ዘዳግም 32 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘዳግም 32:1-52

1ሰማያት ሆይ፤ አድምጡ፤ እኔም እናገራለሁ፤

ምድር ሆይ፤ አንቺም የአፌን ቃል ስሚ።

2ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትውረድ፤

ቃሌም እንደ ጤዛ ይንጠባጠብ፤

በቡቃያ ሣር ላይ እንደ ካፊያ፣

ለጋ ተክልም ላይ እንደ ከባድ ዝናብ ይውረድ።

3እኔ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ዐውጃለሁ፤

የአምላካችንን (ኤሎሂም) ታላቅነት አወድሱ!

4እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤

መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤

የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣

ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው።

5በእርሱ ላይ ክፋት ፈጽመዋል፤ ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ ልጆቹ አይደሉም፤

ወልጋዳና ጠማማ ትውልዶች ናቸው32፥5 ወይም የተጣመሙት እነርሱ እንጂ የእርሱ ልጆች አይደሉም

6አንተ ተላላና ጥበብ የጐደለህ ሕዝብ፣

ለእግዚአብሔር (ለያህዌ) የምትመልስለት በዚህ መንገድ ነውን?

አባትህ ፈጣሪህ32፥6 ወይም ያወጣህ አባትህ።

የሠራህና ያበጀህ እርሱ አይደለምን?

7የጥንቱን ዘመን አስታውስ፤

አባትህን ጠይቅ፤ ይነግርሃልም፤

ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ያስረዱሃል።

8ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን በሰጠ ጊዜ፣

የሰውንም ዘር በለያየ ጊዜ፣

በእስራኤል ልጆች32፥8 የማሶሬቱ ቅጅ፣ የሙት ባሕር ጥቅልል እንዲሁም የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይላሉ። ቍጥር ልክ፣

የአሕዛብን ርስት ድንበር ለየ፤

9የእግዚአብሔር (ያህዌ) ድርሻ የገዛ ሕዝቡ፣

ያዕቆብ የተለየ ርስቱ ነውና።

10እርሱን በምድረ በዳ፣

ባዶና ጭው ባለ በረሓ ውስጥ አገኘው፤

ጋሻ ሆነው፤ ተጠነቀቀለትም፤

እንደ ዐይኑ ብሌን ጠበቀው።

11ንስር ጐጆዋን በትና፣

በጫጩቶቿም ላይ እንደምትረብብ፣

እነርሱን ለመያዝ ክንፎቿን እንደምትዘረጋ፣

በክንፎቿም እንደምትሸከማቸው፣

12እግዚአብሔር (ያህዌ) ብቻ መራው፤

ምንም ባዕድ አምላክ አብሮት አልነበረም።

13በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤

የዕርሻንም ፍሬ መገበው፤

ከዐለት ድንጋይ ማር አበላው፤

ከባልጩትም ድንጋይ ዘይት መገበው።

14የላሙንና የበጉን መንጋ ቅቤና ወተት፣

የሰቡትን በጎችና ፍየሎች፣

የባሳንን ምርጥ አውራ በግ፣

መልካም የሆነውንም ስንዴ፣

ማለፊያውንም የወይን ጠጅ።

15ይሹሩን32፥15 ይሹሩን ማለት ቅን ወይም ትክክለኛ ማለት ሲሆን፣ ይኸውም እስራኤልን የሚያሳይ ነው። ወፈረ፤ ረገጠ፤

ጠገበ፤ ሰውነቱ ደነደነ፤ ለሰለሰ፤

የፈጠረውንም አምላክ (ኤሎሂም) ተወ፤

መጠጊያ ዐለት የሆነውን አዳኙንም ናቀ።

16በባዕዳን አማልክታቸው አስቀኑት፤

በአጸያፊ ጣዖቶቻቸውም አስቈጡት።

17አምላክ ላልሆኑ አጋንንት፦

ላላወቋቸው አማልክት፣

ከጊዜ በኋላ ለተነሡ አማልክት፣

አባቶቻችሁ ላልፈሯቸው አማልክት ሠዉ።

18አባት የሆነህን ዐለት ከዳኸው፤

የወለደህን አምላክ ረሳኸው።

19እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህን አይቶ ናቃቸው፤

በወንድና በሴት ልጆቹ ተቈጥቷልና።

20እርሱም፣ “ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤

መጨረሻቸው ምን እንደሚሆንም አያለሁ” አለ፤

ጠማማ ትውልድ፣

የማይታመኑም ልጆች ናቸውና።

21አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤

በከንቱ ጣዖቶቻቸው አስቈጡኝ።

እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ።

በማያስተውልም ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ።

22በቍጣዬ እሳት ተቀጣጥሏልና፤

እርሱ እስከ ሲኦል ዘልቆ ይነድዳል።

ምድርን እስከ ሰብሏ ይበላል፤

የተራሮችንም መሠረት ያቀጣጥላል።

23“በመዓት ላይ መዓት አመጣባቸዋለሁ።

ፍላጻዬንም በእነርሱ ላይ እጨርሳለሁ።

24የሚያጠፋ ራብ፣ በልቶ የሚጨርስ ቸነፈርና ከባድ

መቅሠፍት እሰድድባቸዋለሁ፤

የአራዊትን ሹል ጥርስ፣ በምድር የሚሳብ የእባብ መርዝም

እሰድድባቸዋለሁ።

25ሰይፍ መንገድ ላይ ያስቀራቸዋል፤

ቤታቸውም ውስጥ ድንጋጤ ይነግሣል፤

ጕልማሳውና ልጃገረዷ፣

ሕፃኑና ሽማግሌው ይጠፋሉ።

26እበትናቸዋለሁ፤ ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውን

አጠፋለሁ አልሁ፤

27ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ፣

‘ድል ያደረገችው እጃችን እንጂ፣

እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህን ሁሉ አላደረገም’ እንዳይሉ፣

የጠላትን መነሣሣት ሠጋሁ።”

28አእምሮ የጐደላቸው፣

ማስተዋልም የሌላቸው ናቸው።

29አስተዋዮች ቢሆኑ ኖሮ ይህን በተገነዘቡ፣

መጨረሻቸውም ምን እንደሚሆን ባስተዋሉ ነበር።

30መጠጊያ ዐለታቸው ካልሸጣቸው፣

እግዚአብሔር (ያህዌ) ካልተዋቸው በቀር፣

አንድ ሰው እንዴት ሺሑን ያሳድዳል?

ሁለቱስ እንዴት ዐሥር ሺሑን እንዲሸሹ ያደርጋሉ?

31የእነርሱ መጠጊያ ዐለት እንደ እኛ መጠጊያ

ዐለት አይደለምና፤ ጠላቶቻችንም እንኳ ይህን አይክዱም።

32ወይናቸው ከሰዶም ወይን፣

ከገሞራም ዕርሻ ይመጣል፤

የወይናቸው ፍሬ በመርዝ፣

ዘለላቸውም በምሬት የተሞላ ነው።

33ወይናቸው የእባብ መርዝ፣

የመራዥ እባብም መርዝ ነው።

34“ይህ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ ያለ፣

በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን?

35በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ፤

ጊዜው ሲደርስ እግራቸው ይሰናከላል፤

የመጥፊያቸው ቀን ቀርቧል፤

የሚመጣባቸውም ፍርድ ፈጥኖባቸዋል።”

36ኀይላቸው መድከሙን፣

ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አለመቅረቱን በሚያይበት ጊዜ፣

እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሕዝቡ ይፈርዳል፤

ለአገልጋዮቹም ይራራል።

37እንዲህም ይላል፤ “መጠጊያ ዐለት የሆኗቸው፣

እነዚያ አማልክታቸው የት አሉ?

38የመሥዋዕታቸውን ሥብ የበሉ፣

የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ አማልክት ወዴት ናቸው?

እስቲ ይነሡና ይርዷችሁ!

እስቲ መጠለያ ይስጧችሁ!

39“እኔ ራሴ እርሱ እንደ ሆንሁ እዩ፤

ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤

እገድላለሁ፤ አድናለሁም፤

አቈስላለሁ፤ እፈውሳለሁም፤

ከእጄም የሚያስጥል ማንም የለም።

40እጄን ወደ ሰማይ አነሣለሁ፤

ለዘላለምም ሕያው እንደ ሆንሁ እናገራለሁ፤

41የሚያብረቀርቅ ሰይፌን ስዬ፣

እጄ ለፍርድ ስትይዘው፣

ባላጋራዎቼን እበቀላቸዋለሁ፤

የሚጠሉኝንም እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ።

42ሰይፌ ሥጋ በሚበላበት ጊዜ፣

ፍላጾቼ በደም እንዲሰክሩ አደርጋለሁ፤

ደሙ የታረዱትና የምርኮኞች፣

የጠላት አለቆችም ራስ ደም ነው።”

43አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ32፥43 ወይም፣ ሕዝቦች ሆይ፤ ደስ ይበላችሁ።32፥43 የማሶሬቱ ቅጅ፣ የሙት ባሕር ጥቅልል እንዲሁም የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም፣ ሕዝቦች ሆይ፤ መላእክት ሁሉ ለእርሱ ይስገዱ ይላሉ።

እርሱ የአገልጋዮቹን ደም ይመልሳል፤

ጠላቶቹንም ይበቀላል።

ምድሪቱንና ሕዝቡን ይቤዣቸዋልና።

44ሙሴም ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ጋር መጥቶ የዚህን መዝሙር ቃሎች በሕዝቡ ጆሮ ተናገረ። 45ሙሴም እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለመላው እስራኤል ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ 46እንዲህ አላቸው፤ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዟቸው፣ እኔ ዛሬ በግልጥ የምነግራችሁን ቃሎች ሁሉ በልባችሁ አኑሩ። 47ቃሎቹ ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃሎች አይደሉም፤ በእነርሱ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፣ በምትወርሷትም ምድር ረዥም ዘመን ትኖራላችሁ።

ሙሴ በናባው ተራራ ላይ መሞቱ

48በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 49“ከኢያሪኮ ማዶ ባለው የሞዓብ ምድር፣ ከዓባሪም ተራሮች አንዱ ወደ ሆነው ወደ ናባው ተራራ ወጥተህ ለእስራኤላውያን ርስት አድርጌ የምሰጣትን የከነዓንን ምድር አሻግረህ ተመልከት። 50ወንድምህ አሮን በሖር ተራራ ላይ እንደ ሞተና ወደ ወገኖቹ እንደ ተሰበሰበ ሁሉ፣ አንተም በወጣህበት በዚያ ተራራ ላይ ሙት፤ ወደ ወገኖችህም ተሰብሰብ። 51ይህ የሚሆንበት ምክንያት ሁለታችሁም በጺን ምድረ በዳ፣ በቃዴስ በመሪባ ውሃ አጠገብ በእኔ ላይ መታመናችሁን በእስራኤላውያን ፊት ስላጐደላችሁና ቅድስናዬንም በእስራኤላውያን መካከል ስላላከበራችሁ ነው። 52ስለዚህ ምድሪቱን ከሩቅ ሆነህ ታያታለህ እንጂ፣ ለእስራኤል ሕዝብ ወደምሰጣት ምድር አትገባም።”