ማቴዎስ 9:14-38 NASV

ማቴዎስ 9:14-38

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያልጾሙበት ምክንያት

9፥14-17 ተጓ ምብ – ማር 2፥18-22ሉቃ 5፥33-39

የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛና ፈሪሳውያን ስንጾም፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ለምን አይጾሙም?” ብለው ጠየቁት።

ኢየሱስም እንዲህ አላችው፤ “ሙሽራው አብሯቸው እያለ ሚዜዎቹ እንዴት ሊያዝኑ ይችላሉ? ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ።

“በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ዕራፊ የሚጥፍ ሰው የለም፤ ይህ ከሆነ አዲሱ ዕራፊ ካረጀው ልብስ ላይ ተቦጭቆ ቀዳዳውን የባሰ ያሰፋዋል። በአሮጌ አቍማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ማንም አይጨምርም፤ ይህ ከሆነ አቍማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቍማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ነገር ግን አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቍማዳ ይጨመራል፤ በዚህ ሁኔታ የወይን ጠጁና አቍማዳው በደኅና ተጠብቀው ይቈያሉ።”

ከሞት የተነሣችው ልጅና ከደም መፍሰስ የተፈወሰችው ሴት

9፥18-26 ተጓ ምብ – ማር 5፥22-43ሉቃ 8፥41-56

ኢየሱስ ሰዎቹን በማናገር ላይ ሳለ፣ አንድ ሹም ከፊቱ ተደፍቶ፣ “ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” አለው። ኢየሱስም ተነሥቶ አብሮት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።

ከዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም እየፈሰሳት ትሠቃይ የነበረች አንዲት ሴት ከኋላው መጥታ የልብሱን ጫፍ ነካች። እርሷም በልቧ፣ “የልብሱን ጫፍ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” ብላ ነበር።

ኢየሱስም ወደ ኋላ ዘወር ብሎ ሴቲቱን አያትና፣ “አይዞሽ፤ ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴቲቱም ወዲያውኑ ተፈወሰች።

ኢየሱስ ወደ ምኵራብ አለቃው ቤት እንደ ደረሰ እንቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፣ “ዞር በሉ፤ ልጂቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው፤ እነርሱ ግን ሣቁበት። ሕዝቡም ከወጣ በኋላ ወደ ውስጥ ገብቶ እጇን ያዘ፤ ልጂቱም ተነሥታ ቆመች። ወሬውም በአካባቢው ሁሉ ተሠራጨ።

የዐይነ ስውሮቹና የድዳው መፈወስ

ኢየሱስም ከዚያ እንደ ሄደ ሁለት ዐይነ ስውሮች፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረን” በማለት እየጮኹ ተከተሉት።

ዐይነ ስውሮቹም ኢየሱስ ወደ ገባበት ቤት ተከትለው ገቡ፤ ኢየሱስም፣ “ዐይናችሁን ላበራላችሁ እንደምችል ታምናላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

እነርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤” ብለው መለሱለት።

ከዚያም ኢየሱስ ዐይናቸውን ዳስሶ፣ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው። ዐይናቸውም በራ፤ ኢየሱስም፣ “ይህን ማንም እንዳያውቅ” ብሎ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው። እነርሱ ግን ወጥተው በአካባቢው ሁሉ ስለ ኢየሱስ አወሩ።

ከዚያም ሲወጡ፣ በጋኔን የተያዘ ድዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ጋኔኑ ከወጣለት በኋላ ድዳው መናገር ጀመረ፤ ሕዝቡም ተደንቀው፣ “እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ምድር ታይቶ አያውቅም” አሉ።

ፈሪሳውያን ግን፣ “አጋንንትን የሚያወጣው፣ በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ።

ሠራተኞች ጥቂቶች ናቸው

ኢየሱስ በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች እየሰበከ፣ እንዲሁም ደዌንና ሕመምን ሁሉ እየፈወሰ በከተሞቹና በመንደሮቹ ዞረ። ሕዝቡም እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ ዐዘነላቸው። ደቀ መዛሙርቱንም እንዲህ አላቸው፤ “መከሩ ብዙ ነው፤ የመከሩ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህ የመከሩ ጌታ፣ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት።”

Read More of ማቴዎስ 9