1 ቆሮንቶስ 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ቆሮንቶስ 2:1-16

1ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን ምስጢር2፥1 አንዳንድ ቅጆች ስለ እግዚአብሔር ይላሉ በረቀቀ የንግግር ችሎታ ወይም በላቀ ጥበብ ልገልጥላችሁ አልመጣሁም። 2በመካከላችሁ ሳለሁ ኢየሱስ ክርስቶስን ያውም የተሰቀለውን፣ እርሱን ብቻ እንጂ ሌላ እንዳላውቅ ወስኜ ነበርና። 3ወደ እናንተ የመጣሁት በድካምና በፍርሀት፣ እንዲሁም በብዙ መንቀጥቀጥ ነበር። 4ቃሌም ስብከቴም የመንፈስን ኀይል በመግለጥ እንጂ፣ በሚያባብል የጥበብ ቃል አልነበረም፤ 5ይኸውም እምነታችሁ በእግዚአብሔር ኀይል እንጂ በሰው ጥበብ ላይ እንዳይመሠረት ነው።

ከመንፈስ የተገኘ ጥበብ

6በበሰሉ ሰዎች መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፤ ይሁን እንጂ የዚህችን ዓለም ጥበብ ወይም የሚጠፉትን የዚህችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም። 7ነገር ግን ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ምስጢር ጥበብ ነው፤ ይህም ጥበብ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ለክብራችን አስቀድሞ የወሰነው ነው። 8ከዚህ ዓለም ገዦች አንዳቸውም ይህን ጥበብ አልተረዱትም፤ ቢረዱትማ ኖሮ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት ነበር። 9ይሁን እንጂ፣ እንደ ተጻፈው፣

“ዐይን ያላየውን፣

ጆሮ ያልሰማውን፣

የሰውም ልብ ያላሰበውን፣

እግዚአብሔር ለሚወድዱት አዘጋጅቷል፤”

10እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦልናል።

መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራል። 11በውስጡ ካለው ከራሱ መንፈስ በስተቀር ከሰው መካከል የአንድን ሰው ሐሳብ የሚያውቅ ማን አለ? እንደዚሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በስተቀር፣ የእግዚአብሔርን ሐሳብ የሚያውቅ ማንም የለም። 12ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንምና፤ ይህም እግዚአብሔር በነጻ የሰጠንን እናውቅ ዘንድ ነው። 13እኛ የምንናገረው ይህን ነው፤ ከሰው ጥበብ በተማርነው ቃል ሳይሆን፣ ከመንፈስ በተማርነው ቃል እንናገራለን፤ መንፈሳዊ እውነትንም የምንገልጸው በመንፈሳዊ ቃል ነው።2፥13 ወይም መንፈሳዊ እውነትንም ለመንፈሳዊ ሰው እንገልጻለን 14መንፈሳዊ ያልሆነ ሰው ከእግዚአብሔር መንፈስ የሆነውን ነገር ሊቀበል አይችልም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ነገር ለእርሱ ሞኝነት ነው፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ፣ ሊረዳው አይችልም። 15መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉንም ነገር ይመረምራል፤ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም።

16“ያስተምረው ዘንድ፣

የጌታን ልብ ማን ዐወቀው?”

እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን።