2 ሳሙኤል 14 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ሳሙኤል 14:1-33

አቤሴሎም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ

1የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ አቤሴሎምን እንደ ናፈቀ ተረዳ። 2ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ቴቁሔ፤ ሰው ልኮ አንዲት ብልኅ የሆነች ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፤ “ሐዘንተኛ በመምሰል የሐዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይት አትቀቢ፤ ለሞተ ሰው ብዙ ጊዜ እንዳዘነች ሴት መስለሽም ታዪ። 3ከዚያም ወደ ንጉሡ ሄደሽ እንዲህ በዪው።” ከዚያም ኢዮአብ የምትናገራቸውን ቃላት ነገራት።

4የቴቁሔዪቱም ሴት ወደ ንጉሡ ገብታ፣14፥4 ብዙ የዕብራይስጥ ቅጆች፣ የሰብዓ ሊቃናት፣ የቩልጌትና የሱርስት ትርጕሞች፣ ሄዳ ይላሉ፤ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች ግን፣ ለንጉሡ ተናገረች ይላሉ። በንጉሡ ፊት ወደ መሬት በግምባሯ ተደፍታ እጅ በመንሣት አክብሮቷን ከገለጠች በኋላ፣ “ንጉሥ ሆይ! እርዳኝ” አለች።

5ንጉሡም፣ “ችግርሽ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃት።

እርሷም እንዲህ አለች፤ “እኔ በርግጥ ባሌ የሞተብኝ መበለት ነኝ፤ 6እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ ገላጋይም ስላልነበረ፣ አንዱ ሌላውን መትቶ ገደለው። 7እነሆ ቤተ ዘመዱ ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሥተው፣ ‘ወንድሙን ስለ ገደለ እንገድለዋለንና ወንድሙን የገደለውን ሰው አሳልፈሽ ስጪን፣ ከዚያም ወራሽ አልባ ትሆኛለሽ’ ይሉኛል፤ ስለዚህ የቀረኝን አንዱን መብራቴን አጥፍተው፣ ባሌን በምድር ላይ ያለ ስምና ያለ ዘር ሊያስቀሩት ነው።”

8ንጉሡም ሴቲቱን፣ “አንቺ ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ ስለ ጕዳይሽ አስፈላጊውን ትእዛዝ እሰጣለሁ” አላት። 9ነገር ግን የቴቁሔዪቱም ሴት፣ “ንጉሥ ጌታዬ፣ በደሉ በእኔና በአባቴ ቤተ ሰብ ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ከበደል የነጹ ይሁኑ” አለች።

10ንጉሡም፣ “ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢናገርሽ እኔ ዘንድ አምጪው፤ ዳግም አያስቸግርሽም” ሲል መለሰላት።

11እርሷም፣ “ደም ተበቃዮቹ ልጄን በማጥፋት የባሰ ጕዳት እንዳያደርሱ፣ ንጉሡ አምላኩን እግዚአብሔርን ይለምን” አለች።

ንጉሡም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ከልጅሽ ራስ ላይ አንዲት ጠጕር እንኳ አትነካም” አላት።

12ከዚያም ሴቲቱ፣ “እኔ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሡ አንዲት ቃል እንድናገር ፍቀድልኝ” አለችው። እርሱም፣ “እሺ ተናገሪ” አላት።

13ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለችው፣ “እንዲህ ያለውን ነገር በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ያሰብኸው ለምንድን ነው? ንጉሡ ከአገር የተሰደደውን ልጁን አልመለሰውም፤ ታዲያ ይህን ሲናገር በራሱ ላይ መፍረዱ አይደለምን? 14በመሬት ላይ የፈሰሰ ውሃ እንደማይታፈስ ሁሉ፣ እኛም እንደዚሁ እንሞታለን፤ እግዚአብሔር ግን ከአገር የተሰደደ ሰው ከእርሱ እንደ ራቀ በዚያው እንዳይቀር የሚመለስበትን ሁኔታ ያመቻቻል እንጂ ሕይወቱ እንድትጠፋ አይፈቅድም።

15“አሁንም ወደዚህ የመጣሁት ሕዝቡ ስላስፈራኝ ይህንኑ ለንጉሥ ጌታዬ ለመንገር ነው። እኔም አገልጋይህ ይህን አሰብሁ፤ ‘ለንጉሡ እነግረዋለሁ፤ ምናልባትም አገልጋዩ የጠየቀችውን ይፈጽምላት ይሆናል፤ 16እግዚአብሔር ከሰጠን ርስት እኔንም ልጄንም ሊነቅለን ከተነሣው ሰው እጅ ንጉሡ አገልጋዩን ሊታደግ ይፈቅድ ይሆናል።’

17“አሁንም አገልጋይህ፤ ‘ንጉሥ ጌታዬ በጎውንና ክፉውን በመለየት እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለሆነ፣ የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኝ፤ እግዚአብሔር አምላክህም ካንተው ጋር ይሁን’ ትላለች።”

18ከዚያም ንጉሡ ሴቲቱን፣ “እኔም ለምጠይቅሽ ነገር አንቺም መልሱን አትደብቂኝ” አላት።

ሴቲቱም፣ “ንጉሥ ጌታዬ፤ እሺ ይናገር” አለችው።

19ንጉሡም፣ “በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ የለበትምን?” ሲል ጠየቃት።

ሴቲቱም መልሳ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከተናገረው ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም የሚል ማንም የለም። አዎን ይህን እንዳደርግ ያዘዘኝና ይህም ሁሉ ቃል በእኔ በአገልጋይህ አንደበት እንዲነገር የላከኝ አገልጋይህ ኢዮአብ ነው። 20አገልጋይህ ኢዮአብ ይህን ያደረገውም ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ ሲል ነው፤ ነገር ግን ጌታዬ የእግዚአብሔርን መልአክ ጥበብ የመሰለ ጥበብ ስላለው፣ በምድሪቱ ላይ የሚሆነውን ነገር ሁሉ ያውቃል።”

21ንጉሡም ኢዮአብን፣ “መልካም ነው፤ ፈቅጃለሁ፤ ሂድና ወጣቱን አቤሴሎምን መልሰህ አምጣው” አለው።

22ኢዮአብም አክብሮቱን ለንጉሡ ለመግለጥ ወደ መሬት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡንም ባረከ፣ ኢዮአብም በመቀጠል፣ “ንጉሡ የአገልጋዩን ልመና ስለ ተቀበለው፣ ባሪያህ በፊትህ ሞገስ ማግኘቱን ዛሬ ለማወቅ ችሏል” አለ። 23ከዚያም ኢዮአብ ወደ ጌሹር ሄዶ አቤሴሎምን ወደ ኢየሩሳሌም መልሶ አመጣው። 24ንጉሡ ግን፣ “እዚያው እቤቱ ይሂድ፤ ዐይኔን ማየት የለበትም” አለ። ስለዚህም አቤሴሎም ወደ ቤቱ ሄደ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም።

25መቼም በመልኩ ማማር አቤሴሎምን የሚያህል አንድም ሰው በመላው እስራኤል አልነበረም፤ ከራስ ጠጕሩ እስከ እግር ጥፍሩ የሚወጣለት እንከን አልነበረም። 26የራስ ጠጕሩ ሲከብደው በዓመት አንድ ጊዜ ይቈርጠው ነበር፤ የተቈረጠውን በሚመዝነው ጊዜ ክብደቱ በቤተ መንግሥቱ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል14፥26 2.3 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ይሆን ነበር።

27አቤሴሎም ሦስት ወንዶች ልጆችና ትዕማር የተባለች አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፤ ሴት ልጁም በጣም ውብ ነበረች።

28አቤሴሎም የንጉሡን ዐይን ሳያይ ሁለት ዓመት በኢየሩሳሌም ኖረ። 29ከዚያም አቤሴሎም ወደ ንጉሡ እንዲሄድለት ኢዮአብን አስጠራው፤ ኢዮአብ ግን ወደ እርሱ መምጣት አልፈለገም፤ ለሁለተኛ ጊዜም ላከበት፤ ኢዮአብ አሁንም መምጣት አልፈለገም። 30ከዚያም አቤሴሎም ለአገልጋዮቹ “ተመልከቱ የኢዮአብ ዕርሻ የሚገኘው ከእኔ ዕርሻ አጠገብ ነው፤ በዕርሻው ላይ የገብስ አዝመራ አለው፤ ሄዳችሁም እሳት ልቀቁበት” አላቸው። ስለዚህ የአቤሴሎም አገልጋዮች ሄደው የኢዮአብን ዕርሻ በእሳት አቃጠሉት።

31ከዚያም ኢዮአብ ወደ አቤሴሎም ቤት ሄደ፣ “አገልጋዮችህ ለምንድን ነው ዕርሻዬን ያቃጠሉት?” ብሎ ጠየቀው።

32አቤሴሎምም፣ ኢዮአብን፣ “ከጌሹር ለምን መጣሁ? ‘ለእኔ እስካሁንም እዚያው ብሆን ይሻለኝ ነበር ብሏል ብለህ እንድትነግርልኝ ወደ ንጉሡ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ና’ ብዬ አስጠራሁህ፤ አሁንም ቢሆን፤ የንጉሡን ዐይን ማየት እፈልጋለሁ፤ ምንም ዐይነት በደል ከተገኘብኝ ይግደለኝ” አለው።

33ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ሄዶ ይህንኑ ነገረው። ከዚያም ንጉሡ አቤሴሎምን አስጠራው፤ እርሱም መጥቶ በንጉሡ ፊት በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።