ማቴዎስ 15:10-39 NASV

ማቴዎስ 15:10-39

ሕዝቡን ወደ እርሱ ቀረብ እንዲሉ አድርጎ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙ፤ አስተውሉም፤ ሰውን የሚያረክሰው ከአፉ የሚወጣው እንጂ ወደ አፉ የሚገባው አይደለም።”

ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው፣ “ፈሪሳውያን ያልኸውን ሰምተው እንደ ተቈጡ ዐወቅህ?” አሉት።

እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ተዉአቸው፣ እነርሱ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውር መሪዎች ናቸው፤ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ተያይዘው ገደል ይገባሉ።”

ጴጥሮስም፣ “ምሳሌውን አስረዳን” አለው።

እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተም እስካሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን? በአፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ ዘልቆ፣ ከዚያም ወደ ውጭ እንደሚወጣ አታውቁምን? ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይመነጫል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው፤ ክፉ ሐሳብ፣ ነፍስ መግደል፣ ማመንዘር፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በሐሰት መመስከርና ስም ማጕደፍ ከልብ ይመነጫሉና። ሰውን የሚያረክሱ እነዚህ ናቸው እንጂ እጅን ሳይታጠቡ መብላት ሰውን አያረክስም።”

የከነዓናዊቷ ሴት እምነት

15፥21-28 ተጓ ምብ – ማር 7፥24-30

ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። አንዲት ከነዓናዊት ሴት ከዚያ አካባቢ በመውጣት ወደ ኢየሱስ መጥታ፣ “ጌታ ሆይ፤ የዳዊት ልጅ፤ ራራልኝ፤ ልጄ በርኩስ መንፈስ ተይዛ በጣም ትሠቃያለች” ብላ ጮኸች።

እርሱ ግን አንድም ቃል አልመለሰላትም፤ በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “እየተከተለችን ትጮኻለችና ብታሰናብታትስ?” ብለው ጠየቁት።

እርሱም፣ “የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ሆነው ወደ ጠፉት በጎች ብቻ ነው” አለ።

ሴትዮዋም እግሩ ላይ ወድቃ፣ “ጌታ ሆይ፤ ርዳኝ” አለች።

እርሱም መልሶ፣ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መወርወር አይገባም” አላት።

እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ ውሾችም እኮ ከጌታቸው ማዕድ የወዳደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለችው።

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ “አንቺ ሴት እምነትሽ ታላቅ ነው! እንደ ፈለግሽው ይሁንልሽ” አላት። ልጇም ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰች።

ኢየሱስ አራት ሺሕ ሰዎች በታምር መገበ

15፥29-31 ተጓ ምብ – ማር 7፥31-37

15፥32-39 ተጓ ምብ – ማር 8፥1-10

15፥32-39 ተጓ ምብ – ማቴ 14፥13-21

ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ በገሊላ ባሕር አጠገብ ወዳለው ስፍራ በመሄድ ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ። ቍጥሩ ብዙ የሆነ ሕዝብም ዐንካሶችን፣ ዐይነ ስውሮችን፣ ሽባዎችን፣ ዲዳዎችን እንዲሁም ሌሎች ብዙዎችን ሕመምተኞች ይዘው ወደ እርሱ በማምጣት በእግሩ ሥር አስቀመጧቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። ሕዝቡም ዲዳው ሲናገር፣ ሽባው ደኅና ሲሆን፣ ዐንካሳው ቀጥ ብሎ ሲሄድ፣ ዐይነ ስውሩም ሲያይ ተመልክተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አመሰገኑ።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፣ “ሕዝቡ ከእኔ ጋር ሦስት ቀን ስለሆናቸውና የሚበሉት ስለሌላቸው ዐዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድ ላይ በራብ ዝለው እንዳይወድቁ ጦማቸውን ልሰድዳቸው አልፈቅድም” አለ።

ደቀ መዛሙርቱም፣ “በዚህ ምንም በሌለበት ምድረ በዳ ይህን ሁሉ ሕዝብ ለማብላት በቂ እንጀራ ከየት እናገኛለን?” አሉት።

ኢየሱስም፣ “ለመሆኑ ስንት እንጀራ አላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

እነርሱም፣ “ሰባት እንጀራና ጥቂት ትንንሽ ዓሣ” አሉት።

እርሱም ሕዝቡን መሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዛቸው፤ ሰባቱን እንጀራና ዓሣውን ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ አከፋፈሉ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም የተረፈውን ቍርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ። የበሉትም ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ አራት ሺሕ ወንዶች ነበሩ። ኢየሱስ ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ፣ በጀልባ ወደ መጌዶል ሄደ።

Read More of ማቴዎስ 15