1 ነገሥት 21 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ነገሥት 21:1-29

የናቡቴ የወይን ተክል ቦታ

1ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ የወይን ተክል ቦታ ላይ አንድ ነገር ደረሰ፤ ቦታውም በኢይዝራኤል ውስጥ ከሰማርያ ንጉሥ ከአክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ ነበር። 2አክዓብም ናቡቴን፣ “የወይን ተክል ቦታህ ከቤተ መንግሥቴ አጠገብ ስለሆነ፣ የአትክልት ቦታ እንዳደርገው ልቀቅልኝ፤ በምትኩ ከዚህ የበለጠ የወይን ተክል ቦታ እሰጥሃለሁ፤ የተሻለ ሆኖ ከታየህም የሚያወጣውን ገንዘብ እከፍልሃለሁ” አለው።

3ናቡቴ ግን፣ “ዐፅመ ርስቴን እለቅልህ ዘንድ እግዚአብሔር አይበለው” ሲል መለሰለት።

4ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ፣ “ዐፅመ ርስቴን አልለቅልህም” ስላለው፣ አክዓብ ተበሳጭቶና ተቈጥቶ ወደ ቤቱ ገባ፤ አኵርፎም በዐልጋው ላይ ተኛ፤ ምግብም መብላት ተወ።

5ሚስቱ ኤልዛቤልም ወደ እርሱ ገብታ፣ “እስከዚህ የተበሳጨኸው፣ ምግብስ የማትበላው ለምንድን ነው?” ብላ ጠየቀችው።

6እርሱም፣ “ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን፣ ‘የወይን ተክል ቦታህን ሽጥልኝ፤ ከፈለግህም በምትኩ ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ’ አልሁት፤ እርሱ ግን፣ ‘የወይን ተክል ቦታዬን አልለቅልህም’ ስላለኝ ነው” አላት።

7ሚስቱ ኤልዛቤልም፣ “አንተ አሁን የእስራኤል ንጉሥ ትባላለህ? በል ተነሥና እህል ቅመስ፤ ደስም ይበልህ፤ የኢይዝራኤላዊውን የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ እኔ እንድታገኝ አደርግሃለሁ” አለችው። 8ስለዚህ በአክዓብ ስም ደብዳቤዎች ጻፈች፤ በገዛ ማኅተሙም ዐትማ በናቡቴ ከተማ አብረውት ለሚኖሩ ሽማግሌዎችና መኳንንት ላከች። 9በደብዳቤዎቹም ላይ እንዲህ ስትል ጻፈች፤

“የአንድ ቀን ጾም ዐውጁ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ መካከል ከፍ ባለ ቦታ ላይ አስቀምጡት። 10እንዲሁም ሁለት የሐሰት ምስክሮች ከፊት ለፊቱ አስቀምጡና፣ ‘እግዚአብሔርንም ንጉሡንም ሰድቧል’ ብለው ይመስክሩበት፤ ከዚያም አውጥታችሁ በድንጋይ ወግራችሁ ግደሉት።”

11ስለዚህ በናቡቴ ከተማ የሚኖሩ ሽማግሌዎችና መኳንንት በደብዳቤዎቹ ላይ እንደ ጻፈችላቸው አደረጉ። 12የአንድ ቀን ጾም ዐወጁ፤ ናቡቴንም በሕዝቡ መካከል ከፍ ባለ ቦታ ላይ አስቀመጡት። 13ከዚያም ሁለት የሐሰት ምስክሮች መጥተው ከፊት ለፊቱ ተቀመጡ፤ በሕዝቡም ፊት፣ “ናቡቴ እግዚአብሔርንና ንጉሡን ሰድቧል” ብለው መሰከሩበት። ስለዚህ ከከተማዪቱ ውጭ ወስደው በድንጋይ ወግረው ገደሉት። 14ከዚያም ለኤልዛቤል፣ “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቷል” ብለው ላኩባት።

15ኤልዛቤልም በድንጋይ ተወግሮ መሞቱን ወዲያው እንደ ሰማች አክዓብን፣ “ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ ሞቷል፤ በል ተነሣና ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ ሊሸጥልህ ያልፈለገውን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ውሰደው” አለችው። 16አክዓብ የናቡቴን ሞት ሲሰማ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ተነሥቶ ወረደ።

17ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 18“ተነሣና በሰማርያ ሆኖ የሚገዛውን የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በርስትነት ለመያዝ ሄዶ አሁን እዚያው ይገኛል። 19እንዲህም በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰውየውን ገደልኸው፤ ደግሞ ርስቱን ልትወስድ?’ ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ቦታ የአንተንም ደም ውሾች እንዲሁ ይልሱታል!’ ”

20አክዓብም ኤልያስን፣ “ጠላቴ ሆይ አገኘኸኝን?” አለው።

ኤልያስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “በእግዚአብሔር ፊት የተጠላውን ነገር ለማድረግ ራስህን ሸጠሃልና አዎን አግኝቼሃለሁ። 21‘እነሆ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፤ ዘርህን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ባሪያም ይሁን ነጻ እያንዳንዱን የአክዓብን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ከእስራኤል እጠርጋለሁ። 22ለቍጣ ስላነሣሣኸኝና እስራኤልንም ስላሳትሃቸው፣ ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፣ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።’

23“ስለ ኤልዛቤልም እግዚአብሔር፣ ‘በኢይዝራኤል ቅጥር አጠገብ21፥23 አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ ነገር ግን አንዳንድ የዕብራይስጥ ቅጆች፣ ቩልጌትና የሱርስቱ ትርጕም (2ነገ 9፥26 ይመ)፣ በዕርሻው ማሳ ላይ ይላሉ። ውሾች ኤልዛቤልን ይበሏታል’ ይላል።

24“ደግሞም ከአክዓብ ወገን ሆኖ በከተማ የሞተውን ውሾች ይበሉታል፤ በገጠር የሞተውንም የሰማይ አሞሮች ይበሉታል።”

25በሚስቱ በኤልዛቤል ተገፋፍቶ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ለማድረግ ራሱን የሸጠ እንደ አክዓብ ያለ ሰው ከቶ አልነበረም። 26እግዚአብሔር ከእስራኤል ፊት ያሳደዳቸው አሞራውያን እንዳደረጉት ሁሉ፣ እርሱም ጣዖታትን በማምለክ እጅግ የሚያስጸይፍ ርኩሰት ፈጸመ።

27አክዓብም ይህን ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶ፤ ጾመ፤ በማቅ ላይ ተኛ በሐዘን ኵርምት ብሎም ይሄድ ነበር።

28ከዚያም እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቴስብያዊው ወደ ኤልያስ መጣ፤ 29“አክዓብ ራሱን በፊቴ እንዴት እንዳዋረደ አየህን? ራሱን ስላዋረደ ይህን መከራ በዘመኑ አላመጣበትም፤ ነገር ግን ይህን በቤቱ ላይ የማመጣው በልጁ ዘመን ነው።”