1 ቆሮንቶስ 13 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ቆሮንቶስ 13:1-13

1በሰዎችና በመላእክት ልሳን13፥1 ወይም ቋንቋዎች ብናገር፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ነኝ። 2የትንቢት ስጦታ ቢኖረኝ፣ ምስጢርን ሁሉና ዕውቀትን ሁሉ ባውቅ፣ ተራራንም ከቦታው የሚነቅል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። 3ያለኝን ሁሉ ለድኾች ብሰጥ፣ ሰውነቴንም እንዲቃጠል ለእሳት ብዳርግ፣13፥3 አንዳንድ የጥንት ቅጆች፣ እንድታበይ አሳልፌ ብሰጥ ይላሉ። ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።

4ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ 5ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቈጥርም። 6ፍቅር ከእውነት ጋር እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። 7ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል።

8ፍቅር ከቶ አይወድቅም፤ ነገር ግን ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ ዕውቀትም ቢሆን ይሻራል። 9ምክንያቱም የምናውቀው በከፊል ነው፤ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው። 10ነገር ግን ፍጹም የሆነው ሲመጣ በከፊል የነበረው ይሻራል። 11ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅ ዐስብ ነበር፤ እንደ ልጅም አሰላ ነበር። ከጐለመስሁ በኋላ ግን የልጅነትን ነገር እርግፍ አድርጌ ትቻለሁ። 12አሁን የምናየው በመስተዋት ውስጥ እንደሚታይ በድንግዝግዝ ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን። አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ እኔ ራሴ ሙሉ በሙሉ የታወቅሁትን ያህል ዐውቃለሁ።

13እንግዲህ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።