ሕዝቅኤል 13:1-23, ሕዝቅኤል 14:1-23, ሕዝቅኤል 15:1-8 NASV

ሕዝቅኤል 13:1-23

የሐሰተኛ ነቢያት መወገዝ

የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት በሚናገሩት በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፤ ከገዛ ራሳቸው ትንቢት የሚናገሩትን እንዲህ በላቸው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አንዳች ነገር ሳያዩ የራሳቸውን መንፈስ ለሚከተሉ ሞኞች13፥3 ወይም ክፉዎች ነቢያት ወዮላቸው! እስራኤል ሆይ፤ ነቢያትሽ በፍርስራሽ መካከል እንደሚኖሩ ቀበሮዎች ናቸው። በእግዚአብሔር ቀን በሚሆነው ጦርነት ጸንቶ መቆም እንዲችል፣ የተሰነጠቀውን ቅጥር ለእስራኤል ቤት ለመጠገን ወደዚያ አልወጣችሁም። ራእያቸው ሐሰት፣ ትንቢታቸው ውሸት ነው፤ እግዚአብሔር ሳይልካቸው፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ይላሉ፤ ይህም ሆኖ የተናገሩት ይፈጸማል ብለው ይጠብቃሉ። እኔ ሳልናገር፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ስትሉ ሐሰተኛ ራእይ ማየታችሁ፣ ውሸተኛስ ትንቢት መናገራችሁ አይደለምን?

“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቃላችሁ ሐሰት፣ ራእያችሁም ውሸት ስለሆነ እኔ በእናንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔርእጄ የሐሰት ራእይ በሚያዩና በሚያሟርቱ ነቢያት ላይ ተነሥቷል። የሕዝቤ ጉባኤ ተካፋይ አይሆኑም፤ በእስራኤል ቤት መዝገብ አይጻፉም፤ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም። በዚያ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።”

“ ‘ሰላም ሳይኖር፣ “ሰላም አለ” እያሉ ሕዝቤን ያስታሉ፤ ሕዝቡ ካብ ሲሠራ እነርሱ በኖራ ይለስናሉ፤ ስለዚህ በኖራ ለሚለስኑት ካቡ እንደሚወድቅ ንገራቸው። ዶፍ ይወርዳል፤ ታላቅ የበረዶ ድንጋይ እሰድዳለሁ፤ ዐውሎ ነፋስም ይነሣል። እነሆ ካቡ ሲፈርስ ሕዝቡ “የለሰናችሁበት ኖራው ወዴት ሄደ?” ብለው አይጠይቋችሁምን?

“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመዓቴ ዐውሎ ነፋስ እሰድዳለሁ፣ በቍጣዬ የበረዶ ድንጋይ እልካለሁ፤ ዶፍም ከታላቅ ጥፋት ጋር ይወርዳል። በኖራ የለሰናችሁትን ካብ አፈርሳለሁ፤ መሠረቱም ተገልጦ እስኪታይ ድረስ ከምድር ጋር አደባልቀዋለሁ። ቅጥሩ13፥14 ወይም ከተማው በሚወድቅበት ጊዜ፣ እናንተም በውስጡ ታልቃላችሁ። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። መዓቴንም በቅጥሩና ኖራ በለሰኑት ሰዎች ላይ እሰድዳለሁ፤ እናንተንም እንዲህ እላችኋለሁ፤ “ቅጥሩና ቅጥሩን በኖራ የለሰኑት የሉም፤ ኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገሩላትና ሰላም ሳይኖር የሰላም ራእይ ያዩላት የእስራኤል ነቢያት ጠፍተዋል”፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

“አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፤ ከራሳቸው አመንጭተው ትንቢት ወደሚናገሩ ወደ ሕዝብህ ሴቶች ልጆች ፊትህን መልስ፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሕዝብን ነፍስ ለማጥመድ፣ ለአስማታቸው ለእጃቸው አንጓ ሁሉ አሸንክታብ ለሚያሰፉና፣ የተለያየ መጠን ያለውን የራስ መሸፈኛ ለሚያበጁ ሴቶች ወዮላቸው! በውኑ የሕዝቤን ነፍስ እያጠመዳችሁ የራሳችሁን ነፍስ ታድናላችሁን? ዕፍኝ ለማይሞላ ገብስና ለቍራሽ እንጀራ ስትሉ ሐሰትን የሚያደምጥ ሕዝቤን እየዋሻችሁ መሞት የማይገባውን በመግደል፣ መኖር የማይገባውንም በማትረፍ በሕዝቤ መካከል አርክሳችሁኛል።”

“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ የሕዝብን ነፍስ እንደ ወፍ በምታጠምዱበት አሸንክታብ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ከክንዳችሁ ላይ እቀዳድደዋለሁ፤ እንደ ወፍ የምታጠምዱትንም ሕዝብ ነጻ አወጣዋለሁ። መሸፈኛችሁን ቀድጄ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ በቍጥጥራችሁ ሥር አይሆኑም፤ በዚያ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። እኔ ያላሳዘንሁትን ጻድቅ በውሸት ስላሳዘናችሁ፣ ኀጢአተኛም ከክፉ መንገዱ ተመልሶ ሕይወቱን እንዳያድን በኀጢአቱ ስላበረታታችሁት፣ ከእንግዲህ የሐሰት ራእይ አታዩም፣ ሟርትም አታሟርቱም፤ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።” ’ ”

Read More of ሕዝቅኤል 13

ሕዝቅኤል 14:1-23

ባዕድ አምልኮ ተከታዮች መወገዛቸው

ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል፤ ክፋታቸውን እንደ ማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፤ ታዲያ ከእኔ እንዳች ነገር እንዲጠይቁ ልፍቀድላቸውን? ስለዚህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ማንኛውም እስራኤላዊ ጣዖትን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ አድርጎ በፊቱ በማስቀመጥ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖቱ ብዛት እመልስለታለሁ። በጣዖቶቻቸው ምክንያት ከእኔ የተለዩትን የእስራኤልን ቤት ሁሉ ልብ ወደ ራሴ ለመመለስ ይህን አደርጋለሁ።’

“ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ንስሓ ግቡ ከጣዖቶቻችሁ ተመለሱ፤ ጸያፍ ተግባራችሁንም ሁሉ ተዉ።”

“ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ራሱን ከእኔ በመለየት ጣዖቶችን በልቡ አኑሮ፣ ክፋቱንም የማሰናከያ ድንጋይ በማድረግ በፊቱ አስቀምጦ ከእኔ ለመጠየቅ ወደ ነቢይ ቢመጣ፣ እኔ ራሴ እግዚአብሔር እመልስለታለሁ። ፊቴን በክፋት ወደዚያ ሰው እመልሳለሁ፤ መቀጣጫና መተረቻ አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

“ ‘ነቢዩ ትንቢት ይናገር ዘንድ ቢታለል፣ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ክንዴን በእርሱ ላይ አነሣለሁ፤ ከሕዝቤ ከእስራኤል መካከልም አጠፋዋለሁ። በደላቸው በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ነቢዩም እርሱን ሊጠይቀው ከመጣው ሰው ጋር እኩል በደለኛ ይሆናል። ከእንግዲህ የእስራኤል ሕዝብ መንገድ ስቶ ከእኔ አይለይም፤ ተመልሶም በኀጢአቱ ሁሉ ራሱን አያረክስም። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

የማያመልጡት ፍርድ

የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ አገር በእኔ ባለመታመን ቢበድለኝና እኔም እጄን በላዩ ዘርግቼ የምግብ ምንጩን ባደርቅ፣ ራብንም አምጥቼበት ሰውንና እንስሳቱን ብገድል፣ ኖኅ፣ ዳንኤልና14፥14 የዕብራይስጡን ቃል አጻጻፍ ስንመለከት ነቢዩን ዳንኤልን ሳይሆን፣ ተመሳሳይ ስም ያለውን ሌላ ሰው የሚያመለክት ይመስላል ኢዮብ እነዚህ ሦስቱ በዚያ ቢኖሩ እንኳ፣ በጽድቃቸው የሚያድኑት ራሳቸውን ብቻ ነው፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር

“የዱር አራዊትንም በአገሪቱ ላይ ሰድጄ፣ አገሪቱን ሕፃናት አልባ ቢያደርጓትና ከአራዊቱም የተነሣ ምድሪቱ ሰው እስከማያልፍባት ባድማ ብትሆን፣ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ!’ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እነዚህ ሦስቱ ሰዎች ቢኖሩባት እንኳ፣ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን ማዳን አይችሉም፤ እነርሱ ብቻ ይድናሉ፤ ምድሪቱ ግን ባድማ ትሆናለች።

“ሰይፍን በአገሪቱ ላይ አምጥቼ፣ ‘ሰይፍ በዚህ ምድር ይለፍ’ ብል፣ ሰውንና እንስሳን ባጠፋ፣ በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ እነዚህ ሦስት ሰዎች ቢኖሩባትም እንኳ ራሳቸው ብቻ ይድናሉ እንጂ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን ማዳን አይችሉም።

“ቸነፈርንም በምድሪቱ ላይ ብሰድድና ደም በማፍሰስ መዓቴን አውርጄ ሰውንና እንስሳን ባጠፋ፣ በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ ቢኖሩባትም እንኳ፣ በጽድቃቸው ራሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችን ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም።

“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ሰውንና እንስሳቱን ለማጥፋት አራቱን አስፈሪ ፍርዶቼን፦ ሰይፍን፣ ራብን፣ የዱር አራዊትንና ቸነፈርን በኢየሩሳሌም ላይ በማመጣበት ጊዜ ምንኛ የከፋ ይሆን! ነገር ግን ከዚያ ወጥተው የሚተርፉ ወንዶችና ሴቶች ልጆች አሉ፤ እነርሱም ወደ እናንተ ይመጣሉ፤ እናንተም አካሄዳቸውንና ተግባራቸውን በምታዩበት ጊዜ፣ በኢየሩሳሌም ላይ ስላመጣሁት መከራ፣ ስላደረስሁባትም አስከፊ ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ። አካሄዳቸውንና ተግባራቸውን በምታዩበት ጊዜ፣ ትጽናናላችሁ፤ አንዳች ነገር በከንቱ እንዳላደረገሁ ትረዳላችሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

Read More of ሕዝቅኤል 14

ሕዝቅኤል 15:1-8

የማይረባው የወይን ግንድ

የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የወይን ግንድ በዱር ካሉት ዛፎች ሁሉ ቅርንጫፍ የሚሻለው በምንድን ነው? የሚጠቅም ነገር ለመሥራት ከግንዱ አንዳች ተወስዶ ያውቃልን? ዕቃ የሚንጠለጠልበትስ ኵላብ ከእርሱ ይበጃልን? እንዲነድድ እሳት ላይ ከተጣለ በኋላ፣ እሳቱ ጫፍና ጫፉን አቃጥሎ፣ መኻሉን ከለበለበው፣ ለአንዳች ነገር ይጠቅማልን? እንግዲህ ደኅና ሆኖ ሳለ ለምንም ነገር ካልጠቀመ፣ እሳት ካቃጠለውና ከለበለበው በኋላ ረብ የለሽነቱ የቱን ያህል የባሰ ይሆን!

“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከዱር ዛፎች መካከል የወይን ግንድ እንዲነድድ ለእሳት አሳልፌ እንደ ሰጠሁ፣ እንዲሁ የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች አሳልፌ እሰጣለሁ። ፊቴን በክፋት ወደ እነርሱ እመልሳለሁ፤ ከእሳት ቢያመልጡም፣ ገና እሳት ይበላቸዋል። ፊቴን በክፋት ወደ እነርሱ በመለስሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። ታማኝ ካለመሆናችሁ የተነሣ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

Read More of ሕዝቅኤል 15