ኢሳይያስ 60:1-22, ኢሳይያስ 61:1-11, ኢሳይያስ 62:1-12 NASV

ኢሳይያስ 60:1-22

የጽዮን ክብር

“ብርሃንሽ መጥቷልና ተነሺ አብሪ፤

የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻል።

እነሆ፤ ጨለማ ምድርን፣

ድቅድቅ ጨለማም ሕዝቦችን ይሸፍናል፤

ነገር ግን እግዚአብሔር ወጥቶልሻል፤

ክብሩንም ይገልጥልሻል።

ሕዝቦች ወደ ብርሃንሽ፣

ነገሥታትም ወደ ንጋትሽ ጸዳል ይመጣሉ።

“ቀና በዪ፤ ዙሪያሽን ተመልከቺ፤

ሁሉም ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤

ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ፣

ሴቶች ልጆችሽም በዕቅፍ ወደ አንቺ ይመጣሉ።

ከዚያም ታያለሽ፤ ታብረቀርቂያለሽ፤

ልብሽ ይዘልላል፤ በደስታም ይሞላል።

በባሕሮች ያለው ሀብት ወደ አንቺ ይመጣል፤

የነገሥታትም ብልጽግና የአንቺ ይሆናል።

የግመል መንጋ፣

የምድያምና የጌፌር ግልገል ግመሎች

ምድርሽን ይሞላሉ፤

ወርቅና ዕጣን ይዘው፣

የእግዚአብሔርን ምስጋና እያወጁ፣

ሁሉም ከሳባ ይመጣሉ።

የቄዳር የበግ መንጋ ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባል፤

የነባዮት አውራ በጎች ያገለግሉሻል።

እነዚህም በመሠዊያዬ ላይ ተቀባይነት የሚኖራቸው መሥዋዕቶች ይሆናሉ፤

እኔም የክብር መቅደሴን ግርማ አጐናጽፈዋለሁ።

“ርግቦች ወደ ጐጇቸው እንደሚበርሩ፣

እንደ ደመና የሚጓዙ እነዚህ እነማን ናቸው?

በርግጥ ደሴቶች እኔን ተስፋ ያደርጋሉ፤

እርሱ ክብሩን ስላጐናጸፈሽ፣

ለእስራኤል ቅዱስ፣

ለእግዚአብሔር አምላክሽ ክብር፣

ከሩቅ ወንዶች ልጆችሽን፣

ከነብራቸውና ከነወርቃቸው ለማምጣት፣

የተርሴስ መርከቦች60፥9 ወይም፣ የንግድ መርከቦች ቀድመው ይወጣሉ።

“ባዕዳን ቅጥሮችሽን ይሠራሉ፤

ነገሥታቶቻቸው ያገለግሉሻል፤

በቍጣዬ ብመታሽም፣

ርኅራኄዬን በፍቅር አሳይሻለሁ።

በሮችሽ ምንጊዜም የተከፈቱ ይሆናሉ፤

ቀንም ሆነ ሌሊት ከቶ አይዘጉም፤

ይህም ሰዎች የመንግሥታትን ብልጽግና ወደ አንቺ እንዲያመጡ፣

ነገሥታታቸውም በድል ወደ አንቺ እንዲገቡ ነው።

ለአንቺ የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፤

ፈጽሞም ይደመሰሳል።

“የመቅደሴን ቦታ ለማስጌጥ፣

የሊባኖስ ክብር፣

ጥዱ፣ አስታውና ባርሰነቱ በአንድነት ወደ አንቺ ይመጣሉ፤

እግሬ የሚያርፍበትንም ስፍራ አከብራለሁ።

የአስጨናቂዎችሽ ወንዶች ልጆች እየሰገዱ ወደ አንቺ ይመጣሉ፤

የናቁሽም ሁሉ እግርሽ ላይ ይደፋሉ፤

የእግዚአብሔር ከተማ፣

የእስራኤል ቅዱስ ገንዘብ የሆንሽው ጽዮን ብለው ይጠሩሻል።

“የተተውሽና የተጠላሽ፣

ማንም ሰው የማያልፍብሽ ብትሆኝም እንኳ፣

እኔ የዘላለም ትምክሕት፣

የትውልድም ሁሉ ደስታ አደርግሻለሁ።

የመንግሥታትን ወተት ትጠጪያለሽ፤

የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤

ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽ፣

ቤዛሽም እኔ የያዕቆብ ኀያል እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ።

በናስ ፈንታ ወርቅ፣

በብረትም ፈንታ ብር አመጣልሻለሁ።

ሰላምን ገዥሽ፣

ጽድቅንም አለቃሽ አደርጋለሁ።

ከእንግዲህ በምድርሽ ሁከት፣

በጠረፎችሽም ጥፋትና መፈራረስ አይሰማም፤

ነገር ግን ቅጥሮችሽን ድነት፣

በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያቸዋለሽ።

ከእንግዲህ በቀን የፀሓይ ብርሃን አያስፈልግሽም፤

በሌሊትም የጨረቃ ብርሃን አያበራልሽም፤

እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃን፣

አምላክሽም ክብርሽ ይሆናልና።

ፀሓይሽ ከእንግዲህ አትጠልቅም፤

ጨረቃሽም ብርሃን መስጠቷን አታቋርጥም፤

እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ ይሆናል፤

የሐዘንሽም ቀን ያከትማል።

ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤

ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ፤

ለክብሬ መግለጫ ይሆኑ ዘንድ፣

የእጆቼ ሥራ፣

እኔ የተከልኋቸው ቍጥቋጦች ናቸው።

ከአንቺ ታናሽ የሆነው ሺሕ፣

ከሁሉም የመጨረሻው ታናሽ ኀያል መንግሥት ይሆናል፤

እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤

ጊዜውም ሲደርስ ይህን በፍጥነት አደርጋለሁ።”

Read More of ኢሳይያስ 60

ኢሳይያስ 61:1-11

የተወደደው የእግዚአብሔር ዓመት

የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤

ለድኾች የምሥራች እንድሰብክ፣

እግዚአብሔር ቀብቶኛል።

ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣

ለምርኮኞች ነጻነትን፣

ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ61፥1 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን፣ ዕውራንን ከጨለማ አወጣቸው ዘንድ ይላል። ልኮኛል፤

የተወደደውን የእግዚአብሔርን ዓመት፣

የአምላካችንንም የበቀል ቀን እንዳውጅ፣

የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል፤

በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣

በዐመድ ፈንታ፣

የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣

በልቅሶ ፈንታ፣

የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣

በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣

የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤

እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣

እግዚአብሔር የተከላቸው፣

የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።

የጥንት ፍርስራሾችን መልሰው ይሠራሉ፤

በቀድሞ ጊዜ የወደሙትን መልሰው ያቆማሉ፤

ከብዙ ትውልድ በፊት የወደሙትን

ፍርስራሽ ከተሞች እንደ ገና ይሠራሉ።

መጻተኞች የበግ መንጎቻችሁን ያግዳሉ፤

ባዕዳን በዕርሻችሁና በወይን ተክል ቦታችሁ ላይ ይሠሩላችኋል።

እናንተም የእግዚአብሔር ካህናት ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤

የአምላካችን ባሮች ትባላላችሁ፤

የመንግሥታትን ሀብት ትመገባላችሁ፤

በብልጽግናቸውም ትኰራላችሁ።

ሕዝቤ በኀፍረታቸው ፈንታ፣

ዕጥፍ ይቀበላሉ፤

በውርደታቸው ፈንታ፣

በርስታቸው ደስ ይላቸዋል፤

የምድራቸውንም ዕጥፍ ርስት ይወርሳሉ፤

ዘላለማዊ ደስታም የእነርሱ ይሆናል።

“እኔ እግዚአብሔር ፍትሕን ስለምወድድ፣

ዝርፊያንና በደልን እጠላለሁ፤

በታማኝነቴም የሚገባቸውን እሰጣቸዋለሁ፤

ከእነርሱም ጋር የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።

ዘሮቻቸው በመንግሥታት፣

ልጆቻቸውም በሕዝቦች ዘንድ የታወቁ ይሆናሉ፤

የሚያዩአቸውም ሁሉ፣

እግዚአብሔር የባረካቸው ሕዝብ እንደ ሆኑ ያውቃሉ።”

በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፤

ነፍሴ በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች፤

ሙሽራ ራሱን እንደሚያሳምር፣

ሙሽራዪቱም በዕንቈቿ እንደምታጌጥ፣

የድነትን ልብስ አልብሶኛል፤

የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።

ምድር ቡቃያ እንደምታበቅል፣

የተክል ቦታ ችግኝ እንደሚያፈላ፣

ጌታ እግዚአብሔርም በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣

ጽድቅንና ምስጋናን ያበቅላል።

Read More of ኢሳይያስ 61

ኢሳይያስ 62:1-12

አዲሱ የጽዮን ስም

ጽድቋ እንደ ማለዳ ወጋገን እስኪፈነጥቅ፣

ድነቷ እንደሚያንጸባርቅ ፋና እስኪታይ፣

ስለ ጽዮን ዝም አልልም፤

ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም።

መንግሥታት ጽድቅሽን፣

ነገሥታት ክብርሽን ያያሉ፤

የእግዚአብሔር አፍ በሚያወጣልሽ፣

በአዲስ ስም ትጠሪያለሽ።

በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፣

በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።

ከእንግዲህ፣ “የተተወች” ብለው አይጠሩሽም፤

ምድርሽም፣ “የተፈታች” አትባልም፤

ነገር ግን፣ “ደስታዬ በእርሷ” ትባያለሽ፤

ምድርሽም፣ “ባለ ባል” ትባላለች፤

እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤

ምድርሽም ባለ ባል ትሆናለች።

ጕልማሳ ድንግሊቱን እንደሚያገባ፣

ልጆችሽ62፥5 ወይም፣ ግንበኞችሽ እንዲሁ ያገቡሻል፤

ሙሽራ በሙሽራዪቱ ደስ እንደሚለው፣

አምላክሽም በአንቺ ደስ ይለዋል።

ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ዘብ ጠባቂዎችን በቅጥሮችሽ ላይ አቁሜአለሁ፤

ቀንም ሆነ ሌሊት ፈጽሞ አይታክቱም።

እናንት ወደ እግዚአብሔር አቤት፣ አቤት የምትሉ፤

ፈጽሞ አትረፉ፤

ኢየሩሳሌምን እስኪያጸናት፣

የምድርም ምስጋና እስኪያደርጋት ዕረፍት አትስጡት።

እግዚአብሔር በቀኝ እጁ፣

በኀያል ክንዱም እንዲህ ሲል ምሏል፤

“ከእንግዲህ እህልሽን፣

ለጠላቶችሽ መብል እንዲሆን አልሰጥም፤

ከእንግዲህ የደከምሽበትን፣

አዲስ የወይን ጠጅ ባዕዳን አይጠጡትም።

ነገር ግን መከሩን የሰበሰቡ ይበሉታል፤

እግዚአብሔርንም ያመሰግናሉ፤

የወይኑን ፍሬ የለቀሙም በመቅደሴ

አደባባዮች ይጠጡታል።”

ዕለፉ፤ በበሮቹ በኩል ዕለፉ፤

ለሕዝቡ መንገድ አዘጋጁ፤

አስተካክሉ፤ ጐዳናውን አስተካክሉ፤

ድንጋዩን አስወግዱ፤

ለመንግሥታትም ምልክት አሳዩ።

እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ፣

እንዲህ ሲል ዐውጇል፤

“ለጽዮን ሴት ልጅ፣

‘እነሆ፤ አዳኝሽ መጥቷል፤

ዋጋሽ በእጁ አለ፤

ዕድል ፈንታሽም ከእርሱ ጋር ነው’ በሏት።”

እነርሱም ቅዱስ ሕዝብ፣

እግዚአብሔር የተቤዣቸው ተብለው ይጠራሉ፤

አንቺም የምትፈለግ፣

ከእንግዲህም የማትተው ከተማ ትባያለሽ።

Read More of ኢሳይያስ 62