1 ሳሙኤል 16 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ሳሙኤል 16:1-23

ሳሙኤል ዳዊትን መቅባቱ

1እግዚአብሔር ሳሙኤልን፣ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? ወደ ቤተ ልሔሙ ሰው ወደ እሴይ ስለምልክህ፣ ዘይት በቀንድ ሞልተህ ሂድ፤ ከልጆቹ አንዱ ንጉሥ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ” አለው።

2ሳሙኤል ግን፣ “ሳኦል ከሰማ ስለሚገድለኝ እንዴት መሄድ እችላለሁ?” አለ።

እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፣ ‘ለእግዚአብሔር ልሠዋ መጥቻለሁ’ በል። 3እሴይን ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፤ ከዚያም የምታደርገውን አሳይሃለሁ፤ የምነግርህንም ሰው ትቀባልኛለህ።”

4ሳሙኤል እግዚአብሔር ያለውን ነገር አደረገ። ቤተ ልሔም እንደ ደረሰም፣ የከተማዪቱ ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡ፣ እነርሱም “አመጣጥህ ለሰላም ነውን?” ብለው ጠየቁት።

5ሳሙኤልም፣ “አዎን፤ ለሰላም ነው፤ የመጣሁትም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ላቀርብ ነው፤ እናንተም ራሳችሁን ቀድሳችሁ ከእኔ ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ” ሲል መለሰላቸው። ከዚያም እሴይንና ልጆቹን ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱም እንዲመጡ ጠራቸው።

6እዚያ በደረሱ ጊዜም፣ ሳሙኤል ኤልያብን አይቶ፣ “በርግጥ እግዚአብሔር የቀባው ሰው እነሆ፤ በእግዚአብሔር ፊት ቆሟል” ብሎ ዐሰበ።

7እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፣ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው።

8ከዚያም እሴይ አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር ይህንም አልመረጠውም” አለው። 9እሴይም ሣማን አሳለፈ፤ ሳሙኤልም፣ “እርሱንም እግዚአብሔር አልመረጠውም” አለ። 10እሴይም ሰባቱን ልጆቹን በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር እነዚህንም አልመረጣቸውም” አለው። 11ቀጥሎም እሴይን፣ “ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸውን?” ሲል ጠየቀው።

እሴይም፣ “የሁሉም ታናሽ ገና አልመጣም፤ ነገር ግን በጎች እየጠበቀ ነው” ብሎ መለሰ።

ሳሙኤልም፣ “በል ልከህ አስመጣው፤ እስኪመጣ ድረስ አንቀመጥምና16፥11 አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ ዕብራይስጡ ግን አንሰበሰብምና ይላል።” አለው።

12ስለዚህ ልኮ አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፣ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ።

እግዚአብሔርም፣ “የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው” አለው።

13ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ፤ ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ።

ዳዊት ሳኦልን ማገልገሉ

14የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ስለ ራቀ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ16፥14 በዚህ እንዲሁም በቍጥር 15፡16 እና 23 ላይ ጐጂ መንፈስ ያሠቃየው ነበር።

15የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ እያሠቃየህ ነው። 16እንግዲህ በገና መደርደር የሚችል ሰው እንዲፈልጉ፣ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን አገልጋዮቹን ይዘዝ፤ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘው ክፉ መንፈስ ባንተ ላይ በሚመጣ ጊዜ በገና ይደረድርልሃል፤ ደኅናም ትሆናለህ።”

17ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው።

18ከአገልጋዮቹም አንዱ፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችለውን የቤተ ልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፣ እርሱም ጀግናና ተዋጊ ነው፤ በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” ብሎ መለሰ።

19ከዚያም ሳኦል፣ “ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” ሲል መልክተኞችን ወደ እሴይ ላከ። 20እሴይም እንጀራና በወይን ጠጅ የተሞላ አቍማዳ በአህያ አስጭኖ፣ የፍየል ጠቦትም አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው።

21ዳዊት ወደ ሳኦል መጥቶ አገልግሎቱን ጀመረ፤ ሳኦልም እጅግ ወደደው፣ እርሱም የሳኦል ጋሻ ጃግሬ ሆነ። 22ከዚያም ሳኦል፣ “ዳዊትን ወድጄዋለሁና ከእኔ ዘንድ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ፍቀድልኝ” ብሎ ወደ እሴይ ላከ።

23ክፉው መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ፣ ዳዊት በገናውን ይዞ ይደረድር ነበር፤ ሳኦልም ይሻለው ነበር፤ ክፉውም መንፈስ ከእርሱ ይርቅ ነበር።