ዘካርያስ 4 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘካርያስ 4:1-14

የወርቁ መቅረዝና ሁለቱ የወይራ ዛፎች

1ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክም ተመልሶ፣ አንድ ሰው ከእንቅልፉ እንደሚነቃ አነቃኝ፤ 2እርሱም፣ “ምን ታያለህ?” አለኝ።

እኔም እንዲህ አልሁ፤ “እነሆ፤ በዐናቱ ላይ የዘይት ማሰሮ ያለበት ሁለንተናው ወርቅ የሆነ መቅረዝ አየሁ፤ በመቅረዙም ላይ ሰባት ቧንቧዎች ያሏቸው ሰባት መብራቶች ነበሩ። 3ደግሞም አንዱ ከዘይቱ ማሰሮ በስተ ቀኝ፣ ሌላውም በስተ ግራ የሆኑ ሁለት የወይራ ዛፎች አሉ።”

4ያነጋግረኝ የነበረውንም መልአክ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው” አልሁት።

5እርሱም፣ “ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን?” አለኝ።

እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አላውቅም” አልሁት።

6ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ለዘሩባቤል የተላከው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ ‘በመንፈሴ እንጂ በኀይልና በብርታት አይደለም’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

7“ታላቅ ተራራ ሆይ፤ አንተ ምንድን ነህ?4፥7 ወይም ማለት ነህ በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፤ ሰዎች፣ ‘ሞገስ ይሁንለት! ሞገስ ይሁንለት!’ ብለው እየጮኹ፣ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል።”

8ደግሞም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 9“የዘሩባቤል እጆች የዚህን ቤተ መቅደስ መሠረት ጣሉ፤ የሚፈጽሙትም የእርሱ እጆች ናቸው። ከዚያም እግዚአብሔር ጸባኦት እኔን ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ።

10“የጥቂቱን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው? ሰዎች በዘሩባቤል እጅ ቱንቢውን ሲያዩ ይደሰታሉ።

“እነዚህ ሰባቱ በምድር ሁሉ የሚዘዋወሩ የእግዚአብሔር ዐይኖች ናቸው።”

11ከዚያም መልአኩን፣ “ከመቅረዙ በስተ ቀኝና በስተ ግራ ያሉት እነዚህ ሁለት የወይራ ዛፎች ምንድን ናቸው?” አልሁት።

12እንደ ገናም፣ “በሁለቱ የወርቅ ቧንቧዎች አጠገብ የወርቅ ዘይት የሚያፈስሱት እነዚህ ሁለት የወይራ ቅርንጫፎች ምንድን ናቸው?” አልሁት።

13እርሱም፣ “ምን እንደ ሆኑ አታውቅምን?” አለኝ።

እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አላውቅም” አልሁት።

14እርሱም፣ “እነዚህ ሁለቱ የምድርን ሁሉ ጌታ ለማገልገል የተቀቡ4፥14 ወይም እና ሁለቱ ዘይትና የሚያመጡ ናቸው” አለኝ።