2 ዜና መዋዕል 5 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ዜና መዋዕል 5:1-14

1ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሠራው ሥራ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ አባቱ ዳዊት የቀደሰውን ብሩንና ወርቁን፣ ዕቃዎቹንም ሁሉ አምጥቶ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አኖራቸው።

ታቦቱ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ

5፥2–6፥11 ተጓ ምብ – 1ነገ 8፥1-21

2ከዚያ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን እንዲያመጡ፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የየነገዱን መሪዎች ሁሉና የእስራኤላውያንን የቤተ ሰብ አለቆች በኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 3የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ የሰባተኛው ወር በዓል በሚከበርበት ጊዜ፣ በንጉሡ ፊት ተሰበሰቡ።

4የእስራኤል ሽማግሌዎች በተሰበሰቡም ጊዜ ሌዋውያኑ ታቦቱን አነሡት፤ 5ታቦቱን፣ የመገናኛ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን የተቀደሱ ዕቃዎች ሁሉ ይዘው ወደ ላይ ወጡ፤ ሌዋውያን የሆኑ ካህናትም ተሸከሟቸው። 6ንጉሥ ሰሎሞንና በአጠገቡ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤ ስፍር ቍጥር የሌላቸውን በጎችና በሬዎች በታቦቱ ፊት ሠዉ።

7ካህናቱም የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት የቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ወደ ሆነው ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ አግብተው ከኪሩቤል ክንፍ በታች ባለው ስፍራው አኖሩት። 8ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ከታቦቱ በላይ ባለው ስፍራ ላይ ዘርግተው፣ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ሸፈኑ። 9መሎጊያዎቹም በጣም ረጃጅም ከመሆናቸው የተነሣ፣ ታቦቱ እስካለበት ድረስ ያሉት ጫፎቻቸው ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ይታዩ ነበር፤ ከመቅደሱ ውጭ ግን አይታዩም ነበር፤ ዛሬም እዚያው ቦታ ይገኛሉ። 10እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ኪዳን ባደረገ ጊዜ፣ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በውስጡ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም። 11ካህናቱም ከቤተ መቅደሱ ወጡ፤ እዚያ የነበሩት ካህናት በምድባቸው መሠረት ባይሆንም፣ ሁሉም ራሳቸውን ቀድሰው ነበር። 12መዘምራን የነበሩት ሌዋውያን ሁሉ፣ አሳፍ፣ ኤማን፣ ሄማንና ኤዶታም፣ ወንዶች ልጆቻቸውና የሥጋ ዘመዶቻቸው ሁሉ ያማረ ቀጭን በፍታ ለብሰው፣ ከመሠዊያው በስተ ምሥራቅ በኩል ቆመው ጸናጽል ይጸነጽሉ፣ በገና ይደረድሩና መሰንቆ ይመቱ ነበር፤ እነርሱም መለከት በሚነፉ አንድ መቶ ሃያ ካህናት ታጅበው ነበር። 13መለከት ነፊዎችና ዘማሪዎችም በአንድነት አንድ ድምፅ ሆነው ለእግዚአብሔር ውዳሴና ምስጋና አቀረቡ፤ በመለከት፣ በጸናጽልና በሌሎች መሣሪያዎች ታጅበውም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እግዚአብሔርን እያወደሱ፣

“እርሱ ቸር ነው፣

ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”

እያሉ ዘመሩ።

ከዚያም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በደመና ተሞላ። 14የእግዚአብሔር ክብር የአምላክን ቤተ መቅደስ ሞልቶት ስለ ነበር፣ ከደመናው የተነሣ ካህናቱ አገልግሎታቸውን ማከናወን አልቻሉም።