Псалтирь 119 – NRT & NASV

New Russian Translation

Псалтирь 119:1-7

Псалом 119

1Песнь восхождения119:1 Песнь восхождения – согласно средневековым и раввинским преданиям, 15 псалмов (с 119 по 133) воспевались на 15 ступенях лестницы, ведущей из «женского двора» во «двор израильтян» в Иерусалимском храме послепленной эпохи. Однако более вероятно, что они воспевались паломниками, следовавшими в Иерусалим на ежегодные религиозные праздники..

В скорби своей я воззвал к Господу,

и Он ответил мне.

2Я сказал: «Избавь мою душу, Господи,

от лгущих уст и обманчивого языка!»

3Что Он даст тебе

и что прибавит, обманчивый язык?

4Он накажет тебя острыми стрелами воина

и горящими углями из дрока.

5Горе мне, что пребываю в Мешехе

и живу среди кедарских шатров!119:5 Местность Мешех находится в Малой Азии. Местность Кедар находится в Аравии (см. Ис. 21:13-17; Иез. 27:21). Эти местности – символы очень отдаленных от Израиля земель.

6Душа моя долго жила

с ненавидящими мир.

7Я – мирный человек,

но только заговорю – они к войне.

New Amharic Standard Version

መዝሙር 119:1-176

መዝሙር 119119 የዚህ መዝሙር የግጥም ስንኞች መነሻ ወይም መነሻና መድረሻ ሆህያት ቍልቍል ሲነበቡ ትርጕም ዐዘል ናቸው። እያንዳንዱ ስንኝ ተመሳሳይ በሆነ በዕብራይስጥ ፊደል ይጀምራል።

ውዳሴ ለሕገ እግዚአብሔር

א አሌፍ

1መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት፣

በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው።

2ምስክርነቱን የሚጠብቁ፣

በፍጹምም ልብ የሚሹት የተባረኩ ናቸው፤

3ዐመፅን አያደርጉም፤

ነገር ግን በመንገዱ ይሄዳሉ።

4ጠንቅቀን እንጠብቃት ዘንድ፣

አንተ ሥርዐትን አዝዘሃል።

5ሥርዐትህን እጠብቅ ዘንድ፣

ምነው መንገዴ ጽኑ በሆነልኝ ኖሮ!

6ወደ ትእዛዞችህ ስመለከት፣

በዚያን ጊዜ አላፍርም።

7የጽድቅ ፍርድህን ስማር፣

በቅን ልብ ምስጋና አቀርብልሃለሁ።

8ሥርዐትህን እጠብቃለሁ፤

ፈጽመህ አትተወኝ።

ב ቤት

9ጕልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል?

በቃልህ መሠረት በመኖር ነው።

10በሙሉ ልቤ ፈለግሁህ፤

ከትእዛዞችህ ፈቀቅ እንዳልል አድርገኝ።

11አንተን እንዳልበድል፣

ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።

12እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤

ሥርዐትህን አስተምረኝ።

13ከአንደበትህ የሚወጣውን ደንብ ሁሉ፣

በከንፈሬ እናገራለሁ።

14ሰው በሀብቱ ብዛት ደስ እንደሚለው፣

ምስክርነትህን በመከተል ደስ ይለኛል።

15ድንጋጌህን አሰላስላለሁ፤

ልቤን በመንገድህ ላይ ጥያለሁ።

16በሥርዐትህ ደስ ይለኛል፤

ቃልህንም አልዘነጋም።

ג ጊሜል

17ሕያው እንድሆን፣ ቃልህንም እንድጠብቅ፣

ለአገልጋይህ መልካም አድርግ።

18ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣

ዐይኖቼን ክፈት።

19እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፤

ትእዛዞችህን ከእኔ አትሰውር።

20ዘወትር ደንብህን በመናፈቅ፣

ነፍሴ እጅግ ዛለች።

21ከትእዛዞችህ የሳቱትን፣

እብሪተኞችንና ርጉሞችን ትገሥጻለህ።

22ምስክርነትህን ጠብቄአለሁና፣

ስድብንና ንቀትን ከእኔ አርቅ።

23ገዦች ተቀምጠው ቢዶልቱብኝ እንኳ፣

አገልጋይህ ሥርዐትህን ያሰላስላል።

24ምስክርነትህ ለእኔ ደስታዬ ነው፤

መካሪዬም ነው።

ד ዳሌት

25ነፍሴ ከዐፈር ተጣበቀች፤

እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።

26ስለ መንገዴ ገልጬ ነገርሁህ፤ አንተም መለስህልኝ፤

ሥርዐትህን አስተምረኝ።

27የድንጋጌህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፤

እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ።

28ነፍሴ በሐዘን ተዝለፈለፈች፤

እንደ ቃልህ አበርታኝ።

29የሽንገላን መንገድ ከእኔ አርቅ፤

ሕግህን በጸጋህ ስጠኝ።

30የእውነትን መንገድ መርጫለሁ፤

ሕግህንም ፊት ለፊቴ አድርጌአለሁ።

31እግዚአብሔር ሆይ፤ ከምስክርነትህ ጋር ተጣብቄአለሁ፤

አሳልፈህ ለውርደት አትስጠኝ።

32ልቤን አስፍተህልኛልና፣

በትእዛዞችህ መንገድ እሮጣለሁ።

ה ሄ

33እግዚአብሔር ሆይ፤ የሥርዐትህን መንገድ አስተምረኝ፤

እኔም እስከ መጨረሻው እጠብቀዋለሁ።

34ሕግህን እንድጠብቅ፣ በፍጹም ልቤም እንድታዘዘው፣ ማስተዋልን ስጠኝ።

35በእርሷ ደስ ይለኛልና፣

በትእዛዝህ መንገድ ምራኝ።

36ከራስ ጥቅም ይልቅ፣

ልቤን ወደ ምስክርነትህ አዘንብል።

37ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ፤

በራስህ መንገድ119፥37 አንዳንድ ትርጕሞች እንደ ቃልህ ይላሉ። እንደ ገና ሕያው አድርገኝ።

38ትፈራ ዘንድ፣

ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ፈጽም።

39የምፈራውን መዋረድ ከእኔ አርቅ፤

ደንብህ መልካም ነውና።

40እነሆ፤ ድንጋጌህን ናፈቅሁ፤

በጽድቅህ ሕያው አድርገኝ።

ו ዋው

41እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ወደ እኔ ይምጣ፤

ማዳንህም እንደ ቃልህ ይላክልኝ።

42በቃልህ ታምኛለሁና፣

ለሚሰድቡኝ መልስ እሰጣለሁ።

43ሕግህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣

የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ።

44ከዘላለም እስከ ዘላለም፣

ሕግህን ዘወትር እጠብቃለሁ።

45ሥርዐትህን እሻለሁና፣

እንደ ልቤ ወዲያ ወዲህ እመላለሳለሁ።

46ምስክርነትህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤

ይህን በማድረግም ዕፍረት አይሰማኝም።

47እኔ እወድደዋለሁና፣

በትእዛዝህ ደስ ይለኛል።

48እጆቼን ወደምወዳቸው119፥48 ወይም ለምወድዳቸው ትእዛዞችህ አነሣለሁ፤

ሥርዐትህንም አሰላስላለሁ።

ז ዛይን

49ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ዐስብ፤

በዚያ ተስፋ ሰጥተኸዋልና።

50ቃልህ ሕያው ያደርገኛልና፣

ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት።

51እብሪተኞች እጅግ ተሣለቁብኝ፤

እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አልልም።

52እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥንት የነበረውን ድንጋጌህን አሰብሁ፤ በዚህም ተጽናናሁ።

53ሕግህን ከተዉ ክፉዎች የተነሣ፣

ቍጣ ወረረኝ።

54በእንግድነቴ አገር፣

ሥርዐትህ መዝሙሬ ናት።

55እግዚአብሔር ሆይ፤ ስምህን በሌሊት ዐስባለሁ፤

ሕግህንም እጠብቃለሁ።

56ሥርዐትህን እከተላለሁ፤

ይህችም ተግባሬ ሆነች።

ח ኼት

57እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤

ቃልህን ለመታዘዝ ቈርጫለሁ።

58በፍጹም ልቤ ፊትህን ፈለግሁ፤

እንደ ቃልህ ቸርነትህን አሳየኝ።

59መንገዴን ቃኘሁ፤

አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ።

60ትእዛዝህን ለመጠበቅ፣

ቸኰልሁ፤ አልዘገየሁምም።

61የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም።

62ስለ ጻድቅ ሥርዐትህ፣

በእኩለ ሌሊት ላመሰግንህ እነሣለሁ።

63እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፣

ሥርዐትህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ።

64እግዚአብሔር ሆይ፤ ምድር በምሕረትህ ተሞላች፤

ሥርዐትህን አስተምረኝ።

ט ቴት

65እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ፣

ለአገልጋይህ በጎ ውለሃል።

66በትእዛዞችህ አምናለሁና፣

በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትን አስተምረኝ።

67እንዲያው ሳይቸግረኝ መንገድ ስቼ ሄድሁ፤

አሁን ግን ቃልህን እጠብቃለሁ።

68አንተ መልካም ነህ፤ የምታደርገው መልካም ነው፤

እንግዲህ ሥርዐትህን አስተምረኝ።

69እብሪተኞች ስሜን በሐሰት አጠፉ፤

እኔ ግን ትእዛዝህን በፍጹም ልብ እጠብቃለሁ።

70ልባቸው የሠባና የደነደነ ነው፤

እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል።

71ሥርዐትህን እማር ዘንድ፣

በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ።

72ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣

ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል።

י ዮድ

73እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤

ትእዛዞችህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ።

74ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣

የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው።

75እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣

ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደ ሆነ ዐወቅሁ።

76ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣

ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ።

77ሕግህ ደስታዬ ነውና፣

በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ።

78እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤

እኔ ግን ትእዛዞችህን አሰላስላለሁ።

79አንተን የሚፈሩህ፣

ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ።

80እኔ እንዳላፍር፣ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን።

כ ካፍ

81ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች፤

ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ።

82“መቼ ታጽናናኛለህ?” እያልሁ፣

ዐይኖቼ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ።

83ጢስ የጠጣ የወይን አቍማዳ ብመስልም፣

ሥርዐትህን አልረሳሁም።

84የባሪያህ ዕድሜ ስንት ቢሆን ነው?

ታዲያ፣ በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ይሆን?

85በሕግህ መሠረት የማይሄዱ እብሪተኞች

ማጥመጃ ጕድጓድ ቈፈሩልኝ።

86ትእዛዞችህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው፤

ሰዎች ያለ ምክንያት አሳድደውኛልና ርዳኝ።

87ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤

እኔ ግን ትእዛዞችህን አልተውሁም።

88እንደ ምሕረትህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ፤

እኔም የአፍህን ምስክርነት እጠብቃለሁ።

ל ላሜድ

89እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃልህ በሰማይ፣

ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።

90ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ይኖራል፤

ምድርን መሠረትሃት፤ እርሷም ጸንታ ትኖራለች።

91ሁሉም አገልጋይህ ነውና፣

በሕግህ መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንተው ይኖራሉ።

92ሕግህ ደስታዬ ባይሆን ኖሮ፣

በመከራዬ ወቅት በጠፋሁ ነበር።

93በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና፣

ትእዛዝህን ከቶ አልረሳም።

94እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ፤

ሕግህንም ፈልጌአለሁና።

95ክፉዎች ሊያጠፉኝ አድብተዋል፤

እኔ ግን ምስክርነትህን አሰላስላለሁ።

96ለፍጹምነት ሁሉ ዳርቻ እንዳለው አየሁ፤

ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው።

מ ሜም

97አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!

ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።

98ትእዛዞችህ ምንጊዜም ስለማይለዩኝ፣

ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረጉኝ።

99ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣

ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ።

100መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣

ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ።

101ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣

እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ።

102አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና፣

ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም።

103ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው!

ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው።

104ከመመሪያህ ማስተዋልን አገኘሁ፤

ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።

נ ኑን

105ሕግህ ለእግሬ መብራት፣

ለመንገዴም ብርሃን ነው።

106የጽድቅ ሕግህን ለመጠበቅ፤

ምያለሁ፤ ይህንኑ አጸናለሁ።

107እጅግ ተቸግሬአለሁ፤

እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።

108እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈቅጄ ያቀረብሁትን የአፌን የምስጋና መሥዋዕት ተቀበል፤

ሕግህንም አስተምረኝ።

109ነፍሴ ዘወትር አደጋ ላይ ናት፤

ሕግህን ግን አልረሳሁም።

110ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ፤

እኔ ግን መመሪያህን አልተላለፍሁም።

111ምስክርነትህ የዘላለም ውርሴ ናት፤

ልቤ በዚህ ሐሤት ያደርጋልና።

112ትእዛዝህን ለዘላለም፣ እስከ ወዲያኛው ለመፈጸም፣

ልቤን ወደዚያው አዘነበልሁ።

ס ሳሜክ

113መንታ ልብ ያላቸውን ጠላሁ፤

ሕግህን ግን ወደድሁ።

114አንተ መጠጊያዬና ጋሻዬ ነህ፤

ቃልህን በተስፋ እጠብቃለሁ።

115የአምላኬን ትእዛዞች እጠብቅ ዘንድ፣

እናንት ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ራቁ።

116እንደ ቃልህ ደግፈኝ፤ እኔም ሕያው እሆናለሁ፤

ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር።

117ያለ ሥጋት እቀመጥ ዘንድ ደግፈህ ያዘኝ፤

ሥርዐትህንም ዘወትር እመለከታለሁ።

118መሠሪነታቸው በከንቱ ነውና፣

ከሥርዐትህ ውጭ የሚሄዱትን ሁሉ ወዲያ አስወገድሃቸው።

119የምድርን ክፉዎች ሁሉ እንደ ጥራጊ አስወገድሃቸው፤

ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ።

120ሥጋዬ አንተን በመፍራት ይንቀጠቀጣል፤

ፍርድህንም እፈራለሁ።

ע ዐዪን

121ፍትሕና ጽድቅ ያለበትን ሠርቻለሁ፤

ለሚጨቍኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ።

122ለባሪያህ በጎነት ዋስትና ሁን፤

እብሪተኞች እንዲጨቍኑኝ አትፍቀድላቸው።

123ዐይኖቼ ማዳንህን፣

የጽድቅ ቃልህን በመጠባበቅ ደከሙ።

124ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ መጠን አድርግ፤

ሥርዐትህንም አስተምረኝ።

125እኔ ባሪያህ ነኝ፤

ምስክርነትህን ዐውቅ ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ።

126እግዚአብሔር ሆይ፤

ሕግህ እየተጣሰ ነውና፣

ጊዜው አንተ የምትሠራበት ነው።

127ስለዚህ ከወርቅ፣ ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ፣

ትእዛዞችህን ወደድሁ።

128መመሪያህ ሙሉ በሙሉ ልክ ነው አልሁ፤

ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ።

פ ፔ

129ምስክርነትህ ሁሉ ድንቅ ነው፤

ስለዚህ ነፍሴ ትጠብቀዋለች።

130የቃልህ ትርጓሜ ያበራል፤

አላዋቂዎችንም አስተዋዮች ያደርጋል።

131ትእዛዝህን ናፍቄአለሁና፣

አፌን ከፈትሁ፤ አለከለክሁም።

132ስምህን ለሚወድዱ ማድረግ ልማድህ እንደ ሆነ ሁሉ፣

ወደ እኔ ተመልሰህ ምሕረት አድርግልኝ።

133አካሄዴን እንደ ቃልህ ቀና አድርግልኝ፤

ኀጢአትም በላዬ እንዲሠለጥን አትፍቀድ።

134ትእዛዝህን መጠበቅ እንድችል፣

ከሰዎች ጥቃት ታደገኝ።

135በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፤

ሥርዐትህንም አስተምረኝ።

136ሕግህ ባለመከበሩ፤

እንባዬ እንደ ውሃ ይፈስሳል።

צ ጻዴ

137እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤

ፍርድህም ትክክል ነው።

138ምስክርነትህን በጽድቅ አዘዝህ፤

እጅግ አስተማማኝም ነው።

139ጠላቶቼ ቃልህን ዘንግተዋልና፣

ቅናት አሳረረኝ።

140ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው፤

ባሪያህም ወደደው።

141እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፤

ነገር ግን መመሪያህን አልዘነጋሁም።

142ጽድቅህ ዘላለማዊ ጽድቅ ነው፤

ሕግህም እውነት ነው።

143መከራና ሥቃይ ደርሶብኛል፤

ነገር ግን ትእዛዝህ ደስታዬ ነው።

144ምስክርነትህ ለዘላለም የጽድቅ ምስክርነት ነው፤

በሕይወት እኖር ዘንድ ማስተዋልን ስጠኝ።

ק ቆፍ

145እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ እጮኻለሁና መልስልኝ፤

ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ።

146ወደ አንተ እጣራለሁና አድነኝ፤

ምስክርነትህንም እጠብቃለሁ።

147ትረዳኝ ዘንድ ጎሕ ሳይቀድድ ተነሥቼ እጮኻለሁ፤

ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ።

148ቃልህን አሰላስል ዘንድ፣

ዐይኔ ሌሊቱን ሙሉ ሳይከደን ያድራል።

149እንደ ቸርነትህ መጠን ድምፄን ስማ፤

እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ሕግህ መልሰህ ሕያው አድርገኝ።

150ደባ የሚያውጠነጥኑ ወደ እኔ ቀርበዋል፤

ከሕግህ ግን የራቁ ናቸው።

151እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ቅርብ ነህ፤

ትእዛዞችህም ሁሉ እውነት ናቸው።

152ለዘላለም እንደ መሠረትሃቸው፣

ከጥንት ምስክርነትህ ተረድቻለሁ።

ר ሬሽ

153ሕግህን አልረሳሁምና፣ ሥቃዬን ተመልከት፤ ታደገኝም።

154ተሟገትልኝ፤ አድነኝም፤

እንደ ቃልህም ሕያው አድርገኝ።

155ሥርዐትህን ስለማይሹ፣

ድነት ከክፉዎች የራቀ ነው።

156እግዚአብሔር ሆይ፤ ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤

እንደ ሕግህ ሕያው አድርገኝ።

157የሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ ብዙዎች ናቸው፤

እኔ ግን ከምስክርህ ዘወር አላልሁም።

158ቃልህን አይጠብቁምና፣

ከዳተኞችን አይቼ አርቃቸዋለሁ።

159መመሪያህን እንዴት እንደምወድድ ተመልከት፤

እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ።

160ቃልህ በሙሉ እውነት ነው፤

ጻድቅ የሆነው ሕግህም ዘላለማዊ ነው።

ש ሲን እና ሺን

161ገዦች ያለ ምክንያት አሳደዱኝ፤

ልቤ ግን ከቃልህ የተነሣ እጅግ ፈራ።

162ትልቅ ምርኮ እንዳገኘ ሰው፣

በቃልህ ደስ አለኝ።

163ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁ፤

ሕግህን ግን ወደድሁ።

164ጻድቅ ስለ ሆነው ሕግህ፣

በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ።

165ሕግህን የሚወድዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤

ዕንቅፋትም የለባቸውም።

166እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ተስፋ አደርጋለሁ፤

ትእዛዝህንም እፈጽማለሁ።

167ነፍሴ ምስክርነትህን ትጠብቃለች፤

እጅግ እወድደዋለሁና።

168መንገዴ ሁሉ በፊትህ ግልጽ ነውና፣

ሕግህንና ምስክርነትህን እጠብቃለሁ።

ת ታው

169እግዚአብሔር ሆይ፤ ጩኸቴ ከፊትህ ይድረስ፤

እንደ ቃልህም ማስተዋልን ስጠኝ።

170ልመናዬ ከፊትህ ይድረስ፤

እንደ ቃልህም ታደገኝ።

171ሥርዐትህን አስተምረኸኛልና፣

ከንፈሮቼ ምስጋናን አፈለቁ።

172ትእዛዞችህ ሁሉ የጽድቅ ትእዛዞች ናቸውና፣

አንደበቴ ስለ ቃልህ ይዘምር።

173ትእዛዝህን መርጫለሁና፣

እጅህ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ይሁን።

174እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ናፈቅሁ፤

ሕግህም ደስታዬ ነው።

175አመሰግንህ ዘንድ በሕይወት ልኑር፤

ሕግህም ይርዳኝ።

176እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፤

ትእዛዞችህን አልረሳሁምና፣

ባሪያህን ፈልገው።