ገላትያ 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ገላትያ 2:1-21

ጳውሎስን ሐዋርያት ተቀበሉት

1ከዐሥራ አራት ዓመት በኋላም፣ ዳግመኛ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ በዚህ ጊዜ ከበርናባስ ጋር ነበርሁ፤ ቲቶንም ይዤው ሄጄ ነበር። 2ካገኘሁትም መገለጥ የተነሣ ወደዚያ ሄድሁ፤ በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል ለእነርሱም ገለጥሁላቸው። ይሁን እንጂ፣ ምናልባት በከንቱ እየሮጥሁ ወይም ሮጬ እንዳይሆን በመሥጋት፣ ዋነኞች ለሚመስሉት ብቻ በግል ይህን አስታወቅኋቸው። 3ከእኔ ጋር የነበረው ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ቢሆንም፣ እንዲገረዝ አልተገደደም ነበር። 4ይህ ጕዳይ የተነሣው አንዳንድ ሐሰተኞች ወንድሞች በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘነውን ነጻነት ሊሰልሉና ባሪያዎች ሊያደርጉን ወደ እኛ ሾልከው በመግባታቸው ነው።

5ለእነዚህ ሰዎች ለአንድ አፍታ እንኳ አልተገዛንላቸውም፤ ይኸውም፣ የወንጌል እውነት ከእናንተ ጋር ጸንቶ እንዲኖር ነው።

6ዋነኛ መስለው ስለሚታዩት ሰዎች ማንነት እኔን አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ እነዚህም ሰዎች ለመልእክቴ የጨመሩልኝ ነገር የለም። 7ነገር ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት2፥7 ወይም ለአይሁድ ወንጌልን እንዲሰብክ ዐደራ እንደ ተሰጠው፣ እኔም ላልተገረዙት2፥7 ወይም ለአረማዊያን እንዲሁም 8 እና 9 ይመ ወንጌልን እንድሰብክ ዐደራ እንደ ተሰጠኝ ተገነዘቡ፤ 8ጴጥሮስን ለአይሁድ ሐዋርያ እንዲሆን የሠራ እግዚአብሔር፣ በእኔ የአሕዛብ ሐዋርያዊ አገልግሎትም ሠርቷል። 9እንደ አዕማድ የሚቈጠሩት ያዕቆብ፣ ጴጥሮስና2፥9 ግሪኩ ኬፋ ይላል፤ እንዲሁም 11 እና 14 ይመ ዮሐንስም የተሰጠኝን ጸጋ ባስተዋሉ ጊዜ፣ ለእኔና ለበርናባስ የትብብር ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ከዚያም እኛ ወደ አሕዛብ፣ እነርሱ ደግሞ ወደ አይሁድ እንድንሄድ ተስማሙ። 10አጥብቀው ዐደራ ያሉን ድኾችን ማሰባችንን እንዳናቋርጥ ብቻ ነው፤ እኔም ይህንኑ ለማድረግ ጓጕቼ ነበር።

ጳውሎስ ጴጥሮስን ተቃወመው

11ጴጥሮስ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ በግልጥ ስቶ ስለ ነበር፣ ፊት ለፊት ተቃወምሁት። 12አንዳንድ ሰዎች ከያዕቆብ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት፣ ከአሕዛብ ጋር ይበላ ነበር፤ እነርሱ በመጡ ጊዜ ግን፣ የተገረዙትን ወገኖች ፈርቶ ከአሕዛብ ራሱን በመለየት ገሸሽ ማለት ጀመረ፤ 13በርናባስም እንኳ በእነርሱ ግብዝነት እስኪወሰድ ድረስ፣ ሌሎቹም አይሁድ በግብዝነቱ ተባበሩት።

14ተግባራቸው እንደ ወንጌል እውነት አለመሆኑን በተረዳሁ ጊዜ፣ በሁሉም ፊት ጴጥሮስን እንዲህ አልሁት፤ “አንተ አይሁዳዊ ነህ፤ ሆኖም በአሕዛብ ሥርዐት እንጂ በአይሁድ ሥርዐት አትኖርም፤ ታዲያ አሕዛብ የአይሁድን ሥርዐት እንዲከተሉ እንዴት ታስገድዳቸዋለህ?

15“እኛ በትውልዳችን አይሁድ እንጂ፣ ‘ኀጢአተኞች አሕዛብ’ ያልሆንን፣ 16ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ፣ ሕግን በመጠበቅ እንደማይጸድቅ እናውቃለን። ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን፣ በክርስቶስ በማመን እንጸድቅ ዘንድ እኛም ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፤ ሕግን በመጠበቅ ማንም አይጸድቅምና።

17“በክርስቶስ ለመጽደቅ ስንፈልግ፣ እኛ ራሳችን ኀጢአተኞች መሆናችን ግልጽ ነው፤ ታዲያ ክርስቶስ ኀጢአት እንዲስፋፋ ያደርጋልን? ፈጽሞ አይደለም! 18ያፈረስሁትን መልሼ የምገነባ ከሆነማ፣ ሕግ ተላላፊ መሆኔን አረጋግጣለሁ። 19ለእግዚአብሔር እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቻለሁና። 20ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው። 21የእግዚአብሔርን ጸጋ አላቃልልም፤ ጽድቅ በሕግ በኩል የሚገኝ ከሆነማ፣ ክርስቶስ እንዲያው በከንቱ ሞተ ማለት ነዋ!”2፥21 አንዳንድ ተርጓሚዎች ትምህርተ ጥቅሱን ከ14 በኋላ ያደርጋሉ።