2 ቆሮንቶስ 12 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ቆሮንቶስ 12:1-21

ጳውሎስ ያየው ራእይና የተሰጠው መውጊያ

1በመመካት የሚገኝ ጥቅም ባይኖርም፣ መመካት ካስፈለገ ከጌታ ወደ ተቀበልሁት ራእይና መገለጥ አመራለሁ። 2ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ የተነጠቀ በክርስቶስ አንድ ሰው ዐውቃለሁ፤ የተነጠቀው በሥጋ ይሁን ወይም ከሥጋ ውጭ አላውቅም፤ እግዚአብሔር ግን ያውቃል። 3ይህ ሰው በሥጋ ይሁን ወይም ከሥጋ ውጭ እኔ አላውቅም፤ እግዚአብሔር ግን ያውቃል፤ 4እርሱም ወደ ገነት እንደ ተነጠቀ፣ በዚያም በሰው አንደበት ሊገለጥ የማይችል፣ ሰውም እንዲናገረው ያልተፈቀደለት ነገር ሰማ። 5እንደዚህ ስላለው ሰው እመካለሁ፤ ስለ ራሴ ግን ከደካማነቴ በስተቀር አልመካም። 6መመካት ብፈልግ እንኳ እንደ ሞኝ መቈጠር የለብኝም፤ ምክንያቱም የምናገረው እውነት ነው። ነገር ግን ማንም ስለ እኔ ከሚያየውና ከሚሰማው በላይ እንዳይገምተኝ ከመመካት እቈጠባለሁ።

7ከዚህ ታላቅ መገለጥ የተነሣ እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፣ እርሱም የሚያሠቃየኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ። 8ይህ ነገር ከእኔ እንዲወገድልኝ፣ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንሁት፤ 9እርሱ ግን፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ። 10ስለ ክርስቶስ በድካም፣ በስድብ፣ በመከራ፣ በስደትና በጭንቀት ደስ የምሰኘው ለዚህ ነው፤ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና።

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የነበረው ጭንቀት

11በመመካቴ ሞኝ ሆኛለሁ፤ ለዚህም ያበቃችሁኝ እናንተ ናችሁ፤ ስለ እኔ መመስከር የሚገባችሁ እናንተ ነበራችሁ። ደግሞም እኔ ከምንም የማልቈጠር ብሆንም፣ “ታላላቅ ሐዋርያት” ከሚባሉት በምንም አላንስም። 12የእውነተኛ ሐዋርያ ምልክቶች በመካከላችሁ ተደርገዋል፤ እነርሱም በትዕግሥት መጽናት፣ ምልክቶች፣ ድንቅ ነገሮችና ታምራት ናቸው። 13በእናንተ ላይ ሸክም ካለመሆኔ በቀር፣ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በምን አነሳችሁ? ይህን በደሌን ይቅር በሉኝ።

14ወደ እናንተ ለመምጣት ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ስመጣ በምንም ነገር ሸክም አልሆንባችሁም፤ እኔ እናንተን እንጂ ከእናንተ ምንም አልፈልግምና፤ ደግሞም ወላጆች ለልጆች ገንዘብ ያከማቻሉ እንጂ ልጆች ለወላጆች አያከማቹም። 15እኔ ግን ስለ እናንተ ያለኝን ሁሉ ራሴንም ጭምር ብሰጥ ደስ ይለኛል፤ ታዲያ እኔ የምወድዳችሁ ይህን ያህል ከሆነ፣ እናንተ የምትወድዱኝ በጥቂቱ ነውን? 16የሆነው ሆኖ ሸክም አልሆንሁባችሁም፤ ነገር ግን በተንኰልና በዘዴ ያጠመድኋችሁ ሳይመስላችሁ አልቀረም! 17ለመሆኑ ወደ እናንተ በላክኋቸው ሰዎች አማካይነት በአንዱ እንኳ በዘበዝኋችሁን? 18ቲቶ ወደ እናንተ እንዲመጣ ለመንሁት፤ ወንድማችንንም ከእርሱ ጋር ላክሁት። ቲቶ በዘበዛችሁን? ከእርሱ ጋር በአንድ መንፈስ አልተመላለስንምን? አካሄዳችንስ አንድ አልነበረምን?

19እስከ አሁን ድረስ በእናንተ ፊት ራሳችንን ስንከላከል የኖርን ይመስላችኋልን? በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት እንናገራለን፤ ደግሞም ወዳጆች ሆይ፤ ይህን ሁሉ የምናደርገው እናንተን ለማነጽ ነው። 20ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ፣ እኔ እንደምፈልገው ሆናችሁ ላላገኛችሁ እችላለሁ ወይም እናንተ እንደምትፈልጉኝ ሆኜ ላታገኙኝ ትችላላችሁ ብዬ እፈራለሁ፤ ምናልባትም በመካከላችሁ ጥል፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ አድመኝነት፣ ስም ማጥፋት፣ ሐሜት፣ እብሪትና ሁከት ይኖራል ብዬ እሠጋለሁ። 21ዳግመኛም ስመጣ አምላኬ በእናንተ ፊት ያዋርደኝ ይሆን ብዬ እፈራለሁ፤ ይኸውም ብዙዎች ከዚህ በፊት ስለ ሠሩት ኀጢአትና ስለ ፈጸሙትም ርኩሰት፣ ዝሙትና መዳራት ንስሓ ሳይገቡ ቀርተው እንዳላዝን ነው።