1 ሳሙኤል 14:24-52, 1 ሳሙኤል 15:1-35 NASV

1 ሳሙኤል 14:24-52

ዮናታን ማር በላ

ሳኦል፣ “ዛሬ ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት እስከ ማታ ድረስ እህል የሚበላ ሰው የተረገመ ይሁን” ብሎ ሕዝቡን አምሎ ስለ ነበር፣ በዚያች ዕለት የእስራኤል ሰዎች ተጨንቀው ዋሉ፤ ስለዚህ ከሕዝቡ አንድም እህል የቀመሰ አልነበረም።

ሰራዊቱ14፥25 ወይም አሁን የምድሩ ነዋሪዎች በሙሉ ሁሉ ወደ ጫካ ሲገባ፣ ማር በመሬቱ ላይ ይታይ ነበር። ሕዝቡ ወደ ጫካው በገባ ጊዜ፣ የማሩ ወለላ እየተንጠባጠበ መውረዱን አየ፤ ሆኖም መሐላውን ፈርቶ ስለ ነበር፣ እጁን ወደ አፉ የዘረጋ ማንም አልነበረም። ነገር ግን ዮናታን አባቱ ሕዝቡን በመሐላ ማሰሩን አልሰማም ነበር። ስለዚህ በእጁ የያዘውን ዘንግ ጫፍ በማሩ ወለላ ውስጥ በማስገባት እጁን ወደ አፉ አደረገ፤ ዐይኑም በራ። ከዚያም አንዱ ወታደር፣ “አባትህ ሰራዊቱን፣ ‘ዛሬ እህል የሚቀምስ ማናቸውም ሰው የተረገመ ይሁን!’ በማለት በጽኑ መሐላ አስሯል። ሰው ሁሉ የተዳከመው በዚሁ ምክንያት ነው” አለው።

ዮናታንም እንዲህ አለ፤ “አባቴ በምድሪቱ ላይ ችግር ፈጥሯል፤ ከዚህ ማር ጥቂት በቀመስሁ ጊዜ ዐይኔ እንዴት እንደ በራ ተመልከቱ።14፥29 ወይም ኀይሌ እንዴት እንደ ታደሰ ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው እጅ ከወሰዱት ምርኮ ዛሬ በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ በተሻለ ነበር፤ የተገደሉትም ፍልስጥኤማውያን ቍጥር ከዚህ በበለጠ ነበር።”

በዚያች ዕለት እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ እስከ ኤሎን ድረስ ከመቷቸው በኋላ እጅግ ዝለው ነበር። በምርኮው ላይ ተረባርበው በጉን፣ በሬውንና ጥጃውን በመውሰድ በመሬት ላይ ዐርደው ሥጋውን ከነደሙ በሉት። ከዚያም ለሳኦል፣ “እነሆ፤ ሕዝቡ ሥጋውን ከነደሙ በመብላት እግዚአብሔርን እየበደለ ነው” ተብሎ ተነገረው።

ሳኦልም፣ “ሕግ ተላልፋችኋል፤ በሉ አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባላችሁ አቅርቡልኝ” አለ። እርሱም፣ “በሕዝቡ መካከል እየዞራችሁ፣ ‘እያንዳንዳችሁ በሬዎቻችሁንና በጎቻችሁን አምጡ፤ እዚሁ ዐርዳችሁ ብሉ፤ ነገር ግን ሥጋውን ከነደሙ በመብላት እግዚአብሔርን አትበድሉ’ በሏቸው” አለ።

ስለዚህ በዚያች ሌሊት እያንዳንዱ ሰው በሬውን አምጥቶ በዚያ ዐረደው። ሳኦልም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያ ሲሠራም ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር።

ሳኦልም፣ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትለን በሌሊት እንውረድና እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው፤ አንድም ሰው በሕይወት አናስቀርላቸው” አለ።

እነርሱም፣ “መልካም መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግ” ብለው መለሱለት።

ካህኑ ግን፣ “እዚሁ እግዚአብሔርን እንጠይቅ” አለ።

በዚህ ጊዜ ሳኦል፣ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትዬ ልውረድን? በእስራኤላውያንስ እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። ነገር ግን እግዚአብሔር በዚያች ቀን አልመለሰለትም።

ስለዚህ ሳኦል እንዲህ አለ፤ “የሰራዊቱ መሪዎች ሁላችሁም ወደዚህ ቅረቡ፤ ዛሬ ምን ኀጢአት እንደ ተሠራ እንወቅ። እስራኤልን የታደገ ሕያው እግዚአብሔርን አድራጊው ልጄ ዮናታን እንኳ ቢሆን መሞት አለበት።” ነገር ግን ከሕዝቡ መካከል የመለሰለት አንድም አልነበረም።

ሳኦልም እስራኤላውያንን ሁሉ፣ “እናንተ በዚያ በኩል ቁሙ፤ እኔና ልጄ ዮናታን ደግሞ በዚህ በኩል እንቆማለን” አላቸው።

ሰዎቹም፣ “መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” ብለው መለሱለት።

ከዚያ በኋላ ሳኦል፣ “ትክክለኛውን መልስ ስጠኝ”14፥41 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን ዛሬ ለባሪያህ ያልመለስህለት ለምንድን ነው? ጥፋቱ በእኔና በልጄ በዮናታን ላይ ከሆነ በኡሪም መልስልን፤ ነገር ግን ጥፋቱ በእስራኤል ሰዎች ላይ ከሆነ በቱሚም መልስ ይላል። ሲል ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ ዕጣው በሳኦልና በዮናታን ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም ነጻ ሆነ። ሳኦልም፣ “በእኔና በልጄ በዮናታን መካከልም ዕጣ ጣሉ” አላቸው። ዕጣውም በዮናታን ላይ ወደቀ።

ከዚያም ሳኦል ዮናታንን፣ “እስቲ ያደረግኸውን ንገረኝ” አለው።

ዮናታንም፣ “በዘንጌ ጫፍ ጥቂት ማር ቀምሻለሁ፤ እነሆ፤ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” አለው።

ሳኦልም፣ “ዮናታን፣ አንተ ካልተገደልህ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፣ የከፋም ነገር ያምጣብኝ” አለ።

ሕዝቡ ግን ሳኦልን፣ “ለእስራኤል ይህን ታላቅ ድል ያስገኘ ዮናታን መሞት ይገባዋልን? አይደረግም! ዛሬ ይህን ያደረገው በእግዚአብሔር ርዳታ ስለሆነ፣ ሕያው እግዚአብሔርን! ከራስ ጠጕሩ አንዲቱ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም” አሉት። ስለዚህ ሰዎቹ ዮናታንን ታደጉት፤ እርሱም ከመሞት ዳነ።

ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመለሰ፤ እነርሱም ወደ አገራቸው ተመለሱ።

ሳኦል በእስራኤል ላይ በትረ መንግሥቱን ከጨበጠ በኋላ፣ በዙሪያው ያሉትን ጠላቶቹን ማለትም ሞዓብን፣ አሞናውያንን፣ ኤዶምን፣ የሱባን ነገሥታትና14፥47 የማሶሬ ቅጅ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሙት ባሕር ጥቅልልና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን ንጉሥ ይላል። ፍልስጥኤማውያንን ወጋቸው። በሄደበት ሁሉ ድል ይነሣ14፥47 ዕብራይስጡ ያሠቃያቸው ነበር ሲል፣ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ደግሞ ድል ይነሣቸው ነበር ይላል። ነበር። በጀግንነት ተዋግቶ አማሌቃውያንን አሸነፈ፤ እስራኤልንም ይዘርፏቸው ከነበሩት እጅ ታደጋቸው።

የሳኦል ቤተ ሰብ

የሳኦል ወንዶች ልጆች ዮናታን፣ የሱዊ፣ ሜልኪሳ ነበሩ፤ ሴቶች ልጆቹም ትልቋ ሜሮብ፣ ትንሿ ሜልኮል ይባሉ ነበር። የሳኦል ሚስት አኪናሆም የምትባል የአኪማአስ ልጅ ነበረች፤ የሰራዊቱም አዛዥ አበኔር የሚባል የአጎቱ የኔር ልጅ ነበረ። የሳኦል አባት ቂስና የአበኔር አባት ኔር ሁለቱም የአቢኤል ልጆች ነበሩ።

በሳኦል ዘመን ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ከባድ ጦርነት ነበረ፤ ስለዚህ ሳኦል ብርቱ ወይም ጀግና ሰው ባየ ቍጥር ወደ ራሱ ወስዶ እንዲያገለግለው ያደርግ ነበር።

Read More of 1 ሳሙኤል 14

1 ሳሙኤል 15:1-35

እግዚአብሔር የሳኦልን ንጉሥነት መናቁ

ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ቀብቼ እንዳነግሥህ፣ እግዚአብሔር የላከው እኔን ነው፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር የመጣውን መልእክት አድምጥ። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ፣ አማሌቃውያን በመንገድ ላይ ስለ ተቃወሙት እቀጣቸዋለሁ። አሁንም ሂድ፤ አማሌቃውያንን ውጋ፤ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፤ አንዱንም አታስቀር፤ ወንዱንና ሴቱን፣ ልጁንና ሕፃኑን፣ የቀንድ ከብቱንና በጉን፣ ግመሉንና አህያውን ግደል።’ ”15፥3 በዚህም ሆነ በቍጥር 8፡9፡15፡18፡20 እና 21 ላይ የዕብራይስጡ ቃል አንድን ሰው ወይም ነገር ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያሳይ ነው።

ስለዚህ ሳኦል ሰዎቹን ጥላኢም በተባለ ቦታ ሰብስቦ ቈጠራቸው፤ እነርሱም ሁለት መቶ ሺሕ እግረኛ ወታደሮችና ከይሁዳም ዐሥር ሺሕ ሰዎች ነበሩ፤ ሳኦልም ወደ አማሌቅ ከተማ ሄዶ በአንዲት ሸለቆ ውስጥ አደፈጠ። እርሱም፣ ቄናውያንን፣ “ከእነርሱ ጋር እንዳላጠፋችሁ ከአማሌቃውያን ራቁ፤ ተለዩአቸውም፤ እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡ ጊዜ፣ ቸርነት አድርጋችሁላቸዋልና” አላቸው። ስለዚህ ቄናውያን ከአማሌቃውያን ተለዩ።

ከዚያም ሳኦል አማሌቃውያንን ከኤውላጥ አንሥቶ በምሥራቅ ግብፅ እስካለው እስከ ሱር ድረስ ወጋቸው። የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን ከነሕይወቱ ማረከው፤ ሕዝቡን ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋቸው። ነገር ግን ሳኦልና ሰራዊቱ አጋግን፣ ምርጥ ምርጡን በግና የቀንድ ከብት፣ የሰባውን ጥጃና15፥9 ወይም ያደገ ጥጃ የዚህ ሐረግ የዕብራይስጡ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። ጠቦት፣ መልካም የሆነውን ሁሉ ሳይገድሉ ተውት። እነዚህን ፈጽመው ለማጥፋት ፈቃደኞች አልነበሩም፤ ነገር ግን የተናቀውንና የማይጠቅመውን ሁሉ አጠፉ።

ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሳሙኤል መጣ፤ “ሳኦልን በማንገሤ ተጸጽቻለሁ፤ እኔን ከመከተል ተመልሷልና፣ ትእዛዜንም አልፈጸመምና።” ሳሙኤልም እጅግ ተጨንቆ፣ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።

ሳሙኤልም ጧት ተነሥቶ በማለዳ ሳኦልን ለመገናኘት ሄደ፤ ነገር ግን፣ “ሳኦል ወደ ቀርሜሎስ ሄዷል፤ ለራሱ ክብር የመታሰቢያ ሐውልት በዚያ ካቆመ በኋላ ተመልሶ ወደ ጌልገላ ወርዷል” ተብሎ ተነገረው።

ሳሙኤል ባገኘው ጊዜ ሳኦል፣ “እግዚአብሔር ይባርክህ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ” አለው።

ሳሙኤል ግን፣ “ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።

ሳኦልም፣ “ሰራዊቱ ከአማሌቃውያን ማርከው ያመጧቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጦቹ በጎችና በሬዎች ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይገድሉ የተዉአቸው ናቸው፤ የቀሩትን ግን በሙሉ አጥፍተናል” ብሎ መለሰ።

ሳሙኤልም ሳኦልን፣ “ስማ! ትናንት ማታ እግዚአብሔር የነገረኝን ልንገርህ?” አለው።

ሳኦልም፣ “ንገረኝ” ሲል መለሰለት።

ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “በዐይንህ ፊት ታናሽ የነበርህ ብትሆንም፣ የእስራኤል ነገዶች መሪ ሆነህ የለምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል። እግዚአብሔርም፣ ‘ሄደህ እነዚያን ኀጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ጨርሰህ እስክታጠፋቸውም ድረስ ውጋቸው’ ብሎ ልኮህ ነበር። ታዲያ እግዚአብሔርን ለምን አልታዘዝህም? ለምርኮውስ ተስገብግበህ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ለምን አደረግህ?”

ሳኦልም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔርን ታዝዣለሁ፤ እግዚአብሔር በላከኝ መሠረት ሄጃለሁ፤ አማሌቃውያንን በሙሉ አጥፍቼ ንጉሣቸውን አጋግን አምጥቻለሁ። ሰራዊቱ ግን ከምርኮው ለእግዚአብሔር ከተለዩት መካከል፣ ምርጥ ምርጡን በግና በሬ፣ በጌልገላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ወስደዋል።”

ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤

“ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር

በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን?

እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣

ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል።

ዐመፅ እንደ ጥንቈላ ያለ ኀጢአት፣

እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው። አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ፣ እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።”

ከዚያም ሳኦል ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን መመሪያ ጥሻለሁ፤ ሕዝቡን ፈርቼ ስለ ነበር፣ የጠየቁኝን ታዝዣለሁ። አሁንም፣ ኀጢአቴን ይቅር እንድትለኝ፣ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ አብረኸኝ እንድትመለስ እለምንሃለሁ።”

ሳሙኤል ግን፣ “ከአንተ ጋር አልመለስም፤ አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃል፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል” አለው።

ሳሙኤል ለመሄድ ዘወር ባለ ጊዜ፣ ሳኦል የልብሱን ጫፍ ያዘ፤ ተቀደደም። ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀዶታል፤ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጥቶታል። የእስራኤል ክብር የሆነው እግዚአብሔር አይዋሽም፤ አይጸጸትምም፤ እርሱ ይጸጸት ዘንድ ሰው አይደለምና።”

ሳኦልም መልሶ፣ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ ነገር ግን በሕዝቤ አለቆች ፊትና በእስራኤል ፊት አክብረኝ፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ እባክህ አብረኸኝ ተመለስ” አለው። ስለዚህ ሳሙኤል አብሮት ተመለሰ፤ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ።

ከዚያም ሳሙኤል፣ “የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ” አለ።

አጋግም፣ “በውኑ ሞት እንዲህ መራራ ነውን?” በማለት እየተንቀጠቀጠ መጣ።

ሳሙኤልም፣

“ሰይፍህ ሴቶችን ልጅ አልባ እንዳደረገቻቸው፣

እናትህም በሴቶች መካከል ልጅ አልባ ትሆናለች”

ሲል አጋግን ጌልገላ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቈራረጠው።

ከዚያም ሳሙኤል ወደ አርማቴም ሄደ። ሳኦል ግን ወደ ቤቱ ወደ ሳኦል ጊብዓ ወጣ። ሳሙኤል ለሳኦል ቢያለቅስለትም እንኳ እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ ዳግመኛ ሊያየው አልሄደም፤ እግዚአብሔርም ሳኦልን በእስራኤል ላይ በማንገሡ ተጸጸተ።

Read More of 1 ሳሙኤል 15