2 ሳሙኤል 12 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ሳሙኤል 12:1-31

ናታን ዳዊትን ገሠጸው

11፥112፥29-31 ተጓ ምብ – 1ዜና 20፥1-3

1እግዚአብሔር ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ባለጠጋ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ። 2ባለ ጠጋው እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤ 3ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም። ተንከባከባት፤ አብራውም ከልጆቹ ጋር አደገች፤ አብራው ትበላ፤ ከጽዋው ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደ ገዛ ልጁ ነበረች።

4“ወደ ባለ ጠጋውም ቤት እንግዳ መጣ፤ ባለ ጠጋው ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ ከዚህ ይልቅ የድኻውን እንስት ጠቦት በግ ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።”

5ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ሕያው እግዚአብሔርን ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! 6እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለ ማዘኑም ስለ በጊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።”

7ከዚያም ናታን፣ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤ 8የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፣ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ አስታቀፍሁህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ፣ ከዚህ በላይ ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር። 9ታዲያ በፊቱ ክፉ ነገር በማድረግ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ያቃለልኸው ስለ ምንድን ነው? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታህ፤ ሚስት እንድትሆንህም ሚስቱን ወሰድሃት፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው። 10ስለዚህ ሰይፍ ለዘላለም ከቤትህ አይርቅም፤ እኔን አቃልለኸኛል፤ ሚስት እንድትሆንህም የኬጢያዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደሃታልና።’

11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ ከራስህ ቤት ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ዐይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለአንተ ቅርብ ለሆነ ሰው ለአንዱ እሰጣለሁ፤ እርሱም በቀን ብርሃን ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። 12አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህንኑ ነገር በቀን ብርሃን በእስራኤል ሁሉ ፊት እገልጠዋለሁ።’ ”

13ከዚያም ዳዊት ለናታን፣ “እግዚአብሔርን በጣም በድያለሁ” አለው። ናታንም እንዲህ አለው፣ “እግዚአብሔር ኀጢአትህን አስወግዶልሃል። አንተ አትሞትም፤ 14ይህን በመፈጸምህ ግን፣ የእግዚአብሔር ጠላቶች እጅግ እንዲያቃልሉት12፥14 የማሶሬቱ ቅጅ ክዚህ ጋር ይስማማል፤ ጥንታዊው የዕብራይስጥ የጸሓፍት ትውፊት ግን፤ በዚህም እግዚአብሔርን እጅግ ስላቃለልህ ይላል። ስላደረግህ፣ የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።”

15ናታን ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ፣ የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ሕፃን እግዚአብሔር ከባድ ሕመም ላይ ጣለው። 16ዳዊት ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ጾመም፤ ከዚያም ወደ ክፍሉ ገብቶ በተከታታይ ሌሊቱን መሬት ላይ ተኝቶ ዐደረ። 17የቤተ ሰቡ ሰው፣ ሽማግሌዎችም ከመሬት ሊያስነሡት በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እንቢ አለ፤ አብሯቸውም አንዳች ነገር አልበላም።

18በሰባተኛው ቀን ሕፃኑ ሞተ፤ የዳዊት አገልጋዮችም፣ “እነሆ ሕፃኑ በሕይወት እያለ የነገርነውን ዳዊት አልሰማንም፤ ታዲያ አሁን የሕፃኑን መሞት እንዴት አድርገን ልንነግረው እንችላለን? በራሱ ላይ ጕዳት ሊያደርስ ይችላል” ብለው መንገሩን ፈሩ።

19ዳዊት አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ አይቶ፣ ሕፃኑ መሞቱን ዐወቀ፤ ስለዚህ፣ “ሕፃኑ ሞተ?” ብሎ ጠየቃቸው።

እነርሱም፣ “አዎን ሞቷል” ብለው መለሱለት።

20በዚህ ጊዜ ዳዊት ከመሬት ተነሣ፤ ከታጠበ፣ ከተቀባና ልብሱን ከለወጠ በኋላ፣ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ሄዶ ሰገደ። ከዚያም ወደ ክፍሉ ገባ፤ በራሱም ጥያቄ ምግብ አቅርበውለት በላ።

21አገልጋዮቹም፣ “እንደዚህ ያደረግኸው ለምንድን ነው? ሕፃኑ በሕይወት እያለ ጾምህ፤ አለቀስህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ በላህ” ብለው ጠየቁት።

22እርሱም እንዲህ አለ፤ “በርግጥ ሕፃኑ በሕይወት እያለ፣ ‘እግዚአብሔር ይቅር ብሎኝ ሕፃኑን በሕይወት ያኖረው ይሆናል’ ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁ። 23አሁን ግን ሕፃኑ ስለ ሞተ፣ የምጾመው ለምንድን ነው? መልሼ ላመጣው እችላለሁን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ፣ እርሱ ወደ እኔ አይመለስ!”

24ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፤ ወደ እርሷም ገብቶ አብሯት ተኛ፤ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሰሎሞን አለው። እግዚአብሔርም ወደደው፤ 25እግዚአብሔር ሕፃኑን ስለ ወደደም ስሙ ይዲድያ12፥25 ይዲድያ ማለት በእግዚአብሔር ያህዌ የተወደደ ማለት ነው። ተብሎ እንዲጠራ በነቢዩ በናታን በኩል ቃል ላከ።

26በዚያን ጊዜም ኢዮአብ የአሞናውያንን ከተማ ረባትን ወግቶ የቤተ መንግሥቱን ምሽግ ያዘ። 27ከዚያም ኢዮአብ እንዲህ በማለት ወደ ዳዊት መልክተኞችን ላከ፤ “ረባትን ወግቼ የውሃውን ከተማ ይዤአለሁ፤ 28እንግዲህ የቀረውን ሰራዊት አሰባስበህ ከተማዪቱን ክበብና ያዛት፤ አለዚያ እኔ ከተማዪቱን እይዛትና በስሜ መጠራቷ ነው።”

29ስለዚህ ዳዊት መላውን ሰራዊት አሰባስቦ ወደ ረባት በመሄድ ወግቶ ያዛት። 30የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ፤ የዘውዱ ክብደት አንድ መክሊት ወርቅ የሚመዝን ሲሆን፣ በከበረ ዕንቍም ያጌጠ ነበር፤ ይህም በዳዊት ራስ ላይ ተጫነ። ዳዊትም ከከተማዪቱ እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰደ፤ 31እዚያ የነበሩትንም ሕዝብ አውጥቶ መጋዝ፣ የብረት መቈፈሪያና መጥረቢያ ተጠቅመው ሥራ እንዲሠሩ አደረጋቸው፣ እንዲሁም የሸክላ ጡብ አሠራቸው12፥31 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም።። እንዲህ ያለውም ሥራ በሌሎቹ የአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲፈጸም አደረገ። ከዚያም ዳዊትና ሰራዊቱ በሙሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።