ዘፀአት 30 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘፀአት 30:1-38

የዕጣን መሠዊያ

30፥1-5 ተጓ ምብ – ዘፀ 37፥25-28

1“ዕጣን የሚጤስበት መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሥራ። 2ርዝመቱና ጐኑ ባለ አንድ አንድ ክንድ30፥2 ርዝመቱና ጐኑ 0.5 ሜትር፣ ከፍታው 0.9 ሜትር ያህል ነው። የሆነ ከፍታውም ሁለት ክንድ የሆነ አራት ማእዘን ይሁን፤ ከመሠዊያው ጋር አንድ ወጥ የሆኑ ቀንዶች ይኑሩት። 3ላዩን፣ ጐኖቹን ሁሉና ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ለብጣቸው፤ ዙሪያውን የወርቅ ክፈፍ አብጅለት። 4መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች የሚይዙ፣ ከክፈፉ በታች ትይዩ የሆኑ ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ለመሠዊያው አብጅ። 5መሎጊያዎቹንም ከግራር ዕንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። 6መሠዊያውን ከመጋረጃው ፊት ለፊት፣ ይኸውም ከምስክሩ ታቦት ፊት፣ ከምስክሩ በላይ ካለው እኔ አንተን ከምገናኝበት ከስርየት መክደኛው ፊት አስቀምጠው።

7“አሮን መብራቶቹን በሚያዘጋጅበት ጊዜ፣ በየማለዳው ደስ የሚያሰኝ ሽታ ዕጣን በመሠዊያው ላይ ያጢስ። 8ምሽት ላይ መብራቶቹን በሚያበራበትም ጊዜ ዕጣኑን ማጠን አለበት፤ ይኸውም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ዕጣኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ዘወትር እንዲጤስ ነው። 9በዚህም መሠዊያ ላይ ሌላ ዕጣን ወይም ሌላ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የእህል መሥዋዕት አታቅርብ፤ የመጠጥ መሥዋዕትም አታፍስስበት። 10አሮን በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርግበታል፤ ይህ ዓመታዊ ማስተስረያ በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለማስተስረያ ከሚሆን የኀጢአት መሥዋዕት ደም ጋር መደረግ አለበት፤ ይህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅግ ቅዱስ ነው።”

የማስተስረያ ገንዘብ

11ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ 12“የእስራኤላውያንን ጠቅላላ ቈጠራ በምታደርግበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው በሚቈጠርበት ወቅት ለሕይወቱ ቤዛ የሚሆን ወጆ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መክፈል አለበት፤ በዚህም ዐይነት ስትቈጥራቸው በእነርሱ ላይ መቅሠፍት አይመጣም። 13ማንም ወደ ተቈጠሩት ዘንድ የሚያልፍ ሃያ አቦሊ በሚመዝን በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግማሽ ሰቅል30፥13 በዚህና በቍጥር 15 ላይ 6 ግራም ያህል ነው። መስጠት አለበት፤ ይህ ግማሽ ሰቅል ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። 14ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከሃያ በላይ ሆኖ ወደ ተቈጠሩት ያለፉት ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸው። 15ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ ባለጠጋው ከግማሽ ሰቅል በላይ፣ ድኻውም አጕድሎ አይስጥ። 16የማስተስረያውን ገንዘብ ከእስራኤላውያን ተቀብለህ ለመገናኛው ድንኳን አገልግሎት አውለው፤ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የእስራኤላውያን ማስተስረያ ይሆናል።”

የመታጠቢያ ሰን

17ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ 18“ለመታጠቢያ ከናስ ማስቀመጫው ጋር የናስ ሰን አብጅ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠህ ውሃ አድርግበት። 19አሮንና ወንዶች ልጆቹ በውስጡ ባለው ውሃ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡበታል። 20ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ሁሉ እንዳይሞቱ በውሃ ይታጠቡ፤ እንዲሁም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የእሳት መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ለማገልገል በሚቀርቡበት ጊዜ፣ 21እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠባሉ፤ ይህም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለአሮንና ለትውልዶቹ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል።”

ቅብዐ ዘይት

22ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፣ 23“ምርጥ ቅመሞችን፣ አምስት መቶ ሰቅል30፥23 ወደ 6 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ፈሳሽ ከርቤ፣ ግማሽ ይኸውም ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል ጣፋጭ ቀረፋ፣ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል ጠጅ ሣር፣ 24አምስት መቶ ሰቅል ብርጕድ ውሰድ፤ ሁሉም እንደ መቅደሱ ሰቅልና አንድ የኢን መስፈሪያ30፥24 ወደ 4 ሊትር ያህል ነው። የወይራ ዘይት ይሁን፤ 25እነዚህን በቀማሚ እንደ ተሠራ እንደሚሸት ቅመም የተቀደሰ ቅብዐ ዘይት አድርግ፤ የተቀደሰ ቅብዐ ዘይት ይሆናል። 26ከዚያም የመገናኛውን ድንኳን፣ የምስክሩን ታቦት፣ 27ጠረጴዛውንና ዕቃዎቹን ሁሉ፣ መቅረዙንና ዕቃዎቹን፣ የዕጣን መሠዊያውን፣ 28የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ እንዲሁም የመታጠቢያ ሰኑን ከነመቆሚያው እንድትቀባበት ይሁን። 29እጅግ የተቀደሱ ይሆኑም ዘንድ ቀድሳቸው፤ የሚነካቸውም ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል።

30“ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ቅባቸው፤ ቀድሳቸውም። 31ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ ‘በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ይህ የእኔ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ይሆናል። 32በማንም ሰው ሰውነት ላይ አታፍስሱት፤ በተመሳሳይ መንገድ ምንም ዘይት አትሥሩ፤ የተቀደሰ ነው፤ ቅዱስ መሆኑን ልብ በሉ። 33ተመሳሳይ ዐይነት የሠራና ከካህናት ሌላ በማንም ሰው ላይ ያፈሰሰ ሁሉ ከወገኑ ይወገድ።’ ”

ዕጣን

34ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ተመጣጣኝ በማድረግ የጣፋጭ ሽቱ ቅመሞች፣ የሚንጠባጠብ ሙጫ፣ በዛጐል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፣ የሚሸት ሙጫ እና ንጹሕ ዕጣን ወስደህ፣ 35በቀማሚ እንደ ተሠራ ጣፋጭ መዐዛ ያለው የተቀመመ ዕጣን አብጅ፤ በጨው የተቀመመ፣ ንጹሕና የተቀደሰ ይሁን። 36ከእርሱም ጥቂቱን ወቅጠህ ዱቄት በማድረግ አልመህ በመገናኛው ድንኳን ከምስክሩ ፊት ለፊት ከአንተ ጋር በምገናኝበት ስፍራ አስቀምጠው፤ ለአንተ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። 37ለራስህ በዚያ ዐይነት መንገድ ምንም ዐይነት ዕጣን አታብጅ። ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ መሆኑን ልብ በል። 38በመልካም ሽታው ይደሰት ዘንድ እርሱን አስመስሎ የሚሠራ ሁሉ ከወገኑ የተወገደ ይሁን።”