2 ቆሮንቶስ 5 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ቆሮንቶስ 5:1-21

ሰማያዊ መኖሪያችን

1መኖሪያችን የሆነው ምድራዊ ድንኳን ቢፈርስም፣ በሰው እጅ ያልተሠራ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሆነ ዘላለማዊ ቤት በሰማይ እንዳለን እናውቃለን። 2እስከዚያው ግን የሰማዩን መኖሪያችንን ለመልበስ እየናፈቅን እንቃትታለን፤ 3በርግጥ ከለበስነው ራቍታችንን ሆነን አንገኝም። 4በዚህ ድንኳን እስካለን ድረስ ከብዶን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ሟች የሆነው በሕይወት እንዲዋጥ ሰማያዊውን መኖሪያችንን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንፈልግም። 5ለዚህ ዐላማ ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው፤ ሊመጣ ላለው ዋስትና እንዲሆነን መንፈሱን መያዣ አድርጎ የሰጠንም እርሱ ነው።

6ስለዚህ ሁልጊዜ በመታመን እንኖራለን፤ በሥጋ እስካለን ድረስ ከጌታ ርቀን እንደምንገኝ እናውቃለን፤ 7ምክንያቱም የምንኖረው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም። 8ከሥጋ ተለይተን ከጌታ ጋር መኖርን እንደምንመርጥ ርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ። 9ስለዚህ በሥጋ ብንኖርም ወይም ከሥጋ ብንለይም ዐላማችን እርሱን ደስ ማሰኘት ነው። 10ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና፤ እያንዳንዱም ሰው በሥጋው ለሠራው በጎ ወይም ክፉ ሥራ ተገቢውን ዋጋ ይቀበላል።

የማስታረቅ አገልግሎት

11እንግዲህ ጌታን መፍራት ምን ማለት እንደ ሆነ ስለምናውቅ፣ ሰዎች የምንናገረውን እንዲቀበሉ ለማድረግ እንጥራለን። የእኛ ማንነት በእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጠ ነው፤ ደግሞም በኅሊናችሁ ዘንድ ግልጽ ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። 12ይህን የምለው ራሳችንን በእናንተ ፊት እንደ ገና ለማመስገን ሳይሆን፣ በእኛ እንድትመኩ ዕድል ልሰጣችሁ ነው፤ ይኸውም በውጭ በሚታየው ለሚመኩት እንጂ በልብ ውስጥ ባለው ነገር ለማይመኩ መልስ መስጠት እንድትችሉ ነው። 13ከአእምሮ ውጭ ብንሆን ለእግዚአብሔር ብለን ነው፤ ባለ አእምሮም ብንሆን ለእናንተ ነው። 14የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ ምክንያቱም አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ ርግጠኞች ሆነናል፣ ከዚህም የተነሣ ሁሉ ሞተዋል። 15በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ።

16ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በውጫዊ ነገር አንመዝንም፤ ከዚህ ቀደም ክርስቶስን በዚህ መልክ መዝነነው ነበር፤ ከእንግዲህ ግን እንደዚህ አናደርግም። 17ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር ዐልፏል፤ እነሆ፤ አዲስ ሆኗል። 18ይህ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በክርስቶስ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታረቀን፤ የማስታረቅንም አገልግሎት ሰጠን፤ 19እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር ሲያስታርቅ የሰዎችን በደል አይቈጥርባቸውም ነበር፤ ለእኛም ደግሞ የማስታረቅ ቃል ሰጠን። 20ስለዚህ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ እግዚአብሔርም በእኛ አማካይነት ጥሪውን ያቀርባል፤ እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን በክርስቶስ እንለምናችኋለን። 21እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኀጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለ እኛ ኀጢአት5፥21 ወይም የኀጢአት መሥዋዕት አደረገው።