ሆሴዕ 8:1-14, ሆሴዕ 9:1-17 NASV

ሆሴዕ 8:1-14

እስራኤል ዐውሎ ነፋስን ታጭዳለች

“መለከትን በአፍህ ላይ አድርግ!

ሕዝቡ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና፣

በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና፣

ንስር በእግዚአብሔር ቤት ላይ ነው፤

እስራኤልም፣ ‘አምላካችን ሆይ፤ እኛ እናውቅሃለን’ እያሉ፣

ወደ እኔ ይጮኻሉ።

ነገር ግን እስራኤል በጎ የሆነውን ነገር ናቁ፤

ጠላትም ያሳድዳቸዋል።

ያለ እኔ ፈቃድ ነገሥታትን አነገሡ፤

እኔንም ሳይጠይቁ አለቆችን መረጡ፤

በብራቸውና በወርቃቸው፣

ለገዛ ጥፋታቸው፣

ጣዖታትን ለራሳቸው ሠሩ።

ሰማርያ ሆይ፤ የጥጃ ጣዖትሽን ጣዪ፤

ቍጣዬ በእነርሱ ላይ ነድዷል፤

የማይነጹት እስከ መቼ ነው?

ይህም በእስራኤል ሆነ!

ባለ እጅ የሠራው ይህ ጥጃ፣ አምላክ

አይደለም፤

ያ የሰማርያ ጥጃ፣

ተሰባብሮ ይደቅቃል።

“ነፋስን ይዘራሉ፤

ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ፤

አገዳው ዛላ የለውም፤

ዱቄትም አይገኝበትም፤

እህል አፍርቶ ቢገኝም፣

ባዕዳን ይበሉታል።

እስራኤል ተውጠዋል፤

በአሕዛብም መካከል፣

ዋጋ እንደሌለው ዕቃ ሆነዋል።

ለብቻው እንደሚባዝን የዱር አህያ፣

ወደ አሦር ሄደዋልና፤

ኤፍሬም በእጅ መንሻ ወዳጅ አበጀ።

በአሕዛብ መካከል ራሳቸውን ቢሸጡም፣

እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፤

በኀያል ንጉሥ ጭቈና ሥር፣

እየመነመኑ ይሄዳሉ።

“ኤፍሬም ለኀጢአት ማስተስረያ ብዙ መሠዊያዎችን ቢሠራም፣

እነርሱ የኀጢአት መሥሪያ መሠዊያዎች ሆነውበታል።

በሕጌ ውስጥ ያለውን ብዙውን ነገር ጻፍሁላቸው፤

እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጠሩት።

ለእኔ የሚገባውን መሥዋዕት ያቀርባሉ፤

ሥጋውንም ይበላሉ፤

እግዚአብሔር ግን በእነርሱ አልተደሰተም፤

ስለዚህ ክፋታቸውን ያስታውሳል፤

ኀጢአታቸውን ይቀጣል፤

ወደ ግብፅም ይመለሳሉ።

እስራኤል ፈጣሪውን ረሳ፤

ቤተ መንግሥቶችንም ሠራ፤

ይሁዳም የተመሸጉ ከተሞችን አበዛ፤

እኔ ግን በከተሞቻቸው ላይ እሳትን እለቃለሁ፤

ምሽጎቻቸውንም ይበላል።”

Read More of ሆሴዕ 8

ሆሴዕ 9:1-17

በእስራኤል ላይ የሚደርሰው ቅጣት

እስራኤል ሆይ፤ ደስ አይበልሽ፤

እንደ ሌሎችም ሕዝቦች ሐሤት አታድርጊ፤

ለአምላክሽ ታማኝ አልሆንሽምና፤

በየእህል ዐውድማውም ላይ፣

ለጋለሞታ የሚከፈለውን ዋጋ ወድደሻል።

የእህል ዐውድማዎችና የወይን መጭመቂያዎች ሕዝቡን አይመግቡም፤

አዲሱም የወይን ጠጅ ይጐድልባቸዋል።

በእግዚአብሔር ምድር አይቀመጡም፤

ኤፍሬም ወደ ግብፅ ይመለሳል፤

የረከሰውንም ምግብ9፥3 በሥርዐቱ መሠረት ያልነጻ ማለት ነው በአሦር ይበላል።

የወይን ጠጅን ቍርባን ለእግዚአብሔር አያፈስሱም፤

መሥዋዕታቸውም ደስ አያሰኘውም፤

እንዲህ ዐይነቱ መሥዋዕት ለእነርሱ የሐዘንተኞች እንጀራ ይሆንባቸዋል፤

የሚበሉትም ሁሉ ይረክሳሉ።

ይህ ምግብ ለገዛ ራሳቸው ይሆናል፤

ወደ እግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ አይገባም።

በእግዚአብሔር የበዓል ቀናት፣

በዓመት በዓሎቻችሁም ቀን ምን ታደርጋላችሁ?

ከጥፋት ቢያመልጡም እንኳ፣

ግብፅ ትሰበስባቸዋለች፤

ሜምፎስም ትቀብራቸዋለች።

የብር ሀብታቸውን ዳዋ ያለብሰዋል፤

ድንኳኖቻቸውንም እሾኽ ይወርሳቸዋል።

የቅጣት ቀን መጥቷል፤

የፍርድም ቀን ቀርቧል፤

እስራኤልም ይህን ይወቅ!

ኀጢአታችሁ ብዙ፣

ጠላትነታችሁም ታላቅ ስለሆነ፣

ነቢዩ እንደ ሞኝ፣

መንፈሳዊውም ሰው እንደ እብድ ተቈጥሯል።

ነቢዩ ከአምላኬ ጋር ሆኖ፣

የኤፍሬም ጠባቂ ነው፤9፥8 ወይም ነቢዩ የኤፍሬም ጠባቂ ነው፤ የአምላኬ ሕዝብ…

ዳሩ ግን በመንገዱ ሁሉ ወጥመድ፣

በአምላኩም ቤት ጠላትነት ይጠብቀዋል።

በጊብዓ እንደ ነበረው፣

በርኩሰት ውስጥ ተዘፍቀዋል፤

እግዚአብሔር ክፋታቸውን ያስባል፤

ስለ ኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል።

“እስራኤልን ማግኘቴ፣

የወይንን ፍሬ በምድረ በዳ የማግኘት ያህል ነበር፤

አባቶቻችሁንም ማየቴ፣

የመጀመሪያውን የበለስ ፍሬ የማየት ያህል ነበር፤

ወደ ብዔልፌጎር በመጡ ጊዜ ግን፣

ለዚያ አሳፋሪ ጣዖት ራሳቸውን ለዩ፤

እንደ ወደዱትም ጣዖት የረከሱ ሆኑ።

የኤፍሬም ክብር እንደ ወፍ በርሮ ይጠፋል፤

መውለድ፣ ማርገዝና መፅነስ የለም።

ልጆችን ቢያሳድጉ እንኳ፣

ልጅ አልባ እስኪሆኑ ድረስ እነጥቃቸዋለሁ፤

ፊቴን ከእነርሱ በመለስሁ ጊዜ፣

ወዮ ለእነርሱ!

ኤፍሬምን እንደ ጢሮስ፣

በመልካም ስፍራ ተተክሎ አየሁት፤

አሁን ግን ኤፍሬም ልጆቹን፣

ለነፍሰ ገዳዮች አሳልፎ ይሰጣል።”

እግዚአብሔር ሆይ፤ ስጣቸው፤

ምን ትሰጣቸዋለህ?

የሚጨነግፉ ማሕፀኖችን፣

የደረቁ ጡቶችን ስጣቸው።

“በጌልገላ ካደረጉት ክፋታቸው ሁሉ የተነሣ፣

እኔ በዚያ ጠላኋቸው፤

ስለ ሠሩት ኀጢአት፣

ከቤቴ አሳድዳቸዋለሁ፤

ከእንግዲህም አልወድዳቸውም፤

መሪዎቻቸው ሁሉ ዐመፀኞች ናቸው።

ኤፍሬም ተመታ፤

ሥራቸው ደረቀ፤

ፍሬም አያፈሩም፤

ልጆች ቢወልዱም እንኳ፣

ተንከባክበው ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን እገድላለሁ።”

ባለመታዘዛቸው ምክንያት፣

አምላኬ ይጥላቸዋል፤

በአሕዛብም መካከል ተንከራታች ይሆናሉ።

Read More of ሆሴዕ 9