ዘዳግም 20 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘዳግም 20:1-20

ለጦርነት መውጣት

1ጠላቶችህን ለመውጋት ወደ ጦርነት ስትሄድ፣ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ከአንተ የሚበልጥ ሰራዊትንም በምታይበት ጊዜ አትፍራቸው፤ ከግብፅ ያወጣህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከአንተ ጋር ነውና። 2ወደ ውጊያው ቦታ ስትቃረቡ፣ ካህኑ ወደ ፊት ወጣ ብሎ ለሰራዊቱ ይናገር፤ 3እንዲህም ይበል፤ “እስራኤል ሆይ ስማ፤ በዛሬው ቀን ጠላቶቻችሁን ለመግጠም ወደ ጦርነት ልትገቡ ነው፤ ልባችሁ አይባባ፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በጠላቶቻችሁ ፊት አትሸበሩ፤ 4ድልን ያቀዳጃችሁ ዘንድ ስለ እናንተ ጠላቶቻችሁን ሊወጋ አብሯችሁ የሚወጣው አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ነውና።”

5አለቆቹም ለሰራዊቱ እንዲህ ይበሉ፤ “አዲስ ቤት ሠርቶ ያላስመረቀ አለን? ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ፤ አለዚያ በጦርነቱ ላይ ይሞትና ቤቱን የሚያስመርቀው ሌላ ሰው ይሆናል። 6ወይን ተክሎ ገና ያልበላለት አለን? ወደ ቤቱ ይመለስ፤ አለዚያ በጦርነቱ ላይ ይሞትና ወይኑን ሌላ ሰው ይበላዋል። 7ሚስት አጭቶ ያላገባት አለን? ወደ ቤቱ ይመለስ፤ አለዚያ በጦርነቱ ይሞትና ሌላ ሰው ያገባታል።” 8ከዚያም አለቆቹ፣ “የሚፈራ ወይም ልቡ የሚባባ ሰው አለን? የወንድሞቹም ልብ እንዳይባባ ወደ ቤቱ ይመለስ” በማለት ጨምረው ይናገሩ።

9አለቆቹ ለሰራዊቱ ተናግረው ሲያበቁ፣ አዛዦችን በሰራዊቱ ላይ ይሹሙ።

10አንድን ከተማ ለመውጋት በምትዘምትበት ጊዜ፣ አስቀድመህ ለሕዝቧ የሰላም ጥሪ አስተላልፍ፤ 11ከተቀበሉህና ደጃቸውን ከከፈቱልህ፣ በከተማዋ ውስጥ ሕዝብ ሁሉ ገባርህ ይሁን፤ ያገልግልህም። 12ዕርቀ ሰላምን ባለመቀበል ውጊያን ከመረጡ፣ ከተማዪቱን ክበባት። 13አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አሳልፎ በእጅህ በሰጠህ ጊዜ፣ በውስጧ ያሉትን ወንዶች በሙሉ በሰይፍ ግደላቸው። 14ነገር ግን ሴቶቹን ሕፃናትን፣ እንስሳቱንና በከተማዪቱ ውስጥ የሚገኘውን ማናቸውንም ነገር በምርኮ ለራስህ አድርግ፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከጠላቶችህ የሚሰጥህን ምርኮ ልትጠቀምበት ትችላለህ። 15እንግዲህ የአካባቢህ አሕዛብ ከተሞች ባልሆኑትና ከአንተ እጅግ ርቀው በሚገኙት ከተሞች ሁሉ ላይ የምታደርገው ይኸው ነው።

16አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጥህ በአሕዛብ ከተሞች ውስጥ፣ እስትንፋስ ያለውን ነገር አታስተርፍ። 17ኬጢያዊውን፣ አሞራዊውን፣ ከነዓናዊውን፣ ፌርዛዊውን፣ ኤዊያዊውንና ኢያቡሳዊውን አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባዘዘህ መሠረት ፈጽመህ ደምስሳቸው20፥17 የዕብራይስጡ ቃል አንድን ነገር ወይም አንድን ሰው ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያሳይ ነው።18አለዚያ አማልክታቸውን በሚያመልኩበት ጊዜ የሚፈጽሟቸውን አስጸያፊ ተግባራት ሁሉ ታደርግ ዘንድ ያስተምሩሃል፤ በአምላክህ በእግዚአብሔርም (ኤሎሂም ያህዌ) ላይ ኀጢአት ትሠራለህ። 19አንድን ከተማ ተዋግተህ ለመያዝ የረጅም ጊዜ ከበባ ካደረግህ፣ ዛፎቹን በመጥረቢያ ጨፍጭፈህ አታጥፋ፤ የእነርሱን ፍሬ መብላት ትችላለህና አትቍረጣቸው፤ ከብበህ የምታጠፋቸው የሜዳ ዛፎች ሰዎች ናቸውን?20፥19 ወይም፣ ለመክበብ ወረደ፤ የዛፎቹ ፍሬ ለሰው ጥቅም ይዋሉ 20የሚበላ ፍሬ እንደማያፈራ የምታውቀውን ዛፍ ግን ልትቈርጠውና ጦርነት የምታካሂድባትን ከተማ በድል እስክትቈጣጠራት ድረስ ለከበባው ምሽግ መሥሪያ ልትጠቀምበት ትችላለህ።