ሐዋርያት ሥራ 16:1-15 NASV

ሐዋርያት ሥራ 16:1-15

ጢሞቴዎስ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተሰማራ

ጳውሎስ ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራን ደረሰ። በዚያም እናቱ አይሁዳዊት ሆና በጌታ ያመነች፣ አባቱ ግን የግሪክ ሰው የሆነ፣ ጢሞቴዎስ የተባለ አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ። እርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን በነበሩት ወንድሞች ዘንድ መልካም ምስክርነት ነበረው። ጳውሎስም ይህ ሰው ከእርሱ ጋር እንዲሄድ ፈለገ፤ ስለዚህ በዚያ አካባቢ በነበሩ አይሁድ ምክንያት ይዞ ገረዘው፤ እነዚህ አይሁድ በሙሉ የጢሞቴዎስ አባት የግሪክ ሰው እንደ ሆነ ያውቁ ነበርና። እነርሱም ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው በሚያልፉበት ጊዜ፣ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም ያሳለፉትን ውሳኔ ተቀብለው እንዲጠብቁ ለምእመናኑ ይሰጡ ነበር። አብያተ ክርስቲያናትም በእምነት እየበረቱና ዕለት ዕለትም በቍጥር እየጨመሩ ይሄዱ ነበር።

ጳውሎስ ስለ መቄዶንያው ሰው ያየው ራእይ

ጳውሎስና ባልደረቦቹ ቃሉን በእስያ እንዳይሰብኩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው፣ በፍርግያና በገላትያ አገር ዐልፈው ሄዱ። ወደ ሚስያም በተቃረቡ ጊዜ፣ ወደ ቢታኒያ ሊገቡ ሞከሩ፤ ነገር ግን የኢየሱስ መንፈስ አልፈቀደላቸውም። ስለዚህ በሚስያ በኩል አድርገው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ፣ “ወደ መቄዶንያ ተሻግረህ ርዳን” ብሎ ሲለምነው አየ። ጳውሎስ ይህን ራእይ ካየ በኋላ፣ እግዚአብሔር ወንጌልን እንድንሰብክላቸው ጠርቶናል ብለን በመወሰን ወዲያው ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ፈለግን።

ልድያ በፊልጵስዩስ በጌታ አመነች

ከጢሮአዳ በመርከብ ተነሥተን በቀጥታ ተጕዘን ወደ ሳሞትራቄ መጣን፤ በማግስቱም ጕዟችንን ወደ ናጱሌ ቀጠልን፤ ከዚያም የሮማውያን ቅኝና የአካባቢው የመቄዶንያ ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ፊልጵስዩስ ገባን፤ በዚያም አያሌ ቀን ተቀመጥን።

በሰንበት ቀንም፣ የጸሎት ስፍራ በመፈለግ፣ ከከተማዪቱ በር ወጥተን ወደ አንድ ወንዝ ወረድን፤ በዚያም ተቀምጠን ተሰብስበው ለነበሩት ሴቶች መናገር ጀመርን። ከሚያዳምጡትም ሴቶች መካከል ልድያ የምትባል አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም እግዚአብሔርን የምታመልክና ከትያጥሮን ከተማ የመጣች የቀይ ሐር ነጋዴ ነበረች። ጌታም፣ ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል ትሰማ ዘንድ ልቧን ከፈተላት። እርሷና ቤተ ሰዎቿ ከተጠመቁ በኋላም፣ “በጌታ ማመኔን በርግጥ ከተረዳችሁልኝ ወደ ቤቴ መጥታችሁ ጥቂት ተቀመጡ” በማለት አጥብቃ ለመነችን።

Read More of ሐዋርያት ሥራ 16