2 ቆሮንቶስ 3 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ቆሮንቶስ 3:1-18

1እንደ ገና ራሳችንን ልናመሰግን እንጀምራለንን? ወይስ እንደ ሌሎቹ ለእናንተ ወይም ከእናንተ የተጻፈ የምስጋና ደብዳቤ ያስፈልገን ይሆንን? 2እናንተ እኮ ሰው ሁሉ የሚያውቃችሁና የሚያነብባችሁ በልባችን ላይ የተጻፋችሁ ደብዳቤዎቻችን ናችሁ፤ 3እናንተ በቀለም ሳይሆን በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ፣ በድንጋይ ጽላት ላይ ሳይሆን በሰው ልብ ጽላት ላይ የተጻፋችሁና በእኛ የተገለገላችሁ የክርስቶስ ግልጽ ደብዳቤ ናችሁ።

4በክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ይህን የመሰለ ነው፤ 5ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፣ በራሳችን ብቃት ከእኛ ነው የምንለው አንዳች ነገር የለንም። 6እርሱም በፊደል ላይ ሳይሆን በመንፈስ ላይ የተመሠረተውን የአዲሱ ኪዳን አገልጋዮች እንድንሆን ብቁዎች አደረገን፤ ምክንያቱም ፊደል ይገድላል፤ መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል። 7እንግዲህ እስራኤላውያን ከፊቱ ክብር የተነሣ የሙሴን ፊት ትኵር ብለው ማየት እስኪሳናቸው ድረስ፣ ያ ከጊዜ በኋላ የሚያልፈውና በድንጋይ ላይ በፊደል የተቀረጸው የሞት አገልግሎት በክብር ከመጣ፣ 8ታዲያ፣ የመንፈስ አገልግሎት እንዴት ከዚያ የላቀ ክብር አይኖረውም? 9ሰዎችን የሚኰንነው አገልግሎት የከበረ ከሆነ፣ የሚያጸድቀው አገልግሎት የቱን ያህል ይበልጥ የከበረ ይሆን! 10ከዚህ በፊት ክቡር የነበረው የላቀ ክብር ካለው ጋር ሲወዳደር ክብር የሌለው ሆኗል። 11የሚያልፈው ያን ያህል ክብር ከነበረው፣ ጸንቶ የሚኖረውማ እንዴት የላቀ ክብር አይኖረውም?

12እንግዲህ ይህን የመሰለ ተስፋ ስላለን፣ በድፍረት እንናገራለን። 13እስራኤላውያን የፊቱ ማንጸባረቅ እየጠፋ ሲሄድ መጨረሻውን እንዳይመለከቱ፣ ፊቱን በጨርቅ እንደ ሸፈነው እንደ ሙሴ አይደለንም። 14ነገር ግን ብሉይ ኪዳን በተነበበ ቍጥር፣ ያ መሸፈኛ እስከ ዛሬ ድረስ ስላልተወገደ ልቡናቸው እንደ ደነዘዘ ነው፤ መሸፈኛው አሁንም አልተወገደም፤ የሚወገደው በክርስቶስ ብቻ ነውና። 15እስከ ዛሬም ድረስ የሙሴ መጻሕፍት በተነበቡ ቍጥር መሸፈኛው ልቡናቸውን ይሸፍናል። 16ነገር ግን አንድ ሰው ወደ ጌታ ዘወር ሲል መሸፈኛው ይወገዳል። 17ጌታ መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ ነጻነት አለ። 18እኛም ሁላችን ባልተሸፈነ ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያንጸባረቅን፣3፥18 ወይም የጌታን ክብር በጥሞና እያሰላሰልን የእርሱን መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን፤ ይህም የሚሆነው መንፈስ ከሆነ ጌታ ነው።