1 ዜና መዋዕል 14 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ዜና መዋዕል 14:1-17

የዳዊት ቤትና ቤተ ሰቡ

14፥1-7 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥11-161ዜና 3፥5-8

1በዚህ ጊዜ የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዳዊት ቤተ መንግሥት እንዲሠሩ መልክተኞችን፣ ድንጋይ ጠራቢዎችንና ዐናጢዎችን ከዝግባ ዕንጨት ጋር ላከ። 2ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ አንግሦ እንዳጸናውና ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል ሲል መንግሥቱን ከፍ ከፍ እንዳደረገለት አስተዋለ።

3ዳዊትም በኢየሩሳሌም ብዙ ሚስቶች አገባ፤ ከእነርሱም ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 4በዚያ ሳለ የወለዳቸው የልጆቹ ስም ይህ ነው፤ ሳሙስ፣ ሶባብ፣ ናታን፣ ሰሎሞን፣ 5ኢያቤሐር፣ ኤሊሱዔ፣ ኤሊፋላት፣ 6ኖጋ፣ ናፌቅ፣ ያፍያ፣ 7ኤሊሳማ፣ ኤሊዳሄ፣ ኤሊፋላት።

ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አደረገ

14፥8-17 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥17-25

8ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ተቀብቶ መንገሡን ፍልስጥኤማውያን በሰሙ ጊዜ፣ እርሱን ፍለጋ በሙሉ ኀይላቸው ወጡ፤ ዳዊት ይህን ሰምቶ ስለ ነበር ሊገጥማቸው ወጣ። 9በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን መጥተው የራፋይምን ሸለቆ ወረሩ። 10ስለዚህ ዳዊት፣ “ወጥቼ በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ልጣልን? አንተስ በእጄ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ።

እግዚአብሔርም፣ “አዎን ውጣ! በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ” ብሎ መለሰለት።

11ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ በኣልፐራሲም ወጡ፤ በዚያም ድል አደረጋቸው። ዳዊትም፣ “ውሃ ነድሎ እንደሚወጣ ሁሉ እግዚአብሔርም ጠላቶቼን በእጄ አፈረሳቸው” አለ፤ ከዚህም የተነሣ ያን ቦታ “በኣልፐራሲም” ብለው ሰየሙት። 12ፍልስጥኤማውያን አማልክታቸውን በዚያው ጥለዋቸው ስለ ነበር፣ ዳዊት በእሳት እንዲያቃጥሏቸው አዘዘ።

13ፍልስጥኤማውያን ሸለቆውን እንደ ገና ወረሩ፤ 14ዳዊትም እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት “ዙሪያውን ከብበህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት አደጋ ጣልባቸው እንጂ በቀጥታ ወደ ላይ አትውጣ፤ 15በሾላው ዐናት ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ ወዲያውኑ ለጦርነት ውጣ፤ ይህም የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመምታት እግዚአብሔር በፊትህ ወጥቷል ማለት ነውና።” 16ስለዚህ ዳዊት እግዚአብሔር እንዳለው አደረገ፤ ከገባዖን ጀምሮ እስከ ጌዝር ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መቷቸው።

17ከዚህም የተነሣ የዳዊት ዝና በየአገሩ ሁሉ ተሰማ፤ እግዚአብሔርም መንግሥታት ሁሉ እንዲፈሩት አደረገ።