1 ዜና መዋዕል 17 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ዜና መዋዕል 17:1-27

እግዚአብሔር ለዳዊት የሰጠው ተስፋ

17፥1-15 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 7፥1-17

1ዳዊት በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ በተቀመጠበት ጊዜ፣ ነቢዩ ናታንን “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው።

2ናታንም ለዳዊት፣ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለሆነ፣ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት።

3በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጥቶ እንዲህ አለው፤

4“ሂድና ለባሪያዬ ለዳዊት እንዲህ ብለህ ንገረው፤ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘እኔ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም። 5እስራኤልን ከግብፅ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ከአንዱ ድንኳን ወደ ሌላው ድንኳን፣ ከአንዱ ማደሪያ ወደ ሌላው ማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ፣ በቤት ውስጥ አልኖርሁም። 6ከእስራኤላውያን ጋር በሄድሁባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ ሕዝቤን እንዲጠብቁ ላዘዝኋቸው መሪዎቻቸው17፥6 በዚህና በቍጥር 10 ላይ በትውፊት፣ መሳፍንት ይባላል ከቶ፣ “ለምን ከዝግባ ዕንጨት ቤት አልሠራችሁልኝም” ያልሁበት ጊዜ አለን?’

7“እንግዲህ አሁንም ለባሪያዬ ለዳዊት እንዲህ ብለህ ንገረው፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘የሕዝቤ የእስራኤል ገዥ እንድትሆን በጎችን ከመጠበቅና ከመከተል አንሥቼ ወሰድሁህ። 8በሄድህበት ሁሉ ከአንተ አልተለየሁም፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስምህን እንደ ምድር ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ። 9ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ ስፍራ እሰጠዋለሁ፤ የራሳቸውም መኖሪያ ስፍራ እንዲኖራቸው፣ ከእንግዲህም በኋላ እንዳይናወጡ አደርጋቸዋለሁ። ክፉ ሰዎች በመጀመሪያ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ከእንግዲህ አይጨቍኗቸውም፤ 10ከዚህ ቀደም በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪዎች በሾምሁ ጊዜ ጨቋኞቹ ያደረጉትን ዛሬ አያደርጉትም፤ ጠላቶቻችሁን ሁሉ አዋርዳቸዋለሁ።

“ ‘እግዚአብሔር ቤት እንደሚሠራልህ በግልጽ እነግርሃለሁ፤ 11ዘመንህን ጨርሰህ ወደ አባቶችህ በምትሄድበት ጊዜ፣ ከአብራክህ ከተከፈሉት ልጆችህ አንዱ በእግርህ እንዲተካ አደርጋለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለታለሁ፤ 12ቤት የሚሠራልኝም እርሱ ነው፤ እኔም ዙፋኑን ለዘላለም አጸናለሁ። 13አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ጽኑ ፍቅሬን ከአንተ በፊት ከነበረው ላይ እንደ ወሰድሁ፣ ከእርሱ ላይ ከቶ አልወስድም። 14በቤቴና በመንግሥቴ ላይ ለዘላለም አኖረዋለሁ፤ ዙፋኑም ለዘላለም ይጸናል።’ ”

15ናታንም የዚህን ሁሉ ራእይ ቃል ለዳዊት ነገረው።

የዳዊት ጸሎት

17፥16-27 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 7፥18-29

16ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦም እንዲህ አለ፤

እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለመሆኑ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤተ ሰቤስ ምንድን ነው? 17አምላክ ሆይ፤ ይህ በፊትህ በቂ እንዳልሆነ ቈጥረህ ስለ ወደ ፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ እኔንም ከሰዎች ሁሉ እጅግ የከበረ ሰው አድርገህ ተመለከትኸኝ።

18“ባሪያህን ስላከበርኸው፣ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ማለት ይችላል? ባሪያህን እኮ ታውቀዋለህ፤ 19እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ባሪያህ ብለህና እንደ ፈቃድህም መሠረት ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ እነዚህም ታላላቅ ተስፋዎች ሁሉ እንዲታወቁ አደረግህ።

20“አቤቱ፤ እንደ አንተ ያለ የለም፤ በጆሯችን እንደ ሰማነው ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። 21ከግብፅ ተቤዥተህ እንዳወጣኸው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ማን አለ? እነርሱ እግዚአብሔር ለራሱ ሊቤዣቸው ከምድር ሕዝቦች መካከል የመረጣቸው ናቸው፤ በሕዝብህም ፊት ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን በማድረግ መንግሥታትን በፊታቸው አሳደድህ። 22ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም የራስህ ሕዝብ አደረግኸው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆንህለት።

23እግዚአብሔር ሆይ፤ አሁንም ስለ ባሪያህና ስለ ቤቱ የሰጠኸው ተስፋ ለዘላለም የጸና ይሁን፤ የሰጠኸውንም ተስፋ ፈጽም፤ 24ይህም ስምህ ጸንቶ እንዲኖርና ለዘላለምም ታላቅ እንዲሆን ነው። ከዚያም ሰዎች ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእውነት የእስራኤል አምላክ ነው!’ ይላሉ፤ የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል።

25“አምላኬ ሆይ፤ ቤት እንደምትሠራለት ለባሪያህ ገልጸህለታል፤ ስለዚህ ባሪያህ ወደ አንተ ለመጸለይ ድፍረት አገኘ። 26እግዚአብሔር ሆይ፤ በእውነት አንተ አምላክ ነህ፤ ይህንም መልካም ተስፋ ለባሪያህ ሰጥተሃል። 27በፊትህ ለዘላለም እንዲኖር አሁንም የባሪያህን ቤት ልትባርክ ወድደሃል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የባረክኸው አንተ ስለ ሆንህ፣ ለዘላለም የተባረከ ይሆናል።”