ዳንኤል 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዳንኤል 2:1-49

ናቡከደነፆር ያለመው ሕልም

1ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም ዐለመ፤ መንፈሱ ታወከ፤ እንቅልፍም ከእርሱ ራቀ። 2ያለመውንም ሕልም እንዲነግሩት ንጉሡ ጠንቋዮችን፣ አስማተኞችን፣ መተተኞችንና ኮከብ ቈጣሪዎችን2፥2 ወይም ከለዳውያንን እንዲሁም 4፡5 እና 10 እንዲጠሩ አዘዘ፤ እነርሱም ገብተው በፊቱ ቆሙ፤ 3እርሱም፣ “አንድ ሕልም ዐለምሁ፤ ሕልሙም ምን እንደ ሆነ2፥3 ወይም ምን እንደ ነበር ለማወቅ መንፈሴ ተጨንቋል” አላቸው።

4ከዚያም ኮከብ ቈጣሪዎቹ ለንጉሡ በአረማይክ2፥4 ይህ ምዕራፍ ከዚህ ጀምሮ እስከ ም 7 ድረስ የተጻፈው በአረማይክ ነው። ቋንቋ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! ሕልምህን ለአገልጋዮችህ ንገረን፤ እኛም እንፈታልሃለን” አሉት።

5ንጉሡም ለኮከብ ቈጣሪዎቹ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሕልሙንና ትርጕሙን ባትነግሩኝ አካላችሁ እንዲቈራረጥና ቤቶቻችሁም የፍርስራሽ ክምር እንዲሆኑ ወስኛለሁ፤ 6ነገር ግን ሕልሙንና ትርጕሙን ብትነግሩኝ፣ ስጦታና ሽልማት፣ ታላቅ ክብርም ከእኔ ትቀበላላችሁ፤ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ትርጕሙንም አሳውቁኝ።”

7እነርሱም እንደ ገና፣ “ንጉሥ ሕልሙን ለአገልጋዮቹ ይንገረን፤ እኛም እንተረጕመዋለን” ብለው መለሱ።

8ንጉሡም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ ምን ብዬ እንደ ወሰንሁ ስለምታውቁ፣ ጊዜ ለማራዘም እንደምትሞክሩ ተረድቼአለሁ፤ 9ሕልሙን ባትነግሩኝ፣ አንድ ቅጣት ይጠብቃችኋል፤ ሁኔታው ይለወጣል ብላችሁ በማሰብ የሚያሳስቱ ነገሮችንና ክፉ ሐሳቦችን ልትነግሩኝ አሲራችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ትርጕሙንም ልትነግሩኝ እንደምትችሉ በዚህ ዐውቃለሁ።”

10ኮከብ ቈጣሪዎቹም ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ንጉሡ የጠየቀውን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ሰው በምድር ላይ አይገኝም! ማንም ንጉሥ ምንም ያህል ታላቅና ኀያል ቢሆን፣ እንዲህ ዐይነት ነገር ማንኛውንም ጠንቋይ፣ አስማተኛ ወይም ኮከብ ቈጣሪን ጠይቆ አያውቅም። 11ንጉሡ የሚጠይቀው እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነው፤ በሰዎች መካከል ከማይኖሩት ከአማልክት በቀር ለንጉሡ የሚገልጽለት የለም።”

12ይህም ንጉሡን እጅግ አበሳጨው፤ አስቈጣውም፤ በባቢሎን ያሉ ጠቢባን ሁሉ እንዲገደሉም አዘዘ፤ 13ጠቢባን ሁሉ እንዲገደሉም ዐዋጅ ወጣ፤ ዳንኤልንና ጓደኞቹን ፈልገው እንዲገድሉ ሰዎች ተላኩ።

14የንጉሡ ዘበኞች አለቃ አርዮክ፣ የባቢሎንን ጠቢባን ለመግደል በመጣ ጊዜ፣ ዳንኤል በጥበብና በዘዴ አነጋገረው። 15የንጉሡን መኰንን፣ “ንጉሡ እንዲህ ዐይነት ከባድ ዐዋጅ ያወጣው ስለ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው፤ አርዮክም ነገሩን ለዳንኤል ገለጠለት። 16በዚህን ጊዜ፣ ዳንኤልም ገብቶ ሕልሙን ይተረጕምለት ዘንድ ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀው።

17ከዚህ በኋላ ዳንኤል ወደ ቤቱ ተመልሶ ለጓደኞቹ ለአናንያ፣ ለሚሳኤልና ለአዛርያ ነገሩን ገለጠላቸው። 18እርሱና ጓደኞቹ ከቀሩት የባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይገደሉ፣ የሰማይ አምላክ ምሕረት ያደርግላቸውና ምስጢሩንም ይገልጥላቸው ዘንድ እንዲጸልዩ አሳሰባቸው። 19ለዳንኤልም ምስጢሩ በሌሊት በራእይ ተገለጠለት፤ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ፤ 20እንዲህም አለ፤

“ጥበብና ኀይል የእርሱ ነውና፣

የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ።

21ጊዜንና ወቅትን ይለውጣል፤

ነገሥታትን በዙፋን ያስቀምጣል፣

ደግሞም ያወርዳቸዋል፤

ጥበብን ለጠቢባን፣

ዕውቀትንም ለሚያስተውሉ ይሰጣል።

22የጠለቀውንና የተሰወረውን ነገር ይገልጣል፤

በጨለማ ያለውን ያውቃል፤

ብርሃንም ከእርሱ ጋር ይኖራል።

23የአባቶቼ አምላክ ሆይ፤ አመሰግንሃለሁ፤

አከብርሃለሁም፤

ጥበብንና ኀይልን ሰጥተኸኛልና፤

ከአንተ የጠየቅነውን ነገር አሳውቀኸኛል፤

የንጉሡን ሕልም አሳውቀኸናል።”

ዳንኤል ሕልሙን ተረጐመ

24ዳንኤልም የባቢሎንን ጠቢባን እንዲገድል ንጉሡ ወዳዘዘው ወደ አርዮክ ሄዶ፣ “የባቢሎንን ጠቢባን አትግደል፤ ወደ ንጉሡ ውሰደኝ፤ እኔም ሕልሙን እተረጕምለታለሁ” አለው።

25አርዮክም ዳንኤልን ወዲያውኑ ወደ ንጉሡ በመውሰድ፣ “ሕልሙንና ትርጕሙን ለንጉሡ መግለጥ የሚችል ሰው ከይሁዳ ምርኮኞች መካከል አግኝቻለሁ” አለው።

26ንጉሡም ብልጣሶር የተባለውን ዳንኤልን፣ “ያየሁትን ሕልምና ትርጕሙን ልትነግረኝ ትችላለህን?” አለው።

27ዳንኤልም እንዲህ አለ፤ “አንድም ጠቢብ፣ አስማተኛ፣ ጠንቋይም ሆነ ቃላተኛ ንጉሡ የጠየቀውን ምስጢር መግለጥ የሚችል የለም፤ 28ነገር ግን ምስጢርን የሚገልጥ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱም በሚመጡት ዘመናት የሚሆነውን ነገር ለንጉሥ ናቡከደነፆር ገልጧል፤ በዐልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ በአእምሮህ የነበረው ሕልምና ራእይ ይህ ነው፤

29“ንጉሥ ሆይ፤ ተኝተህ ሳለ፣ አእምሮህ ወደ ፊት ሊሆን ስላለው ነገር ያሰላስል ነበር፤ ምስጢርን ገላጭ የሆነውም ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር አሳየህ። 30ይህ ምስጢር ለእኔ የተገለጠው፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ ታላቅ ጥበብ ስላለኝ አይደለም፤ ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ትርጕሙን እንድታውቅና በአእምሮህ ታሰላስለው የነበረው ነገር ምን እንደ ሆነ ትረዳ ዘንድ ነው።

31“ንጉሥ ሆይ፤ በፊት ለፊትህ ግዙፍ የሆነ፣ የሚያብረቀርቅና የሚያስፈራ ታላቅ ምስል ቆሞ አየህ፤ 32የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፣ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ከናስ የተሠሩ ነበሩ፤ 33ቅልጥሞቹም ከብረት፣ እግሮቹም ከፊሉ ከብረት፣ ከፊሉም ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ። 34ይህን በመመልከት ላይ ሳለህ፣ አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች መታቸው፤ አደቀቃቸውም። 35ወዲያውኑም ብረቱ፣ ሸክላው፣ ናሱ፣ ብሩና ወርቁ ተሰባበሩ፤ በበጋ ወራት በዐውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅም ሆኑ፤ ነፋስም አንዳች ሳያስቀር ጠራረጋቸው፤ ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን ታላቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሞላ።

36“ሕልሙ ይህ ነበር፤ አሁን ትርጕሙን ለንጉሥ እንናገራለን። 37ንጉሥ ሆይ፤ አንተ የነገሥታት ንጉሥ ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ሥልጣንን፣ ኀይልንና ክብርን ሰጥቶሃል፤ 38የሰው ልጆችን፣ የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፤ በየትም ቦታ ቢሆኑ፣ በሁሉም ላይ ገዥ አድርጎሃል፤ እንግዲህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ።

39“ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፤ ቀጥሎም በናስ የተመሰለው ሦስተኛ መንግሥት ይነሣል፤ መላውን ምድርም ይገዛል። 40በመጨረሻም ሁሉን ነገር እንደሚቀጠቅጥና እንደሚሰብር ብረት ብርቱ የሆነ አራተኛ መንግሥት ይነሣል፤ ብረት ሁሉን ሰባብሮ እንደሚያደቅ ከእርሱ በፊት የነበሩትን መንግሥታት ሁሉ ሰባብሮ ያደቅቃቸዋል። 41እግሮቹና ጣቶቹ ከፊል ብረትና ከፊል ሸክላ ሆነው እንዳየህ፣ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ነገር ግን ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ በከፊል የብረት ጥንካሬ ይኖረዋል። 42የእግሮቹ ጣቶች ከፊሉ ብረት ከፊሉ ሸክላ እንደ ሆኑ ሁሉ ይህም መንግሥት በከፊሉ ብርቱ በከፊሉ ደካማ ይሆናል። 43ብረትና ሸክላ ተደባልቀው እንዳየህ ሁሉ ሕዝቡም ድብልቅ ይሆናል፤ ብረትና ሸክላ እንደማይዋሃድ ሁሉ ሕዝቡም በአንድነት አይኖሩም።

44“በእነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። 45የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ የወረደውና ብረቱን፣ ናሱን፣ ሸክላውን፣ ብሩንና ወርቁን ያደቀቀው ድንጋይ ራእይ ትርጓሜ ይህ ነው፤

“ታላቁ አምላክ ወደ ፊት የሚሆነውን ለንጉሡ አሳይቶታል፤ ሕልሙ እውነት ነው፤ ትርጓሜውም የታመነ ነው።”

46ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነፆር በግንባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት፤ አከበረውም፤ መሥዋዕትና ዕጣንም እንዲያቀርቡለት አዘዘ። 47ንጉሡም ዳንኤልን፣ “ይህን ምስጢር ልትገልጥ ችለሃልና፣ በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክና የነገሥታት ጌታ፣ ምስጢርንም ገላጭ ነው” አለው።

48ንጉሡም ዳንኤልን በከፍተኛ ሥልጣን ላይ አስቀመጠው፤ እጅግ ብዙ ስጦታዎችንም ሰጠው፤ የመላው ባቢሎን አውራጃ ገዥ አደረገው፤ በባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ላይም አለቃ አድርጎ ሾመው። 49ከዚህም በላይ በዳንኤል አሳሳቢነት ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን የባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርጎ ሾማቸው፤ ዳንኤል ግን በቤተ መንግሥት ተቀመጠ።