2 ዜና መዋዕል 33 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ዜና መዋዕል 33:1-25

የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ

33፥1-10 ተጓ ምብ – 2ነገ 21፥1-10

33፥18-20 ተጓ ምብ – 2ነገ 21፥17-18

1ምናሴ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አምሳ አምስት ዓመት ገዛ። 2እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳድዶ ያስወጣቸውን ሕዝቦች አስጸያፊ ልማድ በመከተልም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። 3አባቱ ሕዝቅያስ ያጠፋቸውን የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች መልሶ ሠራ፤ ለበኣሊም መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ዐምዶች ሠራ፤ ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊትም ሰገደ፤ አመለካቸውም። 4እግዚአብሔር፣ “ስሜ ለዘላለም በኢየሩሳሌም ይኖራል” ባለበት በእግዚአብሔር ቤተ መቀደስ መሠዊያዎችን ሠራ። 5በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ላይ፣ ለሁሉም የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት መሠዊያዎችን ሠራ። 6በሄኖም ልጅ ሸለቆ ወንዶች ልጆቹን በእሳት ሠዋ33፥6 ወይም ወንዶች ልጅቹን ገደለ፤ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቍጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ።

7ያበጀውን የተጠረበ ምስል ወስዶም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አኖረ፤ ስለዚህም ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን እንዲህ ብሎ ነበር፤ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ፤ 8በሙሴ አማካይነት ያዘዝኋቸውን ሕግጋቴን፣ ደንቦቼንና ሥርዐቶቼን ሁሉ በጥንቃቄ ይፈጽሙ እንጂ፣ ለቀድሞ አባቶቻችሁ ከሰጠኋቸው ምድር የእስራኤላውያን እግር ከእንግዲህ ለቅቆ እንዲወጣ አላደርግም።” 9ምናሴ ግን እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ የባሰ ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ ዘንድ፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ አሳተ።

10እግዚአብሔር ለምናሴና ለሕዝቡ ተናገረ፤ እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም። 11ስለዚህ እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሰራዊት አዛዦች አመጣባቸው፤ እነርሱም በምናሴ አፍንጫ መንጠቆ አገቡበት፤ በናስ ሰንሰለት አስረውም ወደ ባቢሎን ወሰዱት። 12በተጨነቀም ጊዜ የአምላኩን የእግዚአብሔርን በጎነት ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ። 13ወደ እርሱም በጸለየ ጊዜ፣ በጭንቀት ልመናው ራርቶለት እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰማው። ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ መንግሥቱም መለሰው፤ ምናሴም እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዐወቀ።

14ከዚህ በኋላ በሸለቆው ውስጥ ከሚገኘው ከግዮን ምንጭ ምዕራብ አንሥቶ እስከ ዓሣ በር መግቢያ ድረስ ያለውን የዳዊትን ከተማ የውጭውን ቅጥር፣ የዖፊልን ኰረብታ እንዲከብብ በማድረግ፣ ይበልጥ ከፍ አድርጎ እንደ ገና ሠራው። በተመሸጉትም የይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጦር አዛዦችን አኖረ።

15እንግዶች አማልክትንና ጣዖታቱን ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስወገደ፤ በቤተ መቅደሱ ኰረብታና በኢየሩሳሌም የሠራቸውንም መሠዊያዎች ሁሉ አራቀ፤ ከከተማዪቱም ውጭ ጣላቸው። 16ከዚያም የእግዚአብሔርን መሠዊያ ዐደሰ፤ በላዩም የኅብረት መሥዋዕትና የምስጋና መሥዋዕት አቀረበ፤ ይሁዳም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ አዘዘ። 17ሕዝቡ ግን በኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች መሠዋቱን ቢቀጥልም፣ የሚሠዋው ግን ለአንዱ አምላክ ለእግዚአብሔር ብቻ ነበር።

18በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባር፣ ወደ አምላኩ ያቀረበው ጸሎቱና ባለ ራእዮች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም የነገሩት ቃል በእስራኤል33፥18 በዜና መዋዕሉ መጽሐፍ ተደጋግሞ እንደ ተጠቀሰው ይህ ይሁዳ ነው። ነገሥታት ታሪክ ተጽፏል። 19ጸሎቱና እግዚአብሔር ራርቶ ልመናውን እንዴት እንደ ተቀበለው፣ ኀጢአቱ ሁሉና ታማኝነቱን ማጕደሉ፣ እንደዚሁም ራሱን ከማዋረዱ በፊት ያሠራቸው የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ያቆማቸው የአሼራ ምስል ዐምዶችና ጣዖታት ሁሉ በባለ ራእዮች መዛግብት ተጽፈዋል። 20ምናሴም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በቤተ መንግሥቱም ተቀበረ። ልጁም አሞን በእርሱ ፈንታ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ አሞን

33፥21-25 ተጓ ምብ – 2ነገ 21፥19-20

21አሞን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሁለት ዓመት ገዛ። 22አባቱ ምናሴ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ አሞንም ምናሴ ያሠራቸውን ጣዖታት ሁሉ አመለከ፤ መሥዋዕትም አቀረበላቸው። 23አሞን በእግዚአብሔር ፊት ራሱን እንዳዋረደ እንደ አባቱ እንደ ምናሴ ራሱን አላዋረደም፤ ነገር ግን በበደል ላይ በደል እየጨመረ ሄደ።

24የአሞን ሹማምት በእርሱ ላይ አሢረው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት። 25ከዚያም ያገሩ ሕዝብ በንጉሡ አሞን ላይ ያሤሩትን ሁሉ ገደሉ፤ ልጁን ኢዮስያስንም በእርሱ ፈንታ አነገሡት።