ዘዳግም 6 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘዳግም 6:1-25

አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ

1ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ በምትወርሷት ምድር እንድትጠብቁት አስተምራችሁ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰጠኝ ትእዛዝ፣ ሥርዐትና ሕግ ይህ ነው፤ 2ይኸውም፣ የምሰጣችሁን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ሁሉ በመጠበቅ፣ ዕድሜያችሁ እንዲረዝም፣ አንተ፣ ልጆችህና ከእነርሱ በኋላ የሚመጡት ልጆቻቸው በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትፈሩት ዘንድ ነው። 3እንግዲህ እስራኤል ሆይ ስማ፤ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት፣ ማርና ወተት በምታፈስሰው ምድር መልካም እንዲሆንልህና እጅግ እንድትበዛ፣ ትእዛዙንም ትጠብቅ ዘንድ ጥንቃቄ አድርግ።

4እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አንድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው6፥4 ወይም፣ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ እግዚአብሔር አንድ ነው ወይም እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ እግዚአብሔር ብቻውን5አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ። 6ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች በልብህ ያዝ። 7ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር። 8በእጅህ ላይ ምልክት አድርገህ እሰራቸው፤ በግንባርህም ላይ ይሁኑ። 9በቤትህ መቃኖች በግቢህም በሮች ላይ ጻፋቸው።

10አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለአንተ ለመስጠት ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ወደ ማለላቸው ምድር ሲያስገባህ፣ በዚያም ያልሠራሃቸውን ታላላቅና ያማሩ ከተሞችን፣ 11የራስህ ባልነበሩ መልካም ነገሮች ሁሉ የተሞሉ ቤቶችን፣ ያልቈፈርሃቸውን የውሃ ጕድጓዶች፣ ያልተከልሃቸውን የወይን ተክሎችና የወይራ ዛፎች ሲሰጥህና በልተህም ስትጠግብ፣ 12ከባርነት ምድር ከግብፅ ያወጣህን እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዳትረሳ ተጠንቀቅ!

13አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ፍራ፤ እርሱን ብቻ አገልግል፤ በስሙም ማል። 14በዙሪያህ ያሉ ሕዝቦች የሚያመልኳቸውን ሌሎች አማልክት አትከተል፤ 15ምክንያቱም በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቀናተኛ አምላክ (ኤሎሂም) ስለሆነ፣ በአንተም ላይ ቍጣው ስለሚነድድ፣ ከምድር ገጽ ያጠፋሃል። 16በማሳህ እንዳደረጋችሁት አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አትፈታተኑት። 17አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰጣችሁን ትእዛዞች፣ መመሪያዎችና ሥርዐቶች በጥንቃቄ ጠብቁ። 18መልካም እንዲሆንልህና እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶችህ በመሐላ እንድትወርሳት፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ተስፋ የሰጣቸውን መልካሚቱን ምድር ገብተህ ቀናና መልካም የሆነውን አድርግ፤ 19እግዚአብሔር (ያህዌ) በተናገረው መሠረትም ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ ታስወጣለህ። 20በሚመጡት ዘመናት ልጅህ፣ “አምላካችን እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) ያዘዛችሁ የመመሪያዎቹ፣ የሥርዐቶቹና የሕጎቹ ትርጕም ምንድን ነው?” ብሎ በሚጠይቅህ ጊዜ፣ 21እንዲህ በለው፤ “እኛ በግብፅ የፈርዖን ባሮች ነበርን፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን በብርቱ እጅ ከግብፅ አወጣን። 22እኛ በዐይናችን እያየን እግዚአብሔር (ያህዌ) ታላላቅና አስፈሪ የሆኑ ታምራዊ ምልክቶችና ድንቆችን በግብፅ፣ በፈርዖንና በመላው ቤተ ሰዎቹ ላይ አደረገ። 23እኛን ግን ለአባቶቻችን በመሐላ ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ሊያስገባንና ሊሰጠን ከዚያ አወጣን። 24ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ምንጊዜም መልካም እንዲሆንልንና በሕይወት እንድንኖር ይህን ሥርዐት ሁሉ እንድንፈጽም፣ አምላካችንንም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንድንፈራ እግዚአብሔር (ያህዌ) አዘዘን። 25እንግዲህ ይህን ሁሉ ሕግ እርሱ ባዘዘን መሠረት፣ በአምላካችን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ተጠንቅቀን ከጠበቅን፣ ያ ለእኛ ጽድቃችን ይሆናል።”