2 ሳሙኤል 13 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ሳሙኤል 13:1-39

አምኖን ትዕማርን ደፈረ

1የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ትዕማር የምትባል ቈንጆ እኅት ነበረችው፤ እርሷንም የዳዊት ልጅ አምኖን ወደዳት።

2አምኖን እኅቱን ትዕማርን ከማፍቀሩ የተነሣ እስኪታመም ድረስ ተጨነቀ፤ ድንግል ስለ ሆነች እርሷን ማግኘት የማይቻል ሆኖ አግኝቶታልና።

3አምኖን ኢዮናዳብ የተባለ ወዳጅ ነበረው፤ እርሱም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ነው። ኢዮናዳብ እጅግ ተንኰለኛ ሰው ነበር። 4አምኖንንም፣ “የንጉሥ ልጅ ሆይ፤ ሰውነትህ ቀን በቀን የሚከሳበትን ምክንያት ለምን አትነግረኝም?” ሲል ጠየቀው።

አምኖንም፣ “የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን አፍቅሬ ነው” አለው።

5ኢዮናዳብም፣ “እንግዲያው ‘ታምሜአለሁ’ ብለህ ዐልጋ ላይ ተኛ፤ አባትህ ሊጠይቅህ ሲመጣም፣ ‘እኅቴ ትዕማር መጥታ የምበላውን ነገር ብትሰጠኝ ደስ ይለኛል፤ መብሉንም እዚሁ አጠገቤ ሆና እያየሁ አዘጋጅታ በእጇ እንድታጐርሰኝ እባክህ ፍቀድልኝ ብለህ ንገረው፣’ ” አለው።

6ስለዚህ አምኖን የታመመ ሰው መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው መጣ፤ አምኖንም፣ “እኅቴ ትዕማር መጥታ፣ እያየሁ ሁለት እንጀራ ጋግራ በእጇ እንድታጐርሰኝ እለምንሃለሁ” ብሎ ጠየቀው።

7ዳዊትም፣ “ወንድምሽ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ እንድታዘጋጂለት” በማለት ለትዕማር እንዲነግሯት ወደ ቤተ መንግሥቱ ላከ። 8ስለዚህም ትዕማር ወንድሟ አምኖን ወደ ተኛበት ቤት ሄደች፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ ካቦካች በኋላ እያየ አዘጋጅታ ጋገረችው፤ 9ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ እንጀራውን አቀረበችለት፤ እርሱ ግን መብላት አልፈለገም።

አምኖንም፣ “ሰውን ሁሉ ከዚህ አስወጡልኝ” አለ፤ ያለውም ሰው ሁሉ ትቶት ወጣ። 10ከዚያም አምኖን ትዕማርን፣ “እንድታጐርሺኝ ምግቡን እዚሁ መኝታ ክፍሌ አምጪልኝ” አላት። ትዕማርም ያዘጋጀችውን እንጀራ ይዛ ወንድሟ አምኖን ወዳለበት መኝታ ክፍል ገባች። 11ነገር ግን ምግቡን ስታቀርብለት አፈፍ አድርጎ ያዛትና፣ “እህቴ ነዪ አብረን እንተኛ” አላት።

12እርሷም እንዲህ አለችው፤ “እባክህ ወንድሜ ተው አይሆንም! አታስገድደኝ፤ እንዲህ ያለው ነገር በእስራኤል ተደርጎ አያውቅም፤ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አታድርግ። 13እኔስ እንዴት እሆናለሁ? ነውሬንስ ተሸክሜ የት እገባለሁ? አንተስ ብትሆን በእስራኤል ከወራዳዎቹ እንደ አንዱ መቈጠርህ አይደለምን? እባክህ ለንጉሡ ንገረው፤ እንዳላገባህም አይከለክለኝም።” 14እርሱ ግን ሊሰማት አልፈለገም፤ ከእርሷ ይልቅ ብርቱ ስለ ነበር፣ በግድ አስነወራት፤ ከእርሷም ጋር ተኛ።

15ከዚያም አምኖን እጅግ ጠላት፤ እንዲያውም ቀድሞ ካፈቀራት የበለጠ ጠላት። አምኖንም፣ “ተነሽ ውጭልኝ!” አላት።

16እርሷም፣ “ይህ አይሆንም! እኔን አስወጥቶ መስደድ፣ አስቀድመህ ካደረስህብኝ በደል የባሰ መፈጸምህ ነው” አለችው። እርሱ ግን አልተቀበላትም፤ 17በግል የሚያገለግለውን ወጣት ጠርቶ፣ “ይህችን ሴት ከዚህ አስወጣና በሩን ዝጋባት” አለው። 18ስለዚህም አገልጋዩ አስወጥቶ በሩን ዘጋባት፤ ጌጠኛ13፥18 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። የሆነና በዚያን ጊዜ ድንግል የሆኑት የንጉሥ ልጆች የሚለብሱትን ዐይነት ልብስ ለብሳ ነበር። 19ትዕማርም በራሷ ላይ ዐመድ ነሰነሰች፤ ጌጠኛ13፥19 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። ልብሷን ቀደደች፤ ከዚያም እጇን በራሷ ላይ አድርጋ እያለቀሰች ሄደች።

20ወንድሟ አቤሴሎምም፣ “ያ ወንድምሽ አምኖን ካንቺ ጋር ነበርን? እኅቴ ሆይ፣ አሁን ዝም በዪ፤ ወንድምሽ ስለሆነ፤ ነገሩን በልብሽ አትያዢው” አላት። ትዕማርም በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት ብቸኛ ሴት ሆና ኖረች።

21ንጉሥ ዳዊት ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ 22አቤሴሎም አምኖንን ክፉም ሆነ ደግ አንዳች ቃል አልተናገረውም፤ ምክንያቱም አምኖን እኅቱን ትዕማርን ስላስነወራት ጠልቶት ነበር።

አቤሴሎም አምኖንን ገደለው

23ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም ድንበር አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር ከተማ በጎቹን ይሸልት ነበር፤ በዚህን ጊዜ የንጉሡን ወንዶች ልጆች ሁሉ በዚያ እንዲገኙለት ጋበዛቸው። 24አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ሄዶ፣ “እነሆ፤ ባሪያህ በጎቹን እየሸለተ ነው፤ ታዲያ ንጉሡና ሹማምቱ ፈቃዳቸው ሆኖ እባክህ ይገኙልኝ?” ሲል ጠየቀው።

25ንጉሡም፣ “ልጄ ሆይ፣ ሁላችንም መሄድ የለብንም፤ ሸክም እንሆንብሃለን” ሲል መለሰለት። አቤሴሎም አጥብቆ ቢለምነውም ንጉሡ መሄድ አልፈለገም፤ ነገር ግን መርቆ አሰናበተው።

26አቤሴሎምም፣ “እንግዲያውስ ወንድሜ አምኖን አብሮን ይሂድ” አለው።

ንጉሡም፣ “አብሯችሁ የሚሄደው ስለ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። 27ነገር ግን አቤሴሎም አጥብቆ ስለ ለመነው፣ አምኖንና ሌሎቹ የንጉሡ ወንዶች ልጆች ሁሉ አብረውት እንዲሄዱ አደረገ።

28አቤሴሎምም አገልጋዮቹን፣ “አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ መንፈሱ መለወጡን ተጠባበቁ፤ ከዚያም እኔ አምኖንን፣ ‘ምቱት’ ስላችሁ ግደሉት፤ ያዘዝኋችሁ እኔ ነኝ አትፍሩ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ” ብሎ አዘዛቸው።

29የአቤሴሎምም አገልጋዮች ጌታቸው ያዘዛቸውን በአምኖን ላይ ፈጸሙ። ከዚያም የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተነሥተው በየበቅሎዎቻቸው ላይ ተቀምጠው ሸሹ።

30እነርሱ በመንገድ ላይ ሳሉም፣ “አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች በሙሉ ፈጃቸው፤ አንድም የተረፈ የለም” የሚል ወሬ ለዳዊት ደረሰው። 31ንጉሡም ተነሥቶ ቆመ፤ ልብሱን ቀደደ፤ በመሬትም ላይ ተዘረረ፤ በአጠገቡ ቆመው የነበሩት አገልጋዮቹም ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ።

32የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ ግን እንዲህ አለ፤ “የንጉሡን ልጆች በሙሉ እንደ ፈጇቸው አድርጎ ጌታዬ አያስብ፤ እኅቱን ትዕማርን በግድ ካስነወራት ጊዜ አንሥቶ አቤሴሎም ቈርጦ የተነሣበት ጕዳይ ስለሆነ፣ የሞተው አምኖን ብቻ ነው። 33እንግዲህ የሞተው አምኖን ብቻ ስለሆነ፣ ‘የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተገደሉ’ ተብሎ የተነገረውን ንጉሥ ጌታዬ ማመን የለበትም።”

34አቤሴሎምም ፈጥኖ ሸሸ። ለዘብ ጥበቃ የቆመውም ሰው ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ከእርሱ በስተ ምዕራብ ካለው መንገድ ብዙ ሰዎች በተራራው ጥግ ቍልቍል ሲወርዱ አየ፤ ዘብ ጠባቂውም ሄዶ ለንጉሡ፣ “ከበስተ ሖሮናይም አቅጣጫ በኰረብታው ጥግ ላይ ሰዎች ቍልቍል ሲወርዱ አያለሁ”13፥34 የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ዕብራይስጡ ግን ይህን ዐረፍተ ነገር አይጨምርም። ብሎ ነገረው።

35ኢዮናዳብም ዳዊትን፣ “እነሆ፣ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤ አገልጋይህም እንዳለው ሆኗል” አለው።

36ገና ተናግሮ ሳይጨርስ፣ የንጉሡ ልጆች ጮኸው እየተላቀሱ ገቡ፤ እንደዚሁም ንጉሡና አገልጋዮቹ ሁሉ እጅግ አለቀሱ።

37አቤሴሎም ኰብልሎ የጌሹር ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ተልማይ ሄደ፤ ነገር ግን ዳዊት ስለ ሞተው ልጁ ዘወትር ያለቅስ ነበር።

38አቤሴሎም ሸሽቶ ወደ ጌሹር ከሄደ በኋላ፣ በዚያ ሦስት ዓመት ተቀመጠ። 39ንጉሥ ዳዊት በልጁ በአምኖን ሞት ከደረሰበት ሐዘን ከተጽናና በኋላ፣ ወደ አቤሴሎም ለመሄድ መንፈሱ ተነሣሣ13፥39 የሙት ባሕር ጥቅልልና አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ቅጆች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ የማሶሬቱ ቅጅ ግን፣ የንጉሥ ዳዊት መንፈስ ተነሣሣ ይላል።