ማርቆስ 15:33-47 NASV

ማርቆስ 15:33-47

የኢየሱስ መሞት

15፥33-41 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥45-56ሉቃ 23፥44-49

ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፣ “ኤሎሄ፣ ኤሎሄ፣ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው።

በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን ይጣራል” አሉ።

ከዚያም አንድ ሰው ፈጥኖ ሄዶ የሆመጠጠ የወይን ጠጅ በሰፍነግ ነከረ፤ በዘንግም ሰክቶ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት፤ ከዚያም፣ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያወርደው እናያለን” አለ።

ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ።

የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ15፥39 አንዳንድ ቅጆች እንደዚህ ጮኾ የሚለው ሐረግ የላቸውም። ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አለ።

በዚህ ጊዜ ሴቶች ከሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፣ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፣ እንዲሁም ሰሎሜ ነበሩ፤ እነዚህ ሴቶች በገሊላ ሲከተሉትና ሲያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤ ደግሞም አብረውት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች ብዙ ሴቶች ነበሩ።

የኢየሱስ መቀበር

15፥42-47 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥57-61ሉቃ 23፥50-56ዮሐ 19፥38-42

ጊዜው እየመሸ መጥቶ የሰንበት ዋዜማ ይኸውም የመዘጋጀት ቀን ሆነ፤ የተከበረ የሸንጎ አባልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ በድፍረት ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ጲላጦስም እንዲህ በቶሎ መሞቱን ሲሰማ ተደነቀ፤ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ምን ያህል ጊዜ እንደ ሆነ ጠየቀው፤ መሞቱንም ከመቶ አለቃው ካረጋገጠ በኋላ ሥጋውን ለዮሴፍ ሰጠው። ዮሴፍም በፍታ ገዛ፤ ሥጋውንም አውርዶ በበፍታው ከከፈነው በኋላ፣ ከዐለት በተወቀረ መቃብር አኖረው፤ የመቃብሩንም ደጃፍ በድንጋይ ገጠመው። ማርያም መግደላዊትና የዮሳ እናት ማርያም የት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።

Read More of ማርቆስ 15