1 ነገሥት 20:1-43, 1 ነገሥት 21:1-29 NASV

1 ነገሥት 20:1-43

ቤን ሀዳድ ሰማርያን ወጋ

በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ መላ ሰራዊቱን በአንድነት አሰባሰበ፤ ከእርሱም ጋር ሠላሳ ሁለት ነገሥታት ከነፈረሶቻቸውና ከነሠረገሎቻቸው አብረውት ነበሩ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከብቦ ወጋት። ወደ ከተማዪቱም መልእክተኞች በመላክ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን እንዲህ አለው፤ “ቤን ሀዳድ እንዲህ ይላል፤ ‘ብርና ወርቅህ የእኔ ነው፤ የሚያማምሩት ሚስቶችህና ልጆችህም የእኔ ናቸው።’ ”

የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ልክ እንዳልኸው ነው፤ እኔም ሆንሁ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” ሲል መለሰለት።

መልክተኞቹም እንደ ገና መጥተው እንዲህ አሉት፤ “ቤን ሀዳድ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ብርህንና ወርቅህን፣ ሚስቶችህንና ልጆችህን እንድትሰጠኝ ልኬብህ ነበር፤ ሆኖም ነገ በዚሁ ጊዜ ቤተ መንግሥትህንና የሹማምትህን ቤቶች እንዲበረብሩ፣ ሹማምቴን እልካቸዋለሁ። እነርሱም ማናቸውንም ለአንተ ዋጋ ያለውን ሁሉ በእጃቸው በማስገባት ይወስዱታል።’ ”

የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፣ “ይህ ሰው እንዴት ጠብ እንደሚፈልግ ታያላችሁ፤ ሚስቶቼንና ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንዳስረክበው በጠየቀኝ ጊዜ አልከለከልሁትም” አላቸው።

ሽማግሌዎቹና ሕዝቡም ሁሉ፣ “የሚልህን አትቀበለው፤ የጠየቀህንም እሺ አትበለው” አሉት።

ስለዚህ ለቤን ሀዳድ መልእክተኞች፣ “ለጌታዬ ለንጉሡ፣ ‘እኔ ባሪያህ በመጀመሪያ ያልኸኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤ ያሁኑን ጥያቄህን ግን ልፈጽመው አልችልም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። መልእክተኞቹም ይህንኑ ይዘው ተመለሱ።

ከዚያም ቤን ሀዳድ፣ “ለሚከተለኝ ሰው ሁሉ የሰማርያ ዐፈር አንዳንድ ዕፍኝ የሚዳረስ ሳይሆን ቢቀር፣ አማልክት ይህን ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ሲል ሌሎች መልክተኞችን ወደ አክዓብ ላከ።

የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ ‘ታጥቆ ለጦርነት የሚወጣ ሰው የጦር ትጥቁን እንደ ፈታ ሰው መደንፋት የለበትም’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው።

ቤን ሀዳድ ይህን መልእክት የሰማው አብረውት የነበሩት ነገሥታት በድንኳኖቻቸው20፥12 ወይም ሱኮት በ16 ላይም እንደዚሁ፤ ውስጥ ሆነው በሚጠጡበት ጊዜ ነበር፤ ቤን ሀዳድ ሰዎቹን፣ “በሉ ለጦርነት ተዘጋጁ” አላቸው፤ ስለዚህ ከተማዪቱን ለመውጋት ተዘጋጁ።

አክዓብ ቤን ሀዳድን ድል አደረገ

በዚያን ጊዜ አንድ ነቢይ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ አክዓብ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ብዙ ሰራዊት ታያለህን? ዛሬ በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው።

አክዓብም፣ “ይህን የሚያደርገው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።

ነቢዩም፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን የሚያደርጉት የየአውራጃው አዛዥ የሆኑ ወጣት መኰንኖች ናቸው’ ” አለው።

“ታዲያ ጦርነቱን የሚጀምረው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ።

ነቢዩም፣ “አንተው ትጀምራለህ” ብሎ መለሰ።

ስለዚህ አክዓብ የየአውራጃው አዛዥ የሆኑትን ሁለት መቶ ሠላሳ ሁለት ወጣት መኰንኖች ጠራ፤ ከዚያም የቀሩትን እስራኤላውያን ሰበሰበ፤ እነዚህም በአጠቃላይ ሰባት ሺሕ ነበሩ። እነርሱም ቤን ሀዳድና ከእርሱ ጋር ተባብረው የነበሩት ሠላሳ ሁለቱ ነገሥታት በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሰክረው ሳለ እኩለ ቀን ላይ መጡ። በግንባር ቀደምትነት የወጡት ግን፣ የየአውራጃው አዛዥ የሆኑት ወጣት መኰንኖች ነበሩ።

በዚህ ጊዜ ቤን ሀዳድ ሰላዮች ልኮ ነበርና እነርሱም፣ “ሰዎች ከሰማርያ ወጥተው ወደዚህ በመምጣት ላይ ናቸው” ብለው ነገሩት።

እርሱም፣ “አመጣጣቸው ለሰላምም ይሁን ለጦርነት ከነሕይወታቸው ይዛችሁ አምጧቸው” አለ።

የየአውራጃው አዛዥ የሆኑ ወጣት መኰንኖችም ሰራዊቱን አስከትለው ከከተማዪቱ ወጡ፤ እያንዳንዱም በፊቱ የገጠመውን ጠላት ገደለ፤ ሶርያውያን ሸሹ፤ እስራኤላውያንም ያሳድዷቸው ጀመር። የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ ግን በፈረሱ ላይ ሆኖ ከጥቂት ፈረሰኞቹ ጋር አመለጠ። የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም ወደ ፊት በመግፋት ፈረሶችንና ሠረገሎችን ማረከ፤ በሶርያውያንም ላይ ከባድ ጕዳት አደረሰባቸው።

ከዚያም በኋላ ነቢዩ ወደ እስራኤል ንጉሥ መጥቶ፣ “በሚመጣው የጸደይ ወራት የሶርያ ንጉሥ ተመልሶ ይመጣብሃልና በርታ፤ ምን ማድረግ እንዳለብህም ዕወቅ” አለው።

በዚያኑ ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ሹማምት እንዲህ ሲሉ መከሩት፤ “አማልክታቸው የኰረብታ አማልክት ናቸው፤ ያየሉብንም ከዚህ የተነሣ ነው። በሜዳ ላይ ብንገጥማቸው ግን እኛ እንደምናይልባቸው አያጠራጥርም። እንግዲህ እንዲህ አድርግ፤ ነገሥታቱን በሙሉ ከአዛዥነታቸው አስነሣ፤ በቦታቸውም ሌሎች ሹማምት አድርግ። ከእስራኤል ጋር በሜዳው ላይ እንዲጋጠም በፈረሱ ፈንታ ፈረስ፣ በሠረገላው ፈንታ ሠረገላ በመተካት፣ እንደ ተደመሰሰው ያለ ሰራዊት አቋቁም፤ ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ይበልጥ እኛ እንደምንበረታ አያጠራጥርም።” ንጉሡም ባቀረቡት ሐሳብ ተስማማ፤ እንዳሉትም አደረገ።

በተከታዩም የጸደይ ወራት ቤን ሀዳድ ሶርያውያንን አሰባስቦ እስራኤልን ለመውጋት ወደ አፌቅ ወጣ። እስራኤላውያንም እንደዚሁ ተሰብስበው ስንቅ ከተሰጣቸው በኋላ ሊገጥሟቸው ተሰልፈው ወጡ። ሶርያውያን አገር ምድሩን ሞልተውት ሳለ፣ እስራኤላውያን ግን እንደ ሁለት ትንንሽ የፍየል መንጋ ሆነው ከፊት ለፊታቸው ሰፈሩ።

የእግዚአብሔርም ሰው ወጥቶ ለእስራኤል ንጉሥ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እግዚአብሔር የኰረብታ እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ስፍር ቍጥር የሌለው ሰራዊት በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው።

በየሰፈሩበትም ቦታ ሰባት ቀን ከተፋጠጡ በኋላ በሰባተኛው ቀን ጦርነት ገጠሙ። እስራኤላውያንም በአንዲት ጀምበር ከሶርያውያን ሰራዊት መቶ ሺሕ እግረኛ ገደሉ። የቀሩት ወደ አፌቅ ከተማ ሸሹ፤ በዚያም በሃያ ሰባቱ ሺሕ ላይ ቅጥሩ ተንዶ ወደቀባቸው። ቤን ሃዳድም ወደ ከተማዪቱ ሸሽቶ በመሄድ ወደ አንዲት እልፍኝ ገብቶ ተደበቀ።

ሹማምቱም፣ “የእስራኤል ቤት ነገሥታት መሓሪዎች መሆናቸውን ሰምተናል፤ አሁንም እንነሣና በወገባችን ላይ ማቅ ታጥቀን፣ በራሳችን ላይ ገመድ ጠምጥመን ወደ እስራኤል ንጉሥ እንሂድ፤ ምናልባትም ሕይወትህን ያተርፋት ይሆናል” አሉት።

እነርሱም በወገባቸው ላይ ማቅ ታጥቀው፣ በራሳቸው ላይ ገመድ ጠምጥመው ወደ እስራኤል ንጉሥ በመሄድ፣ “አገልጋይህ ቤን ሀዳድ፣ ‘እባክህ በሕይወት እንድኖር ፍቀድልኝ’ ብሎ ይለምንሃል” አሉት።

ንጉሡም፣ “እስካሁን በሕይወት አለን? ወንድሜ እኮ ነው” አለ።

ሰዎቹም ይህን በደግ በመተርጐም ቃሉን ከአፉ ቀበል አድርገው፤ “አዎን ቤን ሀዳድ ወንድምህ ነው” አሉት።

ንጉሡም፣ “በሉ ሂዱና አምጡት” አላቸው፤ ቤን ሃዳድም በመጣ ጊዜ፣ አክዓብ ሠረገላው ላይ እንዲወጣ አደረገው።

ቤን ሃዳድም፣ “አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልሳለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ፣ አንተም በደማስቆ የራስህን ገበያ ማቋቋም ትችላለህ” አለው።

አክዓብም፣ “እንግዲያውስ ስምምነት አድርገን በነጻ እለቅቅሃለሁ” አለው፤ ስለዚህም ከእርሱ ጋር የውል ስምምነት አድርጎ ለቀቀው።

አንድ ነቢይ በአክዓብ ላይ ፈረደ

ከነቢያት ልጆች አንዱ ጓደኛውን በእግዚአብሔር ቃል ታዞ፣ “ምታኝ” አለው፤ ሰውየው ግን ፈቃደኛ አልሆነም።

ስለዚህም ነቢዩ፣ “ለእግዚአብሔር ባለ መታዘዝህ፣ ከእኔ ተለይተህ እንደ ሄድህ አንበሳ ይገድልሃል” አለው። ሰውየው ከሄደ በኋላ አንበሳ አግኝቶ ገደለው።

ነቢዩም ሌላ ሰው አግኝቶ፣ “እባክህ ምታኝ” አለው። ስለዚህ ያ ሰው መትቶ አቈሰለው። ከዚያም ነቢዩ ሄዶ ከመንገድ ዳር በመቆም፣ ንጉሡን ይጠባበቅ ጀመር። የራሱን መጠምጠሚያ ወደ ታች አውርዶ ዐይኖቹን በመሸፈንም፣ ማንነቱ እንዳይታወቅ አደረገ። ንጉሡ በዚያ በሚያልፍበትም ጊዜ፣ ነቢዩ ጠርቶት እንዲህ አለው፤ “እኔ አገልጋይህ በተፋፋመው ጦርነት መካከል ገብቼ ሳለሁ፣ አንድ ሰው ምርኮኛ ይዞ መጥቶ ‘ይህን ሰው ጠብቅ፤ ቢያመልጥ በገመዱ ትገባለህ ወይም አንድ መክሊት20፥39 34 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር ትከፍላለህ’ አለኝ። ‘ታዲያ እኔ አገልጋይህ ሥራ በዝቶብኝ ወዲያ ወዲህ ስል ሰውየው አምልጦ ሄደ።’ ”

የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ራስህ ፈርደሃል፤ ይኸው ይፈጸምብሃል” አለው።

ከዚያም ነቢዩ መጠምጠሚያውን በፍጥነት ከዐይኑ ላይ አነሣ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ያ ሰው ከነቢያት አንዱ መሆኑን ዐወቀ። ነቢዩም ንጉሡን አለው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ ፈጽሞ ይገደል20፥42 የዕብራይስጡ ቃል ሰውን ወይም ቍስን ፈጽሞ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠት የሚለውን ያመለክታል። ያልሁትን ሰው ለቅቀኸዋልና በገመዱ ትገባለህ፤ በሕዝቡም ፈንታ ያንተ ሕዝብ በገመዱ ይገባል።’ ” የእስራኤልም ንጉሥ ተበሳጭቶና ተቈጥቶ ሰማርያ ወዳለው ቤተ መንግሥቱ ሄደ።

Read More of 1 ነገሥት 20

1 ነገሥት 21:1-29

የናቡቴ የወይን ተክል ቦታ

ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ የወይን ተክል ቦታ ላይ አንድ ነገር ደረሰ፤ ቦታውም በኢይዝራኤል ውስጥ ከሰማርያ ንጉሥ ከአክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ ነበር። አክዓብም ናቡቴን፣ “የወይን ተክል ቦታህ ከቤተ መንግሥቴ አጠገብ ስለሆነ፣ የአትክልት ቦታ እንዳደርገው ልቀቅልኝ፤ በምትኩ ከዚህ የበለጠ የወይን ተክል ቦታ እሰጥሃለሁ፤ የተሻለ ሆኖ ከታየህም የሚያወጣውን ገንዘብ እከፍልሃለሁ” አለው።

ናቡቴ ግን፣ “ዐፅመ ርስቴን እለቅልህ ዘንድ እግዚአብሔር አይበለው” ሲል መለሰለት።

ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ፣ “ዐፅመ ርስቴን አልለቅልህም” ስላለው፣ አክዓብ ተበሳጭቶና ተቈጥቶ ወደ ቤቱ ገባ፤ አኵርፎም በዐልጋው ላይ ተኛ፤ ምግብም መብላት ተወ።

ሚስቱ ኤልዛቤልም ወደ እርሱ ገብታ፣ “እስከዚህ የተበሳጨኸው፣ ምግብስ የማትበላው ለምንድን ነው?” ብላ ጠየቀችው።

እርሱም፣ “ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን፣ ‘የወይን ተክል ቦታህን ሽጥልኝ፤ ከፈለግህም በምትኩ ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ’ አልሁት፤ እርሱ ግን፣ ‘የወይን ተክል ቦታዬን አልለቅልህም’ ስላለኝ ነው” አላት።

ሚስቱ ኤልዛቤልም፣ “አንተ አሁን የእስራኤል ንጉሥ ትባላለህ? በል ተነሥና እህል ቅመስ፤ ደስም ይበልህ፤ የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ እኔ እንድታገኝ አደርግሃለሁ” አለችው። ስለዚህ በአክዓብ ስም ደብዳቤዎች ጻፈች፤ በገዛ ማኅተሙም ዐትማ በናቡቴ ከተማ አብረውት ለሚኖሩ ሽማግሌዎችና መኳንንት ላከች። በደብዳቤዎቹም ላይ እንዲህ ስትል ጻፈች፤

“የአንድ ቀን ጾም ዐውጁ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ መካከል ከፍ ባለ ቦታ ላይ አስቀምጡት። እንዲሁም ሁለት የሐሰት ምስክሮች ከፊት ለፊቱ አስቀምጡና፣ ‘እግዚአብሔርንም ንጉሡንም ሰድቧል’ ብለው ይመስክሩበት፤ ከዚያም አውጥታችሁ በድንጋይ ወግራችሁ ግደሉት።”

ስለዚህ በናቡቴ ከተማ የሚኖሩ ሽማግሌዎችና መኳንንት በደብዳቤዎቹ ላይ እንደ ጻፈችላቸው አደረጉ። የአንድ ቀን ጾም ዐወጁ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ መካከል ከፍ ባለ ቦታ ላይ አስቀመጡት። ከዚያም ሁለት የሐሰት ምስክሮች መጥተው ከፊት ለፊቱ ተቀመጡ፤ በሕዝቡም ፊት፣ “ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቧል” ብለው መሰከሩበት። ስለዚህ ከከተማዪቱ ውጭ ወስደው በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ከዚያም ለኤልዛቤል፣ “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቷል” ብለው ላኩባት።

ኤልዛቤልም በድንጋይ ተወግሮ መሞቱን ወዲያው እንደ ሰማች አክዓብን፣ “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቷል፤ በል ተነሣና ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ ሊሸጥልህ ያልፈለገውን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ውሰደው” አለችው። አክዓብ የናቡቴን ሞት ሲሰማ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ተነሥቶ ወረደ።

ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ “ተነሣና በሰማርያ ሆኖ የሚገዛውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ሄዶ አሁን እዚያው ይገኛል። እንዲህም በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰውየውን ገደልኸው፤ ደግሞ ርስቱን ልትወስድ?’ ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ቦታ የአንተንም ደም ውሾች እንዲሁ ይልሱታል!’ ”

አክዓብም ኤልያስን፣ “ጠላቴ ሆይ አገኘኸኝን?” አለው።

ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “በእግዚአብሔር ፊት የተጠላውን ነገር ለማድረግ ራስህን ሸጠሃልና አዎን አግኝቼሃለሁ። ‘እነሆ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፤ ዘርህን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ባሪያም ይሁን ነጻ እያንዳንዱን የአክዓብን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ከእስራኤል እጠርጋለሁ። ለቍጣ ስላነሣሣኸኝና እስራኤልንም ስላሳትሃቸው፣ ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፣ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።’

“ስለ ኤልዛቤልም እግዚአብሔር፣ ‘በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ21፥23 አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ ነገር ግን አንዳንድ የዕብራይስጥ ቅጆች፣ ቩልጌትና የሱርስቱ ትርጕም (2ነገ 9፥26 ይመ)፣ በዕርሻው ማሳ ላይ ይላሉ። ውሾች ኤልዛቤልን ይበሏታል’ ይላል።

“ደግሞም ከአክዓብ ወገን ሆኖ በከተማ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በገጠር የሞተውንም የሰማይ አሞሮች ይበሉታል።”

በሚስቱ በኤልዛቤል ተገፋፍቶ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ለማድረግ ራሱን የሸጠ እንደ አክዓብ ያለ ሰው ከቶ አልነበረም። እግዚአብሔር ከእስራኤል ፊት ያሳደዳቸው አሞራውያን እንዳደረጉት ሁሉ፣ እርሱም ጣዖታትን በማምለክ እጅግ የሚያስጸይፍ ርኩሰት ፈጸመ።

አክዓብም ይህን ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶ፤ ጾመ፤ በማቅ ላይ ተኛ በሐዘን ኵርምት ብሎም ይሄድ ነበር።

ከዚያም እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ መጣ፤ “አክዓብ ራሱን በፊቴ እንዴት እንዳዋረደ አየህን? ራሱን ስላዋረደ ይህን መከራ በዘመኑ አላመጣበትም፤ ነገር ግን ይህን በቤቱ ላይ የማመጣው በልጁ ዘመን ነው።”

Read More of 1 ነገሥት 21