1 ነገሥት 22 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ነገሥት 22:1-53

ሚክያስ በአክዓብ ላይ ትንቢት ተናገረ

22፥1-28 ተጓ ምብ – 2ዜና 18፥1-27

1በሶርያና በእስራኤል መካከል ለሦስት ዓመት ጦርነት አልነበረም። 2በሦስተኛው ዓመት ግን የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ ለመጐብኘት ወረደ። 3የእስራኤልም ንጉሥ ሹማምቱን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ሬማት የእኛ ሆና ሳለች፣ ከሶርያው ንጉሥ እጅ ለመመለስ ምንም እንዳላደረግን አታውቁምን?” አላቸው።

4ስለዚህ ኢዮሣፍጥን፣ “በገለዓድ የምትገኘው ሬማት ላይ ለመዝመት አብረኸኝ ለመሄድ ትፈቅዳለህን?” ሲል ጠየቀው።

ኢዮሣፍጥም፣ “እኔ ያው እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤ እንደ ሕዝብህ፣ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለ። 5ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፣ “በመጀመሪያ ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ጠይቅ” አለው።

6ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ ልዝመት ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው።

እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት።

7ኢዮሣፍጥ ግን፣ “የምንጠይቀው የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።

8የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በእርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቀው አንድ ሰው አሁንም አለ፤ ነገር ግን ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ አንዳችም መልካም ትንቢት ተናግሮ ስለማያውቅ እጠላዋለሁ፤ ይህም ሰው የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለ። ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሡ እንዲህ ማለት አይገባውም” ሲል መለሰ።

9ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ፣ “በል የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው” አለው።

10የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ አልባሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር አጠገብ ባለው አውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው ሳለ፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።

11በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ የተባለው የክንዓና ልጅ የብረት ቀንዶች አበጅቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ የምትወጋቸው በእነዚህ ነው’ ” አለው።

12የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና በገለዓድ የምትገኘውን ሬማትን ወግተህ ድል አድርግ” በማለት በአንድ ቃል ትንቢት ይናገሩ ነበር።

13ከዚያም ሚክያስን ሊጠራ የሄደው መልእክተኛ፣ “እነሆ፤ ሌሎቹ ነቢያት ንጉሡ ድል እንደሚያደርግ በአንድ ቃል ትንቢት እየተናገሩለት ነውና የአንተም ቃል ከእነርሱ ጋር አንድ እንዲሆን እባክህ መልካም ነገር ተናገር” አለው።

14ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ለእርሱ የምነግረው እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ ነው” አለ።

15እዚያም እንደ ደረሰ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፤ በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ እንዝመትባት ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው።

እርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዘምተህ ድል አድርጋት” ብሎ መለሰለት።

16ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር በእግዚአብሔር ስም አንዳች ነገር እንዳትነግረኝ የማምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው።

17ከዚያም ሚክያስ እንዲህ ሲል መለሰ፣ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በየተራራው ላይ ተበትነው አየሁ፣ እግዚአብሔርም፣ ‘ይህ ሕዝብ ጌታ የለውም፤ እያንዳንዱ በሰላም ወደየቤቱ ይሂድ’ አለ።”

18የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው።

19ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይ ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ፤ 20እግዚአብሔርም፣ ‘በገለዓድ በምትገኘው ሬማት ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት፣ አክዓብን ማን ያስተው?’ አለ።

“ታዲያ አንዱ ይህን፣ ሌላውም ያን አለ፤ 21በመጨረሻም፣ አንድ መንፈስ ወጣ፤ ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ፣ ‘እኔ አስተዋለሁ’ አለ።

22እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው።

“እርሱም፣ ‘እኔ እወጣለሁ፤ በገዛ ነቢያቱም አፍ ሁሉ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ።

እግዚአብሔርም፣ ‘በል እንግዲያው ውጣና አስተው፤ ይሳካልሃል’ አለው።

23“ስለዚህ እነሆ እግዚአብሔር በእነዚህ ሁሉ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ በአንተም ላይ መዓቱን እንደሚያመጣብህ ተናገረ።”

24ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚክያስን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ በየት በኩል ዐልፎ ነው አንተን መጥቶ ያናገረህ?” ሲል ጠየቀው።

25ሚክያስም፤ “ይህንማ ለመደበቅ ወደ አንዲት እልፍኝ በሄድህ ዕለት ታውቀዋለህ” አለው።

26ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “በሉ ሚክያስን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤ 27ከዚያም፣ ‘ንጉሡ፣ በደኅና እስክመለስ ድረስ፣ ይህን ሰው በእስር ቤት አቈዩት፤ ከደረቅ እንጀራና ከውሃ በስተቀር ሌላ እንዳትሰጡት’ ብሏል በሉት” አለ።

28ሚክያስም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስህ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረማ!” አለ፤ ከዚያም በመቀጠል፣ “በዚህ ያለኸው ሕዝብ ሁሉ ይህን ቃሌን ልብ ብለህ ያዘው፤” አለ።

አክዓብ በገለዓድ በምትገኘው በሬማት ተገደለ

22፥29-36 ተጓ ምብ – 2ዜና 18፥28-34

29ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ወደምትገኘው ሬማት ወጡ። 30የእስራኤል ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እንዳልታወቅ እኔ ልብስ ለውጬና ሌላ ሰው መስዬ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ራሱን ደብቆ ወደ ጦርነቱ ገባ።

31በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሠረገላ አዛዦች፣ “ከራሱ ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽም ይሁን ትልቅ ከማንም ጋር እንዳትገጥሙ” ሲል አዝዟቸው ነበር፤ 32የሠረገላ አዛዦቹ ኢዮሣፍጥን ሲያዩት፣ “ያለ ጥርጥር ይህ የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፤ ስለዚህ አደጋ ሊጥሉበት ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ሲጮህ ግን 33የሠረገላ አዛዦቹ እርሱ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን ዐውቀው መከታተሉን ተዉት።

34ነገር ግን አንዱ ቀስቱን ሳያልም እንዲሁ ሲያስፈነጥር በጦር ልብሱ መጋጠሚያ ላይ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው፤ ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን፣ “ቈስያለሁና ወደ ኋላ አዙረህ ከጦሩ ሜዳ አውጣኝ” አለው። 35ጦርነቱም ቀኑን ሙሉ ተፋፍሞ ዋለ፤ በዚህ ጊዜም ንጉሡ በሶርያውያን ፊት ለፊት ሠረገላው ላይ ቀና ብሎ እንደ ተደገፈ ነበር፤ የቍስሉ ደም በሠረገላው ወለል ላይ ይወርድ ነበር፤ በዚያኑ ዕለት ማታም ንጉሡ ሞተ። 36ፀሓይ ስትጠልቅም በሰራዊቱ መካከል፣ “እያንዳንዱ ሰው ወደ ቤቱ፣ እያንዳንዱም ወደ ሀገሩ ይሂድ!” የሚል ጩኸት አስተጋባ።

37ንጉሡ ስለ ሞተም ወደ ሰማርያ አምጥተውት እዚያው ተቀበረ። 38ሠረገላውንም አመንዝሮች በታጠቡበት በሰማርያ22፥38 ወይም፣ የጦር መሣሪያ በሚታጠብበት በሰማርያ ተብሎ መተርጐም ይችላል ኵሬ ዐጠቡት፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ቃል ደሙን ውሾች ላሱት።

39ሌላው በአክዓብ ዘመነ መንግሥት የተፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ ቤተ መንግሥቱን መሥራቱና በዝኆን ጥርስ መለበጡ እንዲሁም የሠራቸው የምሽግ ከተሞች በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን? 40አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ አካዝያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ

22፥41-50 ተጓ ምብ – 2ዜና 20፥31–21፥1

41የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ነገሠ። 42ኢዮሣፍጥ ሲነግሥ ዕድሜው ሠላሳ አምስት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ሃያ አምስት ዓመት ገዛ። እናቱ ዓዙባ ትባላለች፤ እርሷም የሺልሒ ልጅ ነበረች። 43በአካሄዱም ሁሉ የአባቱን የአሳን መንገድ ተከተለ፤ ከዚያች ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን አደረገ፤ ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎች አላጠፋም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ይሠዋ፣ ዕጣንም ያጥን ነበር። 44እንዲሁም ኢዮሣፍጥ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር በሰላም ኖረ።

45ሌላውም ኢዮሣፍጥ በዘመነ መንግሥቱ የፈጸመው፣ ያከናወነውና ያደረገው ጦርነት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን? 46ከአባቱ ከአሳ ዘመን በኋላ እንኳ ተርፈው በጣዖት ማምለኪያ ቦታዎች የነበሩትን የወንደቃ ቅሬታዎች ከምድሪቱ አስወገደ። 47በዚያን ጊዜ ኤዶም ንጉሥ አልነበራትም፤ የሚገዛት እንደራሴ ነበር።

48ኢዮሣፍጥ ወርቅ ለማምጣት ወደ ኦፊር የሚሄዱ የንግድ መርከቦች22፥48 ዕብራይስጡ የተርሴስ መርከቦች ይላል አሠርቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ በዔጽዮንጋብር ስለ ተሰበሩ ከቶ ወደዚያ መሄድ አልቻሉም ነበር። 49በዚያን ጊዜም የአክዓብ ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን “ሰዎቼ ከሰዎችህ ጋር በመርከብ ይሂዱ” ሲል ጠይቆት ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን እሺ አላለውም።

50ኢዮሣፍጥ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበት በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮራምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ

51የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በሰማርያ ነገሠ፤ እስራኤልንም ሁለት ዓመት ገዛ። 52እርሱም የአባቱንና የእናቱን፣ እንዲሁም እስራኤልን ያሳተውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን መንገድ በመከተሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ሥራ ሠራ። 53አባቱ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በኣልን አመለከ፤ ሰገደለትም። በዚህም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ እንዲነሣሣ አደረገ።