካሪም ልጅ መልክያና የፈሐት ሞዓብ ልጅ አሱብ ሌላውን ክፍልና “የእቶን ግንብ” ተብሎ የሚጠራውን መልሰው ሠሩ። የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የአሎኤስ ልጅ ሰሎም ከሴት ልጆቹ ጋር በመሆን ቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ።

“የሸለቆ በር” ተብሎ የሚጠራውን የሐኖንና የዛኖ ነዋሪዎች ዐደሱት፤ መልሰው ሠሩት፤ ከሠሩትም በኋላ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጁ። እንዲሁም “የቈሻሻ መጣያ በር” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን አንድ ሺሕ ክንድ3፥13 450 ሜትር ያህል ነው። ቅጥር መልሰው ሠሩ።

“የቈሻሻ መጣያ በር” ተብሎ የሚጠራው የቤት ሐካሪም አውራጃ ገዥ የሆነው የሬካብ ልጅ መልክያ መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራ በኋላም መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖረ።

የምጽጳ አውራጃ የኮልሖዜ ልጅ ሰሎም “የምንጭ በር” ተብሎ የሚጠራውን መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራም በኋላ ከድኖ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖረ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጀ። “የንጉሥ አትክልት ቦታ” ተብሎ በሚጠራው አጠገብ የሚገኘውን የሼላን መዋኛ ግንብም፣ ከዳዊት ከተማ ጀምሮ ቍልቍል እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ መልሶ ሠራ። ከእርሱም በኋላ የቤት ጹር አውራጃ እኩሌታ ገዥ የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ እስከ ዳዊት መቃብር ትይዩ እስከ ሰው ሠራሹ ኵሬና “የጀግኖች ቤት” ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን መልሶ ሠራ።

ከእርሱ ቀጥሎ ሌዋውያኑ በባኒ ልጅ በሬሁ ሥር ሆነው የዕድሳት ሥራ ሠሩ። ከእርሱ ቀጥሎ የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ ሐሸብያ አውራጃውን መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ደግሞ የሌላው የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ የኤንሐዳድ ልጅ በዋይና በእርሱም ሥር የነበሩት የአገሩ ሰዎች መልሰው ሠሩ። ከእርሱም ቀጥሎ ወደ ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት በሚያወጣውና እስከ ማእዘኑ በሚደርሰው ትይዩ ያለውን ሌላ ክፍል የምጽጳ ገዥ የኢያሱ ልጅ ኤጽር መልሶ ሠራ። ከእርሱም ቀጥሎ የዘባይ ልጅ ባሮክ ከማእዘኑ ጀምሮ እስከ ሊቀ ካህኑ እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ያለውን ሌላ ክፍል በትጋት መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ያለውን ሌላ ክፍል የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት መልሶ ሠራ።

ከእርሱም ቀጥሎ ያለውን ክፍል ከአካባቢው የመጡት ካህናት መልሰው ሠሩ። ከእነርሱ ቀጥሎ ብንያምና አሱብ ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን መልሰው ሠሩ፤ ከእነርሱም ቀጥሎ የሐናንያ ልጅ የመዕሤያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን መልሶ ሠራ። ከእርሱም ቀጥሎ ከዓዛርያስ ቤት ጀምሮ እስከ ማእዘኑና እስከ ማእዘኑም ጫፍ ያለውን ሌላውን ክፍል የኤንሐደድ ልጅ ቢንዊ መልሶ ሠራ፤ የኡዛይ ልጅ ፋላል ከቅጥሩ ማእዘን ትይዩና በዘብ መጠበቂያው አደባባይ አጠገብ ካለው ከላይኛው ቤተ መንግሥት መጠበቂያ ግንብ ጀምሮ ያለውን መልሶ ሠራ። ከእርሱም ቀጥሎ የፋሮስ ልጅ ፈዳያና በዖፌል ኰረብታ ላይ የሚኖሩት የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች “የውሃ በር” ተብሎ ከሚጠራው ትይዩ ጀምሮ በስተ ምሥራቅ እስከሚገኘው ግንብ ድረስ መልሰው ሠሩ። ከእነርሱ ቀጥሎ የቴቁሐ ሰዎች ከታላቁ ግንብ ትይዩ ጀምሮ እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ያለውን ሌላ ክፍል መልሰው ሠሩ።

“የፈረስ በር” ተብሎ ከሚጠራው በላይ ያለውን ደግሞ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየመኖሪያ ቤታቸው ትይዩ ያለውን መልሰው ሠሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን “የምሥራቅ በር” ጠባቂ የሆነው የሴኬንያ ልጅ ሸማያ መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ሌላ ክፍል ደግሞ የሰሌምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛ ልጅ ሐኖን መልሰው ሠሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የበራክያ ልጅ ሜሱላም ከመኖሪያው ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ። ከእርሱ ቀጥሎ ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ መልክያ በመቈጣጠሪያው በር ትይዩ እስከሚገኘው እስከ ቤተ መቅደሱ አገልጋዮችና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት፣ እንዲሁም ከማእዘኑ በላይ እስከሚገኘው ክፍል ያለውን መልሶ ሠራ፤ ከማእዘኑ በላይ ከሚገኘው ክፍል ጀምሮ እስከ በጎች በር ያለውን ደግሞ ወርቅ አንጥረኞቹና ነጋዴዎቹ መልሰው ሠሩ።

Read More of ነህምያ 3

ነህምያ 4:1-23

ቅጥሩ እንዳይሠራ የተደረገ ተቃውሞ

ሰንባላጥ ቅጥሩን እንደምንሠራ በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤ እጅግም ተበሳጨ። በአይሁድም ላይ ተሣለቀ፤ በተባባሪዎቹና በሰማርያ ሰራዊት ፊት፣ “እነዚህ ደካማ አይሁድ ምን እያደረጉ ነው? ቅጥራቸውን መልሰው ሊሠሩ ነውን? መሥዋዕት ሊያቀርቡ ነውን? በአንዲት ጀንበር ሠርተው ሊጨርሱ ነውን? እንደዚያ ተቃጥሎ የፍርስራሽ ክምር የሆነውን ድንጋይ ነፍስ ሊዘሩበት ይችላሉን?” አለ።

በአጠገቡም ቆሞ የነበረው አሞናዊው ጦቢያ፣ “ለመሆኑ የሚገነቡት ምንድን ነው? በድንጋይ የሚሠሩት ቅጥር እኮ ቀበሮ እንኳ ብትወጣበት ሊፈርስ ይችላል” አለ።

አምላካችን ሆይ፤ ተንቀናልና ስማን፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ አውርድባቸው፤ በምርኮ ምድር እንዲበዘበዙ አሳልፈህ ስጣቸው። የፈረሰውን በሚሠሩት ፊት የስድብ ናዳ አውርደዋልና4፥5 ወይም የፈረሰውን በሚሠሩት ፊት እንድትቈጣ አድር ገውሃልና በደላቸውን ይቅር አትበል፤ ኀጢአታቸውንም ከፊትህ አታጥፋው።

ሕዝቡ ከልቡ ስለሚሠራ፣ ቅጥሩን እኩሌታው ድረስ መልሰን ሠራነው።

ሰንባላጥ፣ ጦቢያ፣ ዐረቦች፣ የአሞንና የአሽዶድ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌም ቅጥር ሥራ እየተፋጠነና ክፍት ቦታዎቹም ሁሉ እየተሞሉ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ። መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉ ዘንድ፣ ሽብርንም ይፈጥሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት አደሙ። እኛ ግን ወደ እግዚአብሔር ጸለይን፤ ዛቻቸውንም ለመቋቋም ቀንና ሌሊት የሚጠብቁ ዘቦችን መደብን።

በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሕዝብ፣ “የሠራተኞቹ ጕልበት እየደከመ ነው፤ ከፍርስራሹም ብዛት የተነሣ ቅጥሩን መልሰን ለመሥራት አንችልም” አሉ።

ጠላቶቻችን ደግሞ፣ “በመካከላቸው ገብተን እስክንገድላቸውና ሥራውን እስክናስቆም ድረስ አያውቁም ወይም አያዩም” አሉ።

ከዚያም በአጠገባቸው የሚኖሩ አይሁድ መጥተው፣ “እናንተ የትም ቦታ ብትሆኑ፣ እኛን ማጥቃታቸው አይቀርም!” በማለት ዐሥር ጊዜ ደጋግመው ነገሩን።

ስለዚህ ከቅጥሩ በስተ ኋላ በሚገኙ ግልጽ ቦታዎች ላይ ከሕዝቡ አንዳንዶቹ ሰይፋቸውን፣ ጦራቸውንና ቀስታቸውን እንደ ያዙ በየቤተ ሰባቸው በመመደብ ቦታቸውን እንዲይዙ አደረግሁ። ነገሩን በጥሞና ከተመለከትሁ በኋላ መኳንንቱን፣ ሹማምቱና የቀረውን ሕዝብ፣ “አትፍሯቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፤ ስለ ወንድሞቻችሁ፣ ስለ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ስለ ሚስቶቻችሁና ስለ ቤት ንብረታችሁ ተዋጉ” አልኋቸው።

አድማቸውን እንዳወቅንባቸውና እግዚአብሔርም ዕቅዳቸውን ከንቱ እንዳደረገባቸው ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፣ ሁላችን ወደ ቅጥሩ፣ እያንዳንዳችንም ወደየሥራችን ተመለስን።

ከዚያን ቀን ጀምሮ ከሰዎቼ እኩሌቶቹ ሥራውን ሠሩ፤ የቀሩት ደግሞ ጋሻና ጦር፣ ቀስትና ጥሩር ይዘው ነበር። የጦር አለቆች ከመላው የይሁዳ ሕዝብ በስተ ኋላ ቆሙ፤ እነርሱም ቅጥሩን ይገነቡ ነበር፤ ዕቃ የሚሸከሙት በአንድ እጃቸው ሥራቸውን ሲሠሩ፣ በሌላው እጃቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ነበር፤ እያንዳንዱም ግንበኛ ቅጥሩን በሚሠራበት ጊዜ ሰይፉን በወገቡ ላይ ታጥቆ ነበር፤ መለከት የሚነፋው ሰው ግን ከእኔ አይለይም ነበር።

ከዚያም ለመኳንንቱ፣ ለሹማምቱና ለቀረው ሕዝብ እንዲህ አልሁ፤ “ሥራው ታላቅ ነው፤ ብዙም ነው፤ እርስ በርሳችን በቅጥሩ ላይ እጅግ ተራርቀናል፤ የመለከት ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ፣ ወደ እኛ ተሰብሰቡ። አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል።”

ስለዚህ ጎሕ ሲቀድ ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ እኩሌቶቹ ሰዎች ጦራቸውን እንደ ያዙ ሥራውን ቀጠልን። በዚያን ጊዜ ለሕዝቡ፣ “ሌሊት ዘብ በመጠበቅና ቀን ሥራ በመሥራት እንዲያገለግለን እያንዳንዱ ሰው ከነረዳቱ በኢየሩሳሌም ይቈይ” አልኋቸው። እኔም ሆንሁ ወንድሞቼ፣ ሰዎቼም ሆኑ ከእኔ ጋር ያሉት ጠባቂዎች ልብሳችንን አላወለቅንም፤ ለውሃ እንኳ በምንሄድበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የጦር መሣሪያውን እንደ ያዘ ነበር።4፥23 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም።

Read More of ነህምያ 4