1 ቆሮንቶስ 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ቆሮንቶስ 8:1-13

ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ

1ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋ ደግሞ ይህን እላለሁ፤ ሁላችንም ዕውቀት እንዳለን እናውቃለን8፥1 ወይም እናንተ እንደምትሉት “ሁላችንም ዕውቀት አለን”። ዕውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል። 2ዐውቃለሁ የሚል ሰው፣ ማወቅ የሚገባውን ያህል ገና አላወቀም። 3እግዚአብሔርን የሚወድድ ሰው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።

4እንግዲህ፣ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ስለ መብላት እንዲህ እላለሁ፤ በዚህ ዓለም ጣዖት ከንቱ እንደ ሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። 5መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ በሰማይም ሆነ በምድር አምላክ ተብለው የሚጠሩ አማልክት ቢኖሩም፣ 6ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ደግሞም ሁሉም ነገር በእርሱ አማካይነት የሆነ፣ እኛም በእርሱ አማካይነት የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።

7ነገር ግን ይህን የሚያውቁ ሁሉም አይደሉም፤ አንዳንድ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ ጣዖትን ማምለክ ስለ ለመዱ፣ እንዲህ ያለውን ሥጋ ሲበሉ በርግጥ ለጣዖት እንደ ተሠዋ ያስባሉ፤ ኅሊናቸውም ደካማ ስለሆነ ይረክሳል። 8ነገር ግን ምግብ ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላ የሚጐድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር አይኖርም።

9ነገር ግን ከነጻነታችሁ የተነሣ የምታደርጉት ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆን ተጠንቀቁ። 10አንተ ይህን የመሰለ ዕውቀት ኖሮህ፣ ደካማ ኅሊና ያለው ሰው በቤተ ጣዖት ስትበላ ቢያይህ፣ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ ለመብላት አይደፋፈርምን? 11ስለዚህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ደካማ ወንድም በአንተ ዕውቀት ምክንያት ጠፋ ማለት ነው። 12በዚህ መንገድ ወንድሞቻችሁን በመበደልና ደካማ ኅሊናቸውን በማቍሰል፣ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። 13ስለዚህ እኔ የምበላው ነገር ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፣ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከቶ ሥጋ አልበላም።