2 ነገሥት 10 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ነገሥት 10:1-36

የአክዓብ ቤተ ሰቦች ተገደሉ

1በዚህ ጊዜ አክዓብ በሰማርያ ሰባ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ስለዚህ ኢዩ ደብዳቤ ጽፎ ለኢይዝራኤል ሹማምት፣10፥1 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ነገር ግን እንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞችና የቩልጌት ቅጅ፣ የከተማዪቱ ይላሉ። ለሽማግሌዎችና የአክዓብን ልጆች ለሚያሳድጉ ሞግዚቶች ወደ ሰማርያ ላከ፤ መልእክቱም እንዲህ የሚል ነበር፤ 2“የጌታችሁ ልጆች ከእናንተ ጋር ስለ ሆኑ፣ ሠረገሎችና ፈረሶች፣ የተመሸገች ከተማና መሣሪያም ስላላችሁ፣ ይህ ደብዳቤ እንደ ደረሳችሁ ወዲያውኑ 3ከጌታችሁ ልጆች መካከል ብልጫ ያለውንና ተገቢ ነው የምትሉትን መርጣችሁ በአባቱ ዙፋን አስቀምጡት። ከዚያም ስለ ጌታችሁ ቤት ተዋጉ።”

4እነርሱ ግን እጅግ ፈርተው ነበርና፣ “ሁለት ነገሥታት ሊቋቋሙት ያልቻሉትን ሰው እኛ እንዴት ልንቋቋመው እንችላለን?” አሉ።

5ስለዚህ የቤተ መንግሥቱ አዛዥ፣ የከተማዪቱ ገዥ፣ ሽማግሌዎችና የልጆቹ ሞግዚቶች፣ “እኛ የአንተው አገልጋዮች ነን፤ ትእዛዝህን ሁሉ እንፈጽማለን፤ እኛ ማንንም አናነግሥም፤ ደስ የሚያሰኝህን ሁሉ አንተው አድርግ” በማለት ይህን መልእክት ለኢዩ ላኩ። 6ከዚያም ኢዩ፣ “እንግዲህ የእኔ ወገን ከሆናችሁና ከታዘዛችሁኝ የጌታችሁን ልጆች ራስ ቈርጣችሁ ነገ በዚህ ሰዓት ይዛችሁልኝ ወደ ኢይዝራኤል እንድትመጡ” ሲል ደግሞ ጻፈላቸው።

በዚህም ጊዜ ሰባው የንጉሡ ልጆች በከተማዪቱ ውስጥ ታዋቂ በሆኑ አሳዳጊዎቻቸው ዘንድ ነበሩ። 7ደብዳቤውም በደረሳቸው ጊዜ፣ ሰዎቹ ሰባውን ልዑላን በሙሉ ወስደው ገደሏቸው። ራሳቸውንም በቅርጫት አድርገው ኢዩ ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ላኩ። 8መልእክተኛው እንደ ደረሰም፣ ለኢዩ፣ “የንጉሡን ልጆች ራስ አምጥተዋል” ብሎ ነገረው። ከዚያም ኢዩ፣ “በከተማዪቱ መግቢያ በር ላይ ሁለት ቦታ ከምራችሁ እስከ ነገ ጧት ድረስ አቈዩአቸው” ብሎ አዘዘ።

9በማግስቱም ጧት ኢዩ ወጥቶ በሕዝቡ ሁሉ ፊት በመቆም እንዲህ አለ፤ “እናንተ ንጹሓን ናችሁ፤ ጌታዬን ያሤርሁበትና የገደልሁት እኔ ነኝ። እነዚህን ሁሉ ግን የፈጃቸው ማን ነው? 10እንግዲህ እግዚአብሔር በአክዓብ ቤት ላይ ከተናገረው ቃል አንዲቱ እንኳ በምድር ላይ ወድቃ እንደማትቀር ዕወቁ። እግዚአብሔር በባሪያው በኤልያስ የተናገረውን ፈጽሟል።” 11ስለዚህ ኢዩ ከአክዓብ ቤት የቀረውን ሁሉ፣ ታላላቆቹን ሰዎች በሙሉ፣ የቅርብ ወዳጆቹንና ካህናቱን አንድም ሳይቀር በኢይዝራኤል ገደላቸው።

12ከዚያም ኢዩ ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ ቤት ኤከድ ወደ ተባለው የበግ ጠባቂዎችም ቤት ሲደርስ፣ 13ከይሁዳ ንጉሥ ከአካዝያስ ሥጋ ዘመዶች ጥቂቶቹን አግኝቶ፣ “እናንተ እነማን ናችሁ?” ሲል ጠየቃቸው፤

እነርሱም፣ “እኛ የአካዝያስ ሥጋ ዘመዶች ነን፤ ንጉሣዊውን ቤተ ሰብና የእቴጌዪቱን ልጆች ለመጠየቅ ወደዚህ ወርደን መጥተናል” አሉ።

14እርሱም፣ “ከነሕይወታቸው ያዟቸው!” ሲል አዘዘ፤ ስለዚህ ከነሕይወታቸው ወስደው በቤት ኤከድ ጕድጓድ አጠገብ አርባ ሁለቱን ሰዎች ገደሏቸው፤ አንድ እንኳ አላስቀረም።

15ከዚያም ተነሥቶ ሲሄድ የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ወደ እርሱ ሲመጣ መንገድ ላይ አገኘው። ኢዩም ሰላምታ ሰጥቶት “ልቤ ለልብህ ታማኝ የሆነውን ያህል የአንተስ ልብ ለልቤ እንዲሁ ታማኝ ነውን?” ሲል ጠየቀው።

ኢዮናዳብም፣ “አዎን፤ ነው!” ብሎ መለሰ።

ኢዩም፣ “እንግዲያውስ እጅህን ስጠኝ” አለው። እጁንም ሰጠው፤ ከዚያም ኢዩ ደግፎ ወደ ሠረገላው አወጣው።

16ኢዩም፣ “በል አብረን እንሂድና ለእግዚአብሔር ያለኝን ቅናት እይልኝ” አለው፤ ከዚያም በሠረገላው ይዞት ሄደ።

17ኢዩ ወደ ሰማርያ በደረሰ ጊዜ፣ ከአክዓብ ቤተ ሰብ በዚያ የቀረውን ሁሉ ገደለ። ለነቢዩ ለኤልያስ በተነገረውም የእግዚአብሔር ቃል መሠረት አጠፋቸው።

የበኣል አገልጋዮች ተገደሉ

18ከዚያም ኢዩ ሕዝቡን ሁሉ በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አለ፤ “አክዓብ በኣልን ያገለገለው በጥቂቱ ነው፤ ኢዩ ግን ይበልጥ ያገለግለዋል። 19አሁንም የበኣልን ነቢያት ሁሉ አገልጋዮቹንና ካህናቱንም በሙሉ ጥሩልኝ። ለበኣል ትልቅ መሥዋዕት ስለማቀርብ አንድ ሰው እንኳ እንዳይቀር። የማይመጣ ሰው ቢኖር ግን በሕይወት አይኖርም” ኢዩ ግን ይህን ማድረጉ የበኣልን አገልጋዮች ለማጥፋት ተንኰል መፍጠሩ ነበር።

20ኢዩም፣ “ለበኣል ክብር ጉባኤ ጥሩ” አለ፤ እነርሱም ይህንኑ ለሕዝቡ አስታወቁ። 21ከዚያም በመላው እስራኤል መልእክት ላከ፤ የበኣል አገልጋዮች በሙሉ መጡ፤ ማንም አልቀረም፤ ሁሉም ወደ በኣል ቤተ ጣዖት ገቡ፤ የበኣል ቤተ ጣዖት ዳር እስከ ዳር ሞላ። 22ኢዩም የልብስ ቤቱን ኀላፊ፣ “ለበኣል አገልጋዮች ሁሉ አልባሳት አውጣ” አለው፤ እርሱም አልባሳቱን አወጣላቸው።

23ከዚያም ኢዩ ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ጋር ወደ በኣል ቤተ ጣዖት ገባ። የበኣልንም አገልጋዮች፣ “እንግዲህ የበኣል አገልጋዮች ብቻ እንጂ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እዚህ አብረዋችሁ አለመኖራቸውን አረጋግጡ” አላቸው። 24ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት ለማቅረብ ገቡ። በዚህ ጊዜም ኢዩ፣ “በእጃችሁ አሳልፌ ከሰጠኋችሁ ሰዎች አንድ እንኳ እንዲያመልጥ ያደረገ በገመዱ ይገባበታል” ብሎ በማስጠንቀቅ ውጭ ሰማንያ ሰዎች አዘጋጅቶ ነበር።

25ኢዩ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቦ እንዳበቃ ጠባቂዎቹንና የጦር አለቆቹን፣ “ግቡና ግደሏቸው፤ ማንም እንዳያመልጥ” ሲል አዘዘ። እነርሱም በሰይፍ ፈጇቸው፤ ጠባቂዎቹና የጦር ሹማምቱም ሬሳውን በሙሉ ወደ ውጭ አውጥተው ጣሉ። ከዚያም ወደ ውስጠኛው የበኣል ቤተ ጣዖት ገቡ። 26ከድንጋይ የተሠሩትንም ማምለኪያ ምስሎች ከበኣል ቤተ ጣዖት አውጥተው አቃጠሉ። 27የበኣልን ማምለኪያ ምስል ቀጠቀጡ፤ የበኣልንም ቤተ አምልኮ አፈረሱ፤ ይህንም ሕዝቡ እስከ ዛሬ ድረስ የኵስ መጣያው አድርጎታል።

28በዚህ ሁኔታም ኢዩ የበኣልን አምልኮ ከእስራኤል አስወገደ። 29ይሁን እንጂ ኢዩ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም፣ በቤቴልና በዳን የወርቅ ጥጃዎች እንዲያመልኩ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልራቀም።

30እግዚአብሔርም ኢዩን፣ “በፊቴ መልካም የሆነውን ነገር ስላደረግህና በአክዓብም ቤት ላይ እንዲደርስ በልቤ ያለውን ሁሉ ስለፈጸምህ፣ ዘርህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣል” አለው።

31ነገር ግን ኢዩ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ሕግ በፍጹም ልቡ ለመጠበቅ ጥንቃቄ አላደረገም፤ ኢዮርብዓም፣ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልራቀምና።

32በዚያ ዘመን እግዚአብሔር የእስራኤልን ምድር መቀናነስ ጀመረ። አዛሄልም እስራኤልን ዳር እስከ ዳር መታ። 33ይኸውም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን የገለዓድን ምድር ሁሉ ሲሆን፣ ይህም በአርኖን ወንዝ አጠገብ ካለው ከአሮዔር አንሥቶ የጋድን፣ የሮቤልንና የምናሴን አገር ገለዓድንና ባሳንን ነበር።

34የቀረው በኢዩ ዘመነ መንግሥት የሆነው፣ ያደረገውም ሁሉ፣ ያከናወነውም ሥራ በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

35ኢዩ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያ ቀበሩት። ልጁ ኢዮአካዝም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። 36ኢዩ በሰማርያ ተቀምጦ በእስራኤል ላይ የነገሠው ሃያ ስምንት ዓመት ነበር።